
ʺ ሡሪ ቢሏችሁ ጨርቅ ነው ወይ
የታጠቀ ነው ከልቡ ላይ ”
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 07/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ዘመኑ የጭንቅ ዘመን ነበር፡፡ ወንድ ልጅ ተኝቶ የማያድርበት፣ ሴት ልጅ ልጆቿን በሰላም የማታሳድግበት፡፡ የጣልያን ወራሪ ኢትዮጵያን የወረረበት፡፡ አርበኞች ዱር ቤቴ ብለው ከቤት እንደወጡ አልተመለሱም፡፡ አልመው እየተኮሱ ጠላትን በጥይት ምጣድ እያመሱ ነበር፡፡ ከዛሬ ነገ ይወጣል የተባለው ጠላት ዓመታትን አስቆጠረ፡፡ በዚህ ሁሉ ጊዜ ጥይት ሳይተኮስ፣ የጠላት ወታደር ሳይሸበር የዋለበት ቀን አልነበረም፡፡ የአርበኞች ትንቅንቅ ቀጥሏል፡፡ 1933 ዓ.ም ደረሰ፡፡ የጣልያን ሠራዊት ባሩዱን፣ ሰይፍና ጎራዴውን መቻል ተስኖት ጓዙን እየሸከፈ እየወጣ ነው፡፡ ያልቻለው በኢትዮጵያዊያን ጦር ተወግቶ፣ በሳንጃ ተበልቶ በዱር በገደሉ ቀርቷል፡፡
በመጨረሻው ዓመት ጣልያንን ጠራርጎ ለማስውጣት አርበኞች ሁሉ ወኔያቸው ጨምሯል፡፡ በሰሜን በጌምድር ጠቅላይ ግዛት በደብረታቦር አውራጃ በፋርጣ ወረዳ በክምር ድንጋይ ምክትል ወረዳ፣ መገንዲ ጊዮርጊስ ደብር፣ በጋይድባ ውስጥ አርበኛው ፊታውራሪ መለሰ ከተማ ነብሰ ጡር ባለቤታቸውን ትተው ወደ መጨረሻው ዘመቻ ሄደዋል፡፡ በለስ ከቀናቸው ድል አድርገው ይመለሳሉ፡፡ በለስ ካልቀናቸውም ለውድ ሀገራቸው መስዋዕት ሆነው ሊቀሩ ይችላሉ፡፡ ዘመቻ ሲሄዱ የሚገጥምን መገመት ከባድ ነበር፡፡ ባለቤታቸው ዘውዲቱ ተሰማ ይባላሉ። ባለቤታቸውን ወደ ዘመቻ የሸኙት ወንድ ልጅ ወልደው ሞት በነጠቃቸው ጊዜ ነበር፡፡ የልጃቸው ሐዘን አልወጣላቸውም፡፡ በማሕጸናቸው የያዙት ልጅ ወንድ ቢሆንላቸው ምኞታቸው ከፍ ያለ ነበር፡፡
ፊታውራሪ መለሰ ከዘመቻው አልተመለሱም፡፡ የወይዘሮ ዘውዲቱ መውላጃ ጥር 28/ 1933 ዓ.ም ደረሰ፡፡ ምጥ መጣ፡፡ ወንድ ልጅ ተገላገሉ፡፡ ደስታ ሆነ፡፡ ፈጣሪ የልባቸውን መሻት የሰጣቸው እናት ልጃቸውን ማንተፋርዶ ሲሉ ስም አወጡለት፡፡ አስቀድሞ መስፍን ያሉት ወንድ ልጃቸው በሞት ተነጥቀዋልና ከፈጣሪ ጋር ማን ይፋረዳል ሲሉ ነበር ማንተፋርዶ ያሉት፡፡ ኢትዮጵያ ድል አደረገች፡፡ አርበኞች የልፋታቸውን ዋጋ አገኙ፡፡ ፊታውራሪ መለሰ ዘመቻውን በድል አጠናቅቀው ተመለሱ፡፡ ጀግናው ከዘመቻ ሲመለሱ ወንድ ልጅ አግኝተዋልና ደስታቸው እጥፍ ድርብ ሆነ፡፡ ያ ብላቴና ለቤተ ዘመዱ ብርቅ ነበርና ያገኘው ሁሉ ስም ያወጣለት ነበር፡፡ አያቱ እማሆይ አዱኛ አገኝ አሉት፣ አንድ አክስቱ ደግሞ ቢክስ ብለው ጠሩት። ፈንታነሽ እምሩ የተባሉ ሌላ አክስቱ ደግሞ አንድነህ አሉት። አባቱና የክርስትና አባቱ ደግሞ ኀይለ እንድርያቆስ አሉት። አሥራ አራት ስሞችም ወጡለት፡፡ መታደል ነው፡፡
ከወጡት አሥራ አራት ሥሞች ኀይለ እንድርያቆስ የሚለው ስም እየገነነ ሄደ፡፡ ይሄም ሙሉ ስያሜውን ይዞ አልቀጠለም፤ እንድርያቆስ የሚለው ቀርቶ ኀይለ ወደ ኃይሌ ተቀይሮ ዋነኛ መጠሪያ ስሙ ኃይሌ ተባለ፡፡ ሲፈለጉ የተገኙት ብላቴና የዛሬው ብርጋዴር ጄነራል ኃይሌ መለሰ ናቸው፡፡ አባታቸው ፊታውራሪ መለሰ በአካባቢው የታወቁ አርበኛና አንደበተ ርቱዕ ነበሩ። የተናሩት የሚጥምላቸው፡፡ ያያቸው እጅ የሚነሳቸው የታፈሩና የተከበሩ ጀግና፤ ብላቴናው በስስት አደጉ፡፡ እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ወደ ቄስ ትምህርት ቤት ሄደው ፊደል ቆጠሩ፡፡ ዳዊትም ደገሙ፡፡ በዘመኑ የዓለማዊ ትምህርት ቤት ነበር፡፡ ልጃቸውን በስስት የሚያዩት ወላጆች ግን ከአጠገባቸው እንዲርቁ ስላልፈለጉ መላክን አልመረጡም፡፡ ኃይሌ ግን ዘመናዊ ትምህርት መማር ይሹ ነበርና መማርን መረጡ፡፡ በስስት ያደጉት ልጅ ከቤተሰቦቻቸው ርቀው ደብረታቦር ሄዱ፡፡ በዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ዓለማዊ ትምህርት ጀመሩ፡፡
ኃይሌ ትምህርታቸውን አጠናክረው ቀጠሉ፡፡ ስድስተኛ ክፍል ሲደርሱም አባታቸው ፊታውራሪ መለሰ ሕይወታቸው አለፈች፡፡ የኃይሌ ልብ ተሰበረች፡፡ አብዝተው አዘኑ፡፡ ኃይሌ የአባታቸውን ርዕስትና ጉልት መረከብ፣ የአባታቸውን ስልጣን የመውረስ ኃላፊነት ተጣለባቸው፡፡ ዘመናዊ ትምህርታቸውን አቋረጡ፡፡ ፊታውራሪ መለሰ ነጭ ለባሽ ነበሩ፡፡ ልጃቸው ኃይሌም ያን ማዕረግ ተቀበሉ፡፡ የነጭ ለባሽ ሻምበል ሆኑ። ጊዜው ነጎደ፡፡ እናታቸው ወይዘሮ ዘውዲቱ ባለቤታቸውን ተከትለው ወደማይቀረው ዓለም አሸለቡ፡፡ የኃይሌ ልብ የበለጠ ተጎዳች፡፡ ወላጆቻቸውን በሞት የተነጠቁት ወጣቱ ሹም ጭንቀታቸው ከፍ አለ፤ የተጣሉባቸውን እልፍ ኃላፊነቶች መወጣት ከባድ ነበርና፡፡
ዓመታት እልፈው 1960 ዓ.ም ደረሰ፡፡ የአፄው ሥርዓት ለብሔራዊ ጦር ሻለቃነት ሰው ይመለምል ነበር፡፡ ኃይሌ ተመረጡ፡፡ ወረታ በሚገኘው 11ኛ ሻለቃ ብሔራዊ የጦር ካምፕ ውስጥ የመጀመሪያ ደረጃና መሠረታዊ የእግረኛ ጦር ትምህርታቸውን አጠናቀቁ፡፡ ይህንንም እንዳጠናቀቁ ደብረዘይት ለምለም ጣቢያ ወደሚገኘው 4ኛ ሻለቃ የብሔራዊ ጦር ዋና ማሰልጠኛ በእጩ መኮንንነት ለመሰልጠን ተጠሩ። የመኮንን ስልጠናቸውን አጠናቀቁ፡፡ ሌላ ስልጠናም መጣላቸው፡፡ ወደ ሆለታ ገነት የመኮንኖች ትምህርት ቤት አቀኑ፡፡ በዚህ ትምህርት ቤት ቀዳሚ ኾነው ትምህርታቸውን አጠናቀቁ፡፡ ከንጉሠ ነገሥቱም ሽልማት ተቀበሉ፡፡
ከሆለታ ገነት የመኮንኖች የጦር ትምህርት ቤት በምክትል መቶ አለቃነት የተመረቁት ኃይሌ መለሰ ደብረዘይት በሚገኘው 4ኛ ሻለቃ የብሔራዊ ጦር ማሰልጠኛ የትምህርት መኮንን ሆነው ተመደቡ። ስመ ጥር መኮንንም ሆኑ፡፡ ፊቼ መናገሻ ወደሚገኘው 2ኛ ሻለቃ ብሔራዊ ጦርም ተቀየሩ። በሐምሌ 7/ 1965 ዓ.ም. አዲስ አበባ ወደሚገኘው የብሔራዊ ጦር ጠቅላይ መምሪያ የትምህርት መኮንን ሆነው ተዛወሩ። ሙሉ መቶ አለቃም ሆኑ፡፡ ሆለታ ባመጡት ውጤት የጦሩን ስም ስላስጠሩ በጠቅላይ መምሪያው ከጦሩ አዛዥ ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ ጀምሮ እስከ ታች ባሉት የጠቅላይ መምሪያው አባላት ዘንድ በጣም የተከበሩና ተወዳጅ መኮንን ሆኑ። ኃይሌ ኃይሌ የሚላቸው በዛ፡፡ በጠዋት የተፈተኑት ጀግና ልባቸው በድፍረት የተመላች ነበረችና ነው፡፡ ጠቅላይ መምሪያው ውስጥ ለአንድ ዓመት ያክል እንዳገለገሉ ኮሎኔል አጥናፉ አባተ የብሔራዊ ጦር ሁለት ተወካዮች እንዲልክ ጠቅላይ መምሪያውን ጠየቁ፡፡ መቶ አለቃ ኃይሌ መለሰና ሃምሣ አለቃ ጌታቸው ተቀባ ሰኔ 21/1966 ዓ.ም በጦሩ ተመርጠው ወደ 4ኛ ክፍለ ጦር ተላኩ።
ሌላ ዘመን መጣ፡፡ የንጉሡ ሥርዓት አበቃ፡፡ ወታደራዊ መንግሥት ሀገሪቱን ያዛት፡፡ የወንድ ሚዛን የሆኑት የዚያኔው ወጣት መቶ አለቃ ወታደራዊ መንግሥቱ ሚዛን እንዳይስት አብዘተው ይታገሉ ጀመሩ፡፡ ሀገሪቱን በብስለት ለማስተዳደር ውይይት ተደረገ፡፡ ውይይቱ መቋጫ የሌለውን የመንግሥቱ ኃይለ ማርያምን ስልጣን ገደብ እንዲኖረው የሚያደርግና ሌሎች ውሳኔዎች የተላለፉበት ነበር፡፡ በውይይቱም መንግሥቱ የሚኒስትሮች ምክርቤት ሰብሳቢ ብቻ እንዲሆኑ ሲያደርግ፣ ለኮሎኔል አጥናፉ መከላከያውንና ደኅንነቱን በሥራቸው አድርገው እንዲይዙ ስልጣን ተሰጥቷቸው ነበር።
ጀግናው የጦር መሪ ኃይሌ መለሰ ደግሞ የጎንደር ክፍለ ሀገር ቋሚ የደርግ ተጠሪ ሆነው ተመደቡ፡፡ ሹመታቸው ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ጎንደር ውስጥ ተማሪዎች ፒያሳ ላይ ሰላማዊ ሰልፍ ሲያደርጉ በወታደሮች በመገደላቸውና የጎንደር ሕዝብ ያምፃል ተብሎ ስለተፈራ ሻምበል ኃይሌ ራሳቸውን ጨምሮ 9 የደርግ አባላትና 2 ከፍተኛ የሕዝብ ድርጅት ባለስልጣናት የተካተቱበት ቡድን በኃላፊነት መርተው በመሄድ ሕዝቡን እንዲያረጋጉ ተላኩ።
በዚህም ጊዜ የደርግ ባለስልጣናት ኃይሌ የማይደራደሩባቸው ጉዳዮችን አነሳ፡፡ የጎንደርን ሕዝብ ትጥቅ እናስፈታ፣ የጎንደር ሕዝብ በቀይ ሽብር መመታት አለበትና ሌሎች ለድርድር የማይቀርቡ ጥያቄዎችን አነሳ፡፡ ኀይሌ አይሆንም አሉ፡፡ በጎንደር ሕዝብ ላይ የያዙትን አቋም አለውጥም አሉ፡፡ ዘጠኝ አባላት በተሳተፉበት በዚህ ውይይት ስምንቱ በጎንደር ሕዝብ ላይ የታሰበው ይፈፀም ሲሉ ኃይሌ ግን አይሆንም አሉ፡፡ በሀሳባቸው እንደፀኑ የውይይታቸውን ሪፖርት ለመንግሥቱ ኃይለ ማርያም ላኩ፡፡ መንግሥቱም ʺእኛ ትዕዛዝ እስከምንሰጥ ድረስ ጉዳዩ በይደር ይቀመጥ፣ ተፈፃሚ እንዳይሆን፤ ቃለ ጉባኤውን ግን ቶሎ ላኩልን” አሉ። ጉዳዩ ከፍተኛ ሚስጥር ነበርና ሚስጥርነቱን ለመጠበቅ ሲባል በደርግ አባል እጅ ተላከ።
ሻምበል ኃይሌ የመሩት ቡድን ጎንደር ውስጥ በዚህ አይነት ውጥረት ላይ እንዳለ የእነ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ቡድን ʺለምሳ አስበውን የነበሩትን፣ ለቁርስ አደረግናቸው” ብሎ እነ ጄኔራል ተፈሪ በንቲን መግደሉን በዜና አስነገረ። ኃይሌና መርተውት የሄዱት ቡድንም ጎንደር ላይ እያደረገ ያለውን ሕዝብን የማረጋጋት ሥራ አቋርጦ በ24 ሰዓት ውስጥ ሪፖርት እንዲያደርግ የቴሌግራም መልዕክት ደረሰው።
ኃይሌ ጥያቄውን ትተው ሸፍተው ሊቀሩ አስበው ነበር፡፡ ጊዜው አጭር ነበርና አልተሳካም፡፡ ወደ አዲስ አበባ አቀኑ፡፡ የጎንደርን ሕዝብ በቀይ ሽብር አላስመታም ያሉት የጦር መኮንኑ ለጎንደር ገዥ ተብለው የነበሩት በእንቢተኝነታቸው ምክንያት ሹመታቸው ተሰረዘ፡፡
ኢትዮጵያን ከባድ ፈተና ገጠማት፡፡ የደርግ መንግሥት ሳይጠና ሶማሊያ ኢትዮጵያን ወረረች፡፡ ቆራጡ ወታደር ወደ ጦር ግንባር ይዘምቱ እንደሆነ ተጠየቁ፡፡ ጥያቄውን በደስታ ተቀበሉት፡፡ ወታደሮቻቸውን አሰልጥነው ዘመቱ፡፡ ደፋሩ የጦር ሰው አሰልጥነው ይዘው የዘመቱት ጦር ከገበሬው የተውጣጣ ሕዝባዊ ሠራዊት ጦር ነበር። ጦራቸው 69ኛው ብርጌድ 4 ሻለቆች ሊኖሩት ሲገባ 3 ሻለቆች ብቻ ነበሯቸው። ይህም የሆነው ከ69ተኛ በፊት የዘመተው 68ኛ ብርጌድ የሰው ኃይል ስላልተሟለለት አንድ ሻለቃ ጦራቸውን ለ68ኛ ብርጌድ ስለሰጡ ነው፡፡ በሠጡት ሻለቃ ጦር እንደሚተካላቸው ቃል ተገብቶላቸው ነበር። ነገር ግን በነበረው አጣዳፊ ሁኔታ ሻለቃ ጦራቸው ሳይተካላቸው በሦስት ሻለቆች ብቻ የተዋቀረውን ብርጌዳቸውን ይዘው ወደ ውጊያው ግንባር ገቡ።
ኃይሌ የመሩት ጦር የመጀመሪያውን ከባድ ውጊያ ያደረገው ድሬዳዋ አጠገብ “ፉላ ቦራ” ድልድይን ላለማስያዝ በተደረገው ውጊያ ላይ ነበር። ያቺን ቀን ኃያሉ የጦር መሪ በማስታወሻቸው ሲያሰፍሩ ʺድሬዳዋ ላይ እያለን የሶማሊያ ጦር ከፋቱሌ ኤረር ጉታ የሚያልፈውን የባቡርና የመኪና መንገድ ፉላ ቦራ ላይ ሊዘጋ ነው ስለተባለ እንድንከላከል ትዕዛዝ ተሰጠኝ። በሁርሶ በኩል አልፈን የተሰጠን የግዳጅ ቦታ ለመያዝ ስንቃረብ፣ ፉላ ቦራ ላይ የሶማሊያ ጦር አድፍጦ ጠበቀን። የመድፍ፣ የታንክና የላውንቸር ተኩስ አወረደብን። የሚሊሺያው ጦር ከትምህርት ውጭ የተግባር ውጊያ ሲገጥም ገና የመጀመሪያው ስለሆነ የከባድ መሣሪያው ተኩስ ረበሸውና ተበረገገብኝ። አንድ የሬዲዮ መገናኛ ሠራተኛና ከሦስት የማይበልጡ ወታደሮችን እንደያዝኩ በሶማሊያ ጦር ተከበብኩ። የከበበንን ከፍተኛ የሶማሊያ ጦር ተከላክለንና ሰብረን የምንወጣበት አንዳችም አቅም አልነበረንም። እንደ አንድ የደርግ አባልና የብርጌድ አዛዥ መኮንን ደግሞ እጄን ለጠላት ሰጥቼ መማረክ ፈፅሞ የማይታሰብ ነበር። ስለዚህ በእንዲህ ያለው ችግር ጊዜ እንድጠቀምበት የተሰጠኝን ፈንጅ አውጥቸ በእጄ ይዤ እራሴን ለማጥፋት ስል፣ በጌታቸው ተቀባ የሚመራው 2ኛ ሻለቃ ጦር ከየት መጣ ሳይባል በሶማሊያው ጦር ላይ ሠፈረበት። የእኔም ሕይዎት ከሞት አፋፍ ተመለሰች” ብለዋል፡፡
ʺ ሡሪ ቢሏችሁ ጨርቅ ነው ወይ
የታጠቀ ነው ከልቡ ላይ ” የተባለላቸው ደፋሩ የጦር መሪ ጦርነታቸውን ቀጠሉ፡፡ ጦራቸውን አረጋጉ፡፡ ውጊያው ቀጠለ፡፡ በጀግናው የሚመራው ብርጌድ የሶማሊያ ጦር ሊያንበራግገው ቀርቶ ተኩስ ሲሰማ ድል እየናፈቀው ስለመጣ የእርሱን ክንድ ሊመክት የሚችል የሶማሌ ጦር ጠፋ። ድሬዳዋንና አካባቢውን ተከላክሎ ማዳን ብቻ ሳይሆን የማጥቃት አድማሱን በማስፋት ፉላ ቦራን፣ ቢዮ ባይህን፣ አራቢን፣ ጎሎልቻን፣ ደንበልን፣ ጭናቅሰንን፣ ጅግጅጋን፣ ካራማራን፣ ደገሐቡርን፣ ቀብሪዳህርን ከሶማሊያ ወራሪ ጦር ነፃ አውጥቶ በመቆጣጠር የምሥራቁን ግንባር ጦርነት በድል እንዲጠናቀቅ አደረገ፡፡ በጀግናው የጦር መሪ የሚመራው ብርጌድ ጀግንነቱ አጀብ አስባለ፤ የሚገጥመውን መከራ በድል እየተወጣ ገሰገሰ፡፡ ድልም ተቀዳጄ፡፡ ይህ ብርጌድ በኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን በኩባውያንም ዘንድ የተመሠከረለት ብርጌድ ነበር፡፡
በቤተሰቦቻቸው በተዘጋጄው ታሪክ እንዲህ የሚል ነገር ሰፍሯል ʺጦርነቱን ለመጀመር ስንሰለፍ አንድ መኪና አልነበረንም። በኋላ ግን ከሶማሊያ ጦር የማረክነው የመኪና ብዛት የአንድን ክፍለጦር ሙሉ ሊያጓጉዝ የሚችል ነበር። ባዙቃ ለአይነት እንኳን አንድም አልነበረንም፤ ግን ከወራሪው የሶማሊያ ጦር በመማረክ መኪና ላይ እንደፍልጥ ከመርነው። ውጊያውን ስንጀምር መትረጌስ በቁጥር ብቻ ጥቂት ነበሩን። በኋላ ግን እርሱንም እንደፍልጥ መኪና ላይ ከመርነው። ስንጀምር የስንቅ ችግር ነበረብን። በኋላ ግን የምናባርረውን የሶማሊያን ስንቅ ስለተረከብነው የተትረፈረፈ ስንቅ ነበረን” ይላል፡፡
ጀግናው የጦር መሪ ዝናቸው ከፍ እያለ ሄደ፡፡ ማዕረጋቸውም እንደዚያው፡፡ ከጦርነት በኋላ የባሕር ዳር አውራጃ አስተዳደሪ ሆነው ተሾሙ፡፡ አያሌ ሥራዎችን በጥበብ ከወኑ፡፡ ማዕረጋቸው ከፍ ብሎ የሸዋ ክፍለ ሀገር ወታደራዊ ኮሚሣር ሆነው ተሾሙ፡፡ በዚያም አያሌ ሥራዎች ሠሩ፡፡ ሥራቸው ቀጠለ፡፡
ደፋሩ ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌ በትግራይ ክፍለ ሀገር በዚያ አስቸጋሪ ሠዓት አያሌ ሥራዎችን ከወኑ፡፡ ወደ ትውልድ ሥፍራቸው የኢሠፓ ሹም ሆነውም መጡ፡፡ በዚህ ጊዜ ደርግን ለመጣል ሲጣደፉ የነበሩት ታጣቂዎች መምጣታቸውን ሰሙ፡፡ እሳቸውም ጦር አዘጋጅተው በእብናት፣ በሐሙስ ወንዝና በመና ልከው ተከዜን ተሻግሮ የመጣውን ቡድን መቱት፡፡ የደርግ ሥርዓት እየተዳከመ ሄደ፡፡ ታጣቂዎቹ እያየሉ መጡ፡፡ ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌም በትግላቸው ቀጠሉ፡፡ ቤተሰቦቻቸው 7 ጊዜ ቆስለዋል ይላሉ፡፡
የደርግ ባለስልጣናት ውጊያው እየገፋ ሲሄድ ወደ አዲስ አበባ መሄድን መረጡ፡፡ የጦር መኮንኖች ወደ አዲስ አበባ ሲሄዱ ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌ እንዲህ አሉ ʺዳሩን ጠንክረን ካልጠበቅነው፣ መሃሉ ዳር አይሆንም ያለው ማነው? በዚህ ሁኔታ አዲስ አበባስ አትደፈርም ያለው ማነው? አዲስ አበባ ስትያዝስ ወዴት ነው የሚሸሸው? ይህ ትከሻየ ላይ የጫንኩት ማዕረግም እጄን አንከርፍፌ ለጠላት እንድሰጥም ሆነ ሕዝቤን ለጠላት አጋልጨ ሰጥቼ እንድሸሽ አይፈቅድልኝም። ከሁሉም በላይ ደግሞ እኒያ ጊዜ የማይሽራቸው የቆራጥነት ተምሳሌት የሆኑት ታላቁ ንጉሥ አፄ ቴዎድሮስ ለጠላት እጅን አንከርፍፎ መስጠትን አላስተማሩኝም። ስለዚህ ከዚህ በኋላ በፍፁም ለሽሽት እግሬን አላነሳም። በማንኛውም መልኩ አስተዳድረው ወደ ነበረው ሕዝቤ ተመልሼ ችግሩን እካፈላለው። ቢችል ያግዘኝና ተጋግዘን ጠላታችንን እናሸንፋለን። ባይሳካልኝም እንደ እንቧይ ከበቀልኩበት ምድር እረግፋለሁ እንጅ የትም አልሄድም” አሉ፡፡ የማይሻር የጀግንት ውሳኔያቸው ነው፡፡
ጀግናው ደማቸውን እያዘሩ ወደ ዘጌ ሄዱ፡፡ በጀልባም ወደ ደራ አቀኑ፡፡ የሽምቅ ውጊያ ቀጠሉ፡፡ እርሳቸውን ተከትለዋል የሚባሉ ሁሉ መከራው በዛባቸው፡፡ የደርግ የስልጣን ዘመን ተጠናቋል፡፡ የጀግና ውኃ ልክ ግን እጅ መስጠት አልሻም ብለዋል፡፡ ወደ ኬኒያም አቀኑ፡፡ በዚያም ሆነው ለትግል አላረፉም፡፡ ለሌላ ትግል ነገሮችን አመቻችተው ወደ ሱዳን አመሩ፡፡ ትግላቸውን ቀጠሉ፡፡ የትግል መንገዳቸው ግን አስቸጋሪ ነበር፡፡ ይባስ ብሎ ጄነራሉ በሱዳን መንግሥት ታሰሩ፡፡ ወዳጆቻው ይፈቱልን ሲሉ ጥያቄ አቀረቡ፡፡ ጥያቄው በዋዛ የሚተው አልነበረም፡፡ ጄኔራሉ በብዙ ትግል ተፈቱ፡፡ ወደ ኒውዝላንድም ሄዱ፡፡ ቆይተውም ወደ አውስትራሊያ አቀኑ፡፡ በዚያም ሆነው ስለሀገራቸው ሳያስቡ የማያድሩት የጦር መሪው ʺበሀገሬ ላይና በወገኔ መሀል ሆኜ ለወገኔ እየታገልኩ እንደ እንቧይ ከበቀልኩበት መሬት ላይ መርገፍ ነው የዘወትር ፍላጎቴ” ይሉ ነበር ይባላል፡፡
አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው ሕወሓት በነፍስ ማጥፋትና በሌሎች ወንጀሎች ከሷቸው እንደነበር የሚነገረው ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌ መለሰ በቀረበባቸው ክስ ላይ ʺበመሠረቱ እኔ በግል ኃላፊነቴ ገበያ ላይ የማይገኝ የሰው ሕይወት ቀርቶ ተሠርቶ የሚገኝ ሀብትና ንብረት ወስደህብኛል ብሎ የሚጠይቀኝ አንድም ኢትዮጵያዊ እንደማይኖር ሥራየንና ተዘዋውሬ ያገለገልኩትን ሕዝብ ምሥክር አድርጌ እቆማለሁ። እንዲያውም ለልጆቼና ለቅርብ ወገኖቸ የማወርሳቸው አንጡራ ሀብትና ቋሚ ቅርስ ብትኖረኝ ይህቺው ያልተጉደፈደፈች ስምና ተግባሬ ናት።” ብለው ነበር፡፡ ኢትዮጵያን እስከ ሕይወት መስጠት ድረስ የሚወዷት ጀግናው የጦር መሪ ትሁት እንደነበሩም ይነገርላቸዋል፡፡
እኒህ የጦር መሪ በዘመናቸው የኅብረተሰባዊት ኢትዮጵያ ታላቅ የክብር ኮከብ ኒሻን 1ኛ ደረጃ፣ የየካቲት 66 አብዮት ኒሻን 1ኛ ደረጃ ፣ በአውስትራሊያ የፐርዝ ነዋሪዎች 2 ኒሻኖችና 2 ዋንጫዎችን ተሸልመዋል፡፡
የጀግናው ዘመን ተጠናቀቀች፡፡ ወደማይቀረው ዓለም የመጠራት ዘመን ደረሰ፡፡ ኢትዮጵያዬ እንደገና የመወለድ እድል ቢኖረኝ ወታደር ሁኜ ላገለግልሽ ከፍተኛ ፍላጎት ነበረኝ ይሉ የነበሩት ጀግና ለሞት እጅ ሰጡ፡፡ ጀግናው የጦር መሪ ነብሴ ኢትዮጵያ ውስጥ ትለፍ ብለው እንደተመኙ በሀገራቸው ግንቦት 03/2013 ዓ.ም ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌ መለሰ የ7 ልጆች አባት ነበሩ። ለክብር መዝመት፣ ለሀገር መሞት ደስታቸው ነበር፡፡ መልካም ረፍት
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m