ʺብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌ የነጻነት፣ የአንድነት፣ የጀግንነት ፊደል ስለሆኑ ፊደል ይነበባል እንጂ አይሞትም” ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ

179

ʺብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌ የነጻነት፣ የአንድነት፣ የጀግንነት ፊደል ስለሆኑ ፊደል ይነበባል እንጂ አይሞትም” ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 07/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌ መለሰ አስከሬን በክብር ወደ ደብረታቦር ተሸኝቷል፡፡
የጀነራሉ አስክሬን በባሕር ዳር ፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ሥርዓተ ፍትሃት ተፈጽሞለት ነው የተሸኘው፡፡ በአስከሬን
ሽኝቱ የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳደር ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ፣ የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ
አባል ብፁዕ አቡነ አብረሃምን ጨምሮ የሃይማኖት አባቶች፣ የትግል ጓደኞቻቸው፣ ቤተሰቦቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው
ተገኝተዋል፡፡
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ፈንታ ማንደፍሮ (ዶ.ር) በሽኝቱ ላይ እንደተናገሩት ጄኔራል ኃይሌ ኢትዮጵያ በተፈተነችበት ቀን
የፈተናዋን ጥያቄ የመለሱ ታላቅ ጀግና ነበሩ፡፡ ያረፉበት ዘመንም ኢትዮጵያ መልሳ በተፈተነችበት ጊዜ በመሆኑ ለዚህ ትልውልድ
ታላቅ መልዕክት አለው ብለዋል፡፡ በዚያድ ባሬ የተመራውን የሶማሊያ ጦር ኢትዮጵያን ሲወር ጦር እየመሩ ሀገር ነጻ ያደረጉ ጀግና
ናቸውም ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ በዳር ድንበሯ እንደ ቅርጫ ስጋ ሊከፋሏት የፈለጉ ሁሉ ባሰፈፉበት ጊዜ በአጭር ቀን አሰልጥነው
መቁሰልን እሾህ እንደመውጋት ሳይቆጥሩ ነጻ የሚያወጡ ልጆች ዛሬ አለን ወይ? ሲሉም ጠይቀዋል፡፡
ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌ ታፍሰው ሳይሆን መርጠው ወታደር የሆኑ፣ ያዋጉ፣ ኢትዮጵያ አምጣ የወለደቻቸው የጦር ጠበብት ናቸው
ነው ያሉት ዶክተር ፈንታ፡፡
ብርጋዴር ጄነራል ኃይሌ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የአንድት ቀንዲል ናቸውም ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ በተወረረችበት ኹሉ የዘመቱ ነጻ
ያወጡ፣ ድንብራቸው ኢትዮጵያ የሆነች ናቸውም ብለዋቸዋል፡፡ ጄነራሉ የጦር መሪ ብቻ ሳይሆኑ ፖለቲከኛና የአስተዳደር ሰው
እንደነበሩም አስታውሰዋል፡፡
በጎንደር ሕዝብ የተደገሰውን የቀይ ሽብር የተቃዎሙና አሻፈረኝ ያሉ ስለመሆናቸውም አንስተዋል፡፡ ለማሉለት ቃልና ለሕዝባቸው
የኖሩ ወታደራዊ ሣይንስን በቅጡ የተረጎሙ ታላቅ ጀግና ናቸውም ነው ያሉት፡፡ ጄኔራል ኃይሌ ታላቅ የነጻነት ቀንዲል ናቸው ያሉት
ዶክተር ፈንታ እስከ እለተ ህልፈታቸው ድረስ በኢትዮጵያ ጉዳይ የማይደራደሩ እንደነበሩም ተናግረዋል፡፡ በሀገሩ ላይ ኾኖ ሀገሩን
ለመሸጥ የሚደራደር ባለበት ዘመን ላይ ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌ ግን በሰው ሀገርም ኾነው በመከራ ቀን ለሀገራቸው የቆሙ
ናቸውም ነው ያሉት፡፡
በነበራቸው የፖለቲካ ብስለት ኢትዮጵያ ዛሬ የገጠማት ችግር እንደሚገጥማት ያውቁ እንደነበርና ያም እንዳይሆን ትግል ሲያደርጉ
እንደነበሩም አስታውሰዋል፡፡
ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌ ታሪክ ሠርተው አልፈዋል ያሉት ዶክተር ፈንታ እኛ ዛሬ ታሪክ ፈተና ጽፎ ባቆመልን ሰዓት ቆመናል፣ ይህን
ፈተና ማለፍ ነው የዚህ ትውልድ ኃላፊነት ነው ያሉት፡፡ ሀገር ስትሸነሸን፣ እኛ በየሰፈሩ እየተሸነሸንን፣ ሀገር አልፋ ስትሰጥ፣ በገዛ
ማዕዳችን ላይ ሌሎች እጃቸውን ሲሰዱ ቆመን የምናይ ስለሆን በሞታቸው ትንሣኤያችንን ማሰብ አለብንም ነው ያሉት፡፡
“ብርጋዴል ጄኔራል ኃይሌ የነጻነት፣ የአንድት፣ የጀግንነት ፊደል ስለሆኑ ፊደል ይነበባል እንጂ አይሞትም” ይነበባሉ ይቀጥላሉም
ብለዋል፡፡ ልጆቻችን የእርሳቸውን ጀግንነት ይማሩታልም ነው ያሉት፡፡
በውጭ ሀገራት ኾነውም ስለ ኢትዮጵያ አንድነት፣ ስለ ጠላቶቿ ሴራ ሲፅፉ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡ ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌ
የምንነሳበት ደወል፣ ሕያው የሆኑ የጀግንነት ተምሳሌት ናቸውም ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከከፍታ ማማዋ መውረድ የጀመረችው
ጀግኖቿ ሲንቋሸሹ፣ ደምና አጥንታቸውን ለከፈሉላት ስደት ሲዘጋጅ ነው ያሉት ዶክተር ፈንታ ላይቀር ሞት ታሪክ መሥራት
ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡
ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌ ደማቸውን ያለ ስስት የሰጡ የሀገርን ሀብት ያልነኩ ጀግና እንደነበሩም ተናግረዋል፡፡ ቤት ሳይኖራቸው
ሀገራቸውን ቤት አድርገው የኖሩ ታላቅ ሰው ናቸውም ነው ያሉት፡፡ ለሀገርና ለሕዝብ መኖርን፣ የጦር ስልትን፣ የፖለቲካ ጥበብን
ከታላቁ ሰው መማር ይገባልም ነው ያሉት፡፡ ዛሬ ላይ በወሬ እየቆሰለ በየመንደሩ የሚውለው ሰው ብዙ ነው ያሉት ዶክተር ፈንታ
ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌ ግን በሰባት ጥይት ተመትተው በጀግንታቸው የቀጠሉ ኃያል ናቸው ነው ያሉት፡፡
ዘመኑን በመዋጄት ኢትዮጵያ እንደሀገር እንድትቀጥል መሥራት ይገባልም ብለዋል፡፡ ብዙ ጥቁር ሕዝቦች የኢትዮጵያን ነጻነት
አይተው፣ በጨለማ መካከል እንደተሰቀለ መብራት ከሩቅ ተመልክተው፣ ለነጻነታቸው ተዋግተው፣ ዛሬ ነጻ ሕዝቦች ናቸው፣ እኛ ዛሬ
ወደ ባርነት የምንመልስት ባሕሪ ከዬት የተገዛ ነው? በእኛ ተምሳሌት ነጻ የሆኑ ሀገራት በአንድነትና በፍቅር ሀገራቸውን ሲገነቡ እኛ
በመለያዬት ሌሎች ጥለውት ወደመጡት አዘቅት የሚከተንን አባዜ እናስታውልም ብለዋል፡፡
የክልሉ ሕዝብና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ኢትዮጵያን ጠብቆ ማቆዬት አለበት፤ አባቶች በጀግንነት ያቆሟትን ሀገር አሳልፎ
መስጠት አይገባምም ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleየግብጽ ሴራ በዓባይ ላይ …
Next articleየኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን በ22 ሚሊየን ብር ወጪ በኮምቦልቻ ከተማ ያስገነባዉ የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ማማ ተመረቀ፡፡