
“በኮሮና ቫይረስ ተይዘው በጽኑ ህመም ደረጃ የሚገኙ ሰዎች የመተንፈሻ መሳሪያ በማጣት ህይወታቸው ከማለፉ በፊት አስቀድሞ የመከላከሉ ሥራ አስፈላጊ ነው” ዶክተር ሙሉነሽ አበበ
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 07/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የኀብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኮሮናቫይረስ ስርጭት የመከላከልና የመቆጣጠር ዘመቻን ውጤታማ ለማድረግ ይቻል ዘንድ ከጸጥታና ከፍትሕ እንዲሁም ከአስፈጻሚ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ደረጃ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የአማራ ክልል የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ እና የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከላከልና መቆጣጠር ግብረ ኃይል ሰብሳቢ ሙሉነሽ አበበ (ዶ.ር) ”ዳግም ትኩረት ለኮሮናቫይረስ” በሚል ዘመቻ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
ባለፉት ጊዜያት በሀገሪቱ በተከሰቱት የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት ለኮሮናቫይረስ የተሰጠው ትኩረት በመቀነሱ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ በቫይረሱ በተያዙ ሰዎች 4ኛ እና በጽኑ ህመም ላይ በሚገኙ ታማሚዎች ደግሞ 1ኛ ወይም የከፋ ደረጃ ላይ እንደደረሰች ተናግረዋል።
“በሽታው በሀገራችን እያደረሰ ያለውን ጉዳት በሚነጥቀን የሀገራችን ታላላቅ ሰዎች መረዳት እንችላለን” ነው ያሉት፡፡ ”አሁን ላይ በችግሩ መስፋትና በመከላከያ ቁሳቁስ እጥረት ምክንያት በኮሮና ቫይረስ ተይዘው በጽኑ ህመም ደረጃ የሚገኙ ሰዎች የመተንፈሻ መሳሪያ በማጣት ህይወታቸው ከማለፉ በፊት አስቀድሞ የመከላከሉ ሥራ አስፈላጊ ነው” ብለዋል።
ማስተማር፣ ሕግ ማስከበርና የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባት መስጠት የመከላከሉ ሥራ አካል መሆናቸውን የጠቀሱት ዶክተር ሙሉነሽ በክልሉ በተሳሳተ ግንዛቤ ምክንያት የቫይረሱን መከላከያ ክትባት መወሰድ የሚገባውን ያክል እንዳልሆነ ነው የጠቆሙት።
እያንዳንዱ ተቋም ሠራተኞቹ የኮሮናቫይረስ ስርጭት የመከላከል ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የማድረግ ግዴታ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ – ከደብረታቦር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m