የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የድምፅ መስጫ ወረቀት የሕትመት ሂደትንና የደኅንነት አጠባበቅ ሥርዓቱን ለፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች አስጎበኘ፡፡

247
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የድምፅ መስጫ ወረቀት የሕትመት ሂደትንና የደኅንነት አጠባበቅ ሥርዓቱን ለፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች አስጎበኘ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 06/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፓለቲካ ፓርቲዎች እና የመገናኛ ብዙኃን የተወጣጣ የልዑካን ቡድን ወደ ደቡብ አፍሪካ በመላክ የድምጽ መስጫ ወረቀት ሕትመትን እንዲጎበኙ አደረገ።
በቦርዱ ከፍተኛ አመራር ፍቅሬ ገብረ ሕይወት ለተመሩት ከፓርቲዎች እና ከመገናኛ ብዙኃን ለተውጣጡ ተወካዮች የድምፅ መስጫ ወረቀት የሕትመት ሂደቱን፣ የቴክኒክና የደኅንነት አጠባበቅ ሥርዓቱን በዝርዝር ማሳየት ችሏል።
ቦርዱ የፍትሐዊ አሠራሩ አንዱ ማሳያ አድርጎ ከሚወስደው የድምፅ መስጫ ወረቀት የዕጩዎች አደራደር ቀደም ተከተል መወሠኛ ሎተሪን በይፋ ካስጀመረበት ከመጋቢት 25/2013 ዓ.ም. ጀምሮ የድምፅ መስጫ ወረቀት ሕትመቱ ተጀምሯል፡፡ የድምፅ መስጫ ወረቀት ሕትመት ሥራ ከሚያካሂዱት ሁለት የሕትመት ድርጅቶች አንዱ በሆነውና በደቡብ አፍሪካ የሚገኘውን የሬን-ፎርም ሕትመት ማኅበር ከፓርቲዎች እና ከመገናኛ ብዙኃን የተወጣጡ የታዛቢ ቡድኑ አባላት ጎብኝተውታል።
በጉብኝቱም የሥራ ሂደትና የሕትመቱ የደኅንነት አጠባበቁን ምን እንደሚመስል በሕትመት ኩባንያው የሥራ ኃላፊዎች ገለጻ ተሰጥቷል።
የሕትመት ሂደቱ ምን እንደሚመስል፣ ከጥሬ ቁሳቁስ ምርት አንስቶ እስከ ሕትመት ሂደቱና የማሸግ ሥርዓቱ ድረስ ያለውን አጠቃላይ ሂደት የተመለከተ ጉብኝት ተካሂዷል።
ፓርቲዎቹም ከጉብኝቱ በኋላ ለብዙኃን መገናኛ አካላት በሰጡት አስተያየት፤ ባዩት ነገር መደሰታቸውንና ጉብኝቱም የቦርዱን ግልጽ አሠራር ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የጉብኝት አጋጣሚውም ፓርቲዎቹ ተቀራርበው ለመወያየት አጋጣሚን የፈጠረ እንደነበር ጠቁመዋል።
የድምፅ መስጫ ወረቀት ሕትመት ሥራ ከሚያካሂዱት አንዱ የሆነው በደቡብ አፍሪካ የሚገኘውን የሬን-ፎርም ሕትመት ማኅበር የድምፅ መስጫ ወረቀት ሕትመቱን 45 በመቶ የሚሸፍን ሲሆን ይኸውም የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል፣ የአማራ ክልል፣ የሲዳማ ክልልና የደቡብ ምዕራብ ሕዝቦች ሕዝበ ውሣኔን ያካትታል።
ቀሪውና 55 በመቶ የሚሸፍነው የሕትመት ሥራ ዱባይ በሚገኘው አል-ጉህራር ማኅበር እየተከናወነ ይገኛል። ለአራት ቀናት በቆየው ጉብኝትም የብልጽግና ፓርቲ፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ የህብር ኢትዮጵያ ተወካይ (ህብር)፣ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) እንዲሁም የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡
የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ እና የመገናኛ ብዙኃን አካላት በጉብኝቱ መሳተፋቸውን ከቦርዱ የማኅበራዊ ትስስር የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleኢትዮጵያ ፈተናዎችን በመቋቋም እየሄደችበት ያለው የሰላም መንገድ ተመራጭ መሆኑን ምሁራን ተናገሩ፡፡
Next articleየኢትዮ-ቻይና ዲፖሎማሲያዊ ግንኙነትን ለማጠናከር ሀገራቱ በጋራ እንደሚሠሩ አስታወቁ።