የኢትዮ-ቻይና ዲፖሎማሲያዊ ግንኙነትን ለማጠናከር ሀገራቱ በጋራ እንደሚሠሩ አስታወቁ።

71
የኢትዮ-ቻይና ዲፖሎማሲያዊ ግንኙነትን ለማጠናከር ሀገራቱ በጋራ እንደሚሠሩ አስታወቁ።
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 06/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገራቱን 50ኛ ዓመት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አስመልክቶ የቴምብር ምረቃ እየተካሄደ ነዉ። የኢትዮጵያ ፖስታ ድርጅት ዳይሬክተር ሐና አርዓያ ኢትዮጵያ እና ቻይና የጠነከረ ግንኙነት እንዳላቸዉ ገልጸዋል፡፡ በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን በተመለከተ የሁለትዮሽ ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ከማጠናከር ጀምሮ በርካታ ሥራዎችን ማከናወኑንም አስረድተዋል። 50ኛ ዓመቱን አስመልክቶም የቴምብር ምረቃ ሥነ ሥርዓት እየተከናወነ ነው።
በቴምብሩ ላይ የቻይና አሻራ ያረፈበት የሸገር ፓርክ እና የቤጅንግ ኦሎምፒክ ምስልም ተካቶበታል። በቻይና ኢምባሲ የሚኒስተር አማካሪ የሆኑት ዣ ቲያን የኢትዮጵያ እና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለዓመታት የቆየ እና የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሀገራቱ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከላከልን ጨምሮ በሌሎች ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ሲሠሩ ቆይተዋል ሲሉም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ያዘጋጀዉ ቴምብር የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የሚያሳይ መሆኑንም አመላክተዋል። በዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኤስያ እና በፓስፊክ አካባቢ ዳይሬክተር ጄነራል ሞላልኝ አስፋዉ ሁለቱም ሀገራት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በጋራ የሠሩት ሥራ የሚበረታታ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ለኮሮናቫይረስ ክትባት ቻይና ለኢትዮጵያ ድጋፍ እያደረገች መሆኗም የሚያስመሰግን ነዉ ብለዋል። ዳይሬክተር ጄነራል ሞላልኝ ምስጋና ለቴምብር ምርቃቱ መሳካት የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅትን እና የቻይና ኢምባሲን አመስግነዋል።
ዘጋቢ፡- ኤልሳ ጉዕሽ -ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የድምፅ መስጫ ወረቀት የሕትመት ሂደትንና የደኅንነት አጠባበቅ ሥርዓቱን ለፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች አስጎበኘ፡፡
Next articleለመምረጥ የሚችሉ ዜጎች ሊጠናቀቅ ሰዓታት በቀረው የመራጮች ምዝገባ ጊዜያቸውን በመጠቀም የምርጫ ካርድ እንዲወስዱ መራጮች ጥሪ አቀረቡ፡፡