የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን በ22 ሚሊየን ብር ወጪ በኮምቦልቻ ከተማ ያስገነባዉ የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ማማ ተመረቀ፡፡

251

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን በ22 ሚሊየን ብር ወጪ በኮምቦልቻ ከተማ ያስገነባዉ የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ማማ ተመረቀ፡፡

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 07/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የማማው ሥራ መጀመር ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ የሚሰጠዉን አገልግሎት አስተማማኝ ለማድረግ ያግዛል ተብሏል፡፡ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን በሀገር ዉስጥ ያለዉን የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍን ለማሳደግና ደኅንነቱ የተጠበቀ ለማድረግ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን የኮርፖሬት ዳይሬክተር ጄኔራል እና ተወካይ ኃላፊ አቶ ፈቃዱ ዉለታዉ ተናግረዋል፡፡

ተቋሙ በተለያዩ አካባቢዎች የማስፋፊያ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው ከነዚህ መካከል የኮምቦልቻ የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ማማ አንዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኮምቦልቻ የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ማማ ለክልሉ አጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አቶ ፈቃዱ ገልጸዋል፡፡ ካሁን ቀደም በራዲዮ መገናኛ ይሰጥ የነበረዉን የትራንስፖርት የቁጥጥር ሥርዓት በማስቀረት የቁጥጥር ስራዉ ዓለም አቀፍ ደረጃዉን የጠበቀ እንዲሆንና ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ የሚሰጠዉ አገልግሎት አስተማማኝ እንዲሆን ያስችላል ነው ያሉት፡፡

የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ማማዉ ዘመናዊ ኤሮነቲካል የድምጽ መሣሪያዎች የተገጠሙለት ነው፡፡ ከአየር ትራፊክ መቆጣጠር ሥራ በተጨማሪ የአየር ትንበያ ሥራዎችን መሥራት እንዲችል ተደረጎ መገንባቱንም አቶ ፈቃዱ አመላክተዋል፡፡

በአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ማማዉ ምረቃ ላይ የተገኙት የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሰይድ መሃመድ የኮምቦልቻ ኤርፖርት በቅርብ ጊዜ ወደ ሥራ የገባ ቢሆንም ከፍተኛ የተጠቃሚ ቁጥር ማስተናገድ የቻለ በመሆኑ የአየር መቆጣጠሪያ ማማ መገንባቱና አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ለአካባቢዉ ኢንቨስትመንት እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል፡፡

ኤርፖቱ በቀን 3 ጊዜ በረራ እያስተናገደ ቢሆንም አገልግሎቱን የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር በማደጉ የበረራ አገልግሎት ሊጨምር ይገባል ነው ያሉት፡፡

ዘጋቢ፡- አሊ ይመር – ከኮምቦልቻ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleʺብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌ የነጻነት፣ የአንድነት፣ የጀግንነት ፊደል ስለሆኑ ፊደል ይነበባል እንጂ አይሞትም” ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ
Next articleየአማራ ሊግ ክለቦች የ2013 ዓ.ም የማጠቃለያ ውድድር በባሕር ዳር መካሄድ ጀመረ።