
“ሀገር ጀግና ወልዳለች ከሚባሉት ውስጥ ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌ መለሰ አንዱ ናቸው” የትግል ጓደኞቻቸው
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 07/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የጀግናው ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌ መለሰ አስከሬን ሽኝት በባሕር ዳር እየተካሄደ
ነው። በፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ቤተ ክርስትያን ሥርዓተ ፍትሐት ተደርጎላቸዋል፡፡
በብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌ መለሰ አስከሬን ሽኝት የተገኙት የትግል ጓዶቻቸው ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ጀግኖች መካከል አንደኛው
ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌ መለሰ ናቸው ብለዋል።
የቀድሞ የትግል አጋር ኮሎኔል መሠረት ገላው ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌ ሀገራቸውን የሚወዱ፣ ሽንፈት የማይቀበሉ ልበ ሙሉ
ጀግና ናቸው ብለዋቸዋል። ብርጋዴር ጄኔራሉ ሁልጊዜም ለትልቅነት ራሳቸውን የሚያዘጋጁ ታላቅ የጦር መሪ እንደነበሩም
ተናግረዋል። ስልጣን የማይፈልጉ፣ ብርቱና ለሀገር ራሳቸውን አሳልፈው የሚሰጡ እንደነበሩም ነው የተናገሩት።
“ሀገር ጀግና ወልዳለች ከሚባሉት ከሚባሉት ውስጥ ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌ መለሰ አንዱ ናቸው” ነው ያሉት።
ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌ መለሰ ለጀግንነት የተፈጠሩ ናቸው ያሉት ኮሎኔል መሠረት በሶማሊያ ወረራ ጊዜ ጀብዱ የፈፀሙና
ለፈፀሙት ገደል ሽልማት የተበረከተላቸው ናቸውም ብለዋል።
ጀነራሉ አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀውን ሕወሓት ቡድን ለመጣል ለተነሳው ትግል አርዓያ ናቸውም ነው ያሉት። ቡድኑ ሀገር ለመበተን፣
ለዘረፋና ለውንብድና የመጣ መሆኑን አስቀድመው ተረድተው የነበሩ እንደነበሩም ተናግረዋል። የጦር መሪው ለሕወሓት መራሹ
መንግሥት አልገዛም ብለው በጀግንነት የተዋጉ ሰው እንደነበሩም ነው ያመላከቱት።
በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅ የነበሩት ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌ መለሰ አሸባሪው ሕወሓት ሊይዛቸው ያደገው ጥረት ሳይሳከለት
መቅረቱንም አስታውሰዋል። ከሀገር ወጥተውም ራሳቸውን መደብቅ ሳይሆን ትግል መጀመራቸው ጥንካሬያቸውን የሚያሳይ
መሆኑንም ገልጸዋል።
የአሁኑ ትውልድም እንደ ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌ ኹሉ ኃላፊነት መወጣትን፣ በዓላማ መፅናትን፣ የታሪክ ሰው ለመሆን ራስን
ማዘጋጄትን መውረስ አለበት ነው ያሉት።
ለሀገራቸው የነበራቸው ፍቅር በትውልዱ መቀጠል አለበትም ብለዋል። ጀግኖች ሩህሩህ ናቸው ያሉት ኮሎኔሉ እሳቸውም
ሩህሩህና ታማኝ ነበሩ ብለዋቸዋል።
ሌላኛው ጓደኛ ኮሎኔል ዓለሙ መብራት “ጄኔራሉን ስገልፅ ኢትዮጵያን ነው የምገልፀው” ነው ያሉት። ለቤተሰቦቻቸው
የኢትዮጵያዊነትን ካባ የደረቡ ናቸው ብለዋል። ሲሠሩም በኢትዮጵያዊነት መርህ ነው ብለዋል። ጥንቁቅና በሀገራቸው ጉዳይ
የማይደራደሩ ነበሩም ብለዋቸዋል። ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ሲነገሩ ያደጉ፣ ስለ ኢትዮጵያ የኖሩ ናቸውም ነው ያሏቸው።
ጀግና የጦር ሰው ጀብዱ ፈፃሚ፣ ኢትዮጵያን የሚወዱ ሕዝብን የሚያከብሩ እንደነበሩም ነው የተናገሩት። ሩቅ አሳቢ ለሀገር
ሕይወትን የሚሰጡ እንደነበሩም ገልጸዋል።
“ሕወሓት ልቡን የሚሰብር ነገር ሲያስታውስ ቀድመው የሚመጡት ጀግናው ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌ ናቸው” ያሉት ኮሎኔል
ዓለሙ በጉና ተራራ ላይ የነበራቸውን ተጋድሎ አስታውሰዋል።
የጄኔራል ኃይሌ ሀብት ኢትዮጵያ ብቻ ናት ሌላ ሀብት የላቸውምም ብለዋል። በጨዋ ደንብ ያደጉ ሩህሩህ ሰው ነበሩም ነው
ያሉት። ስለ ሀገራቸው የትኛውንም መስዋዕት መክፈል የሚሹ ሰው እንደነበሩም ተናግረዋል። ለሕዝብ ታማኝ እንደነበሩም
ተናግረዋል።
ወጣቱ መንፈሰ ጠንካራነት፣ ትግዕስት፣ የዓላማ ፅናት፣ በብዙኃኑን መወደድና ሀገርን መውደድ ከእሳቸው መማር አለበትም
ብለዋል።
ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌ መለስ ባደረባቸው ህመም በህክምና ሲረዱ ቆይተው ግንቦት 3/ 2013 ዓ. ም ነው ህይወታቸው
ያለፈው።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m