የኮሮናቫይረስ ስርጭት ለመግታት ሁሉን አቀፍ ምላሽ ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

124

የኮሮናቫይረስ ስርጭት ለመግታት ሁሉን አቀፍ ምላሽ ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

ባሕር ዳር: ግንቦት 06/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ዳግም ትኩረት ለኮሮናቫይረስ ንቅናቄ ሀገር አቀፍ የማስጀመሪያ መርኃ ግብር ላይ እንደተናገሩት አሁን ያለውን የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ሁሉን አቀፍ ምላሽ ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከብሔራዊ የኮሮናቫይረስ ግብረኃይል፣ ከክልል ርእሰ መሥተዳደሮች እና ከተለያዩ ሴክተር መሥርያ ቤቶች የተገኙ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በበየነ መረብ ውይይት አድርገዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀገር አቀፍና በክልል ደረጃ ለሁለት ወራት የሚቆይና ዝርዝር ተግባራትን ያካተተ እንዲሁም ሁሉን አቀፍ ምላሽን ማጠናከር የሚያስችል ዳግም ትኩረት ለኮሮናቫይረስ በሚል ሀገር አቀፍ ንቅናቄ አስጀምረዋል፡፡

አሁን ያለውን የኮሮናቫይረስ የስርጭት ሁኔታ እየተገበርነው ባለው የምላሽ አካሄድ መፍታት ስለማይቻል ምላሹን ከጤና ሴክተር ባለፈ ሁሉን አቀፍ ምላሽን ማጠናከር፣ የአመራርና የኅብረተሰቡን ትኩረትና ተሳትፎ ማሻሻል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወቅታዊዉን ዓለምአቀፍና ሀገር አቀፍ የኮሮናቫይረስ ሁኔታን ከግንዛቤ ዉስጥ በማስገባት በየደረጃዉ ያለዉ አመራርና የሚመለከተዉ አካላት ሁሉ ለንቅናቄዉ ስኬት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በቅንጅት ኅብረተሰቡን በማሳተፍ መሥራት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

የመገናኛ ብዙኃን፣ የኮምዩኒኬሽን ባለሙያዎች የኪነጥበብ ሰዎች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ኅብረተሰቡን ማንቃትና ቫይረሱ እያስከተለ ያለዉን ጉዳት ማሳወቅ ላይ በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመመሪያ ቁጥር 30 የተቀመጡ ክልከላዎችን ተከታትሎ ማስፈጸምና የተቀመጡ ስታንዳርዶችን ሳያሟሉ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ላይ አስፈላጊዉ እርምጃ መዉሰድ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ለሁለት ወራት የሚቆየውን ዳግም ትኩረት ለኮሮናቫይረስ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ ዝርዝር እቅድ አቅርበዋል።

አሁን ላይ ያለዉ የቫይረሱ ስርጭት እጅግ አሳሳቢ መሆኑን ገልጸዋል።

የቫይረሱን ስርጭት መቀልበስና የሞት መጠንን መቀነስ ፣ የዘርፈ ብዙ ምላሽን ማጠናከር ፣ የኮሮናቫይረስ ጽኑ ህክምና ተደራሽነት ማሳደግ፣ የተቀናጀ የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የሕግ ማስከበር ንቅናቄዎችን ማከናወን፣ የምርመራ አቅምና የክትባት ሽፋንን ማሳደግ ላይ ትኩረት በመስጠት ይሠራል ነው ያሉት፡፡

በንቅናቄዉም የቤት ለቤት ዳሰሳ ሥራ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል አጠቃቀም ተግባራዊ ማድረግ፣ አካላዊ ርቀት አተገባበርን መከታተል፣ ዕለታዊ አማካይ የመመርመር አቅምን ከፍ ማድረግ በትኩረት እንደሚሠራ ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

የሁለት ወር ንቅናቄው ውጤት ተገምግሞ አስፈላጊዉን ማሻሻያ በማድረግ ምላሹ የሚቀጥል መሆኑን እንደገለጹ ከጤና ሚኒስቴር የማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous article“ኢትዮጵያ በውጪ ኀይሎች መልካም ፈቃድ አትመራም” የሰላም ሚኒስቴር
Next article“ሀገር ጀግና ወልዳለች ከሚባሉት ውስጥ ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌ መለሰ አንዱ ናቸው” የትግል ጓደኞቻቸው