ሼህ ሰኢድ መሀመድ የኢድ አልፈጥር በዓልን ምክንያት በማድርግ በፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተገኝተው ሕሙማንን ጠየቁ፡፡

177

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 05/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የተቋቋመው ፈውስ በጎ አድራጎት ማኀበርና የባሕር ዳር ከተማ ሙስሊም ወጣቶች የኢድ አልፈጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ ከህሙማን ጋር ለማሳለፍ በአዘጋጁት መርሃ ግብር ላይ የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሰኢድ መሀመድ ተገኝተው ህሙማንንና አስታማሚዎችን ጠይቀዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ሼህ ሰኢድ ‹‹ከስጋዊ ሕክምና በተጨማሪ መንፈሳዊ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ስላሉ የሃይማኖት አባቶች ሆስፒታል ተገኝተን ሕሙማንን ጠይቀና›› ብለዋል፡፡ ሕሙማንም በእንደዚህ ዓይነት በዓላት በሃይማት አባቶች ሲጠየቁ መንፈሳዊ ደስታን ይጎናፃፋሉ ተብሎ በቅዱስ ቁራን እንደተገለጸ ጠቁመዋል፡፡ ህሙማንም ፈውስን እንዲያገኙ እንደሚጸልዩላቸው ነው የገለጹት፡፡ ፕሬዝዳንት ሼህ ሰኢድ ቅዱስ ቁራን የሚያዘውን ለመፈጸም በዓሉን ከሕሙማን ጋር ማሳለፋቸውን ነው የገለጹት፡፡

ህሙማንን የመጠየቅ ተግባር በዓላትን ብቻ በመጠበቅ ሊኾን እንደማይገባም ተናግረዋል፡፡ በተለይም ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች በርሃብና በውኃ ጥም እንዳይጎዱ ሁሉም ዜጋ ሊተባበር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቀዶ ህክምና ስፔሻሊስትና የፈውስ በጎ አድራጎት ማኅበር ሰብሳቢ መልካሙ ባየ (ዶክተር) የፈውስ በጎ አድራጎት ማኅበር በኢኮኖሚ፣ በማኀበራዊና በሥነ ልቦና ምክንያት የሚጎዱ ህሙማንና አስታማሚዎችን ለማገዝ የተቋቋመ በጎ አድራጎት ማኅበር መኾኑን ተናግረዋል፡፡

የማኅበሩ አባላትም በየወሩ 10 ብር በቋሚነት በማውጣት የተቸገሩ ዜጎችን እያገዙ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ የኢድ አልፈጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ ከባሕር ዳር ከተማ ሙስሊም ወጣቶች ጋር በመተባበር በዓልን በሆስፒታል የሚገኙ ህሙማን ተደስተው እንዲውሉ የቴምር፣ የውሃ፣ የለስላሳ መጠቶችና ሌሎች ድጋፎች ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

እንደዚህ ዓይነት መርሃ ግብር በትንሣኤ በዓልም ተዘጋጅቶ እንደነበረ አስረድተዋል፡፡ በዛሬው መርሃ ግብር ከ600 በላይ ለሚኾኑ ህሙማንና አስታማሚዎች ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

የባሕር ዳር ሙስሊም ወጣቶች አባል ወጣት ሰይድ አደም እንደገለጸው የመርሃ ግብሩ ዓላማ በእስልምና ሃይማኖት አስተምሮ በዓሉን ከተቸገሩ ዜጎች ጋር መዋል ፅድቅን ያስገኛል ተብሎ ስለሚታመንና አብሮነት አንዱ መገለጫ በመኾኑ መዘጋጀቱን ተናግሯል፡፡

ወጣት ሰይድ ህሙማን ከሰዎች ጋር ሲውሉ ሃሳብ ይለዋወጣሉ፣ ይጫወታሉ፣ ከአልጋ በመነሳት ለሌላ ተስፋ እንዲዘጋጁም ያግዛቸዋል ብሏል፡፡

በዛሬው ቀንም ከ51 ሺህ ብር በላይ ወጪ በማድረግ ለህሙማን እና አስታማሚዎች ግብዣ መደረጉን ተናግሯል፡፡ ‹‹እስልምና ለተቸገሩ የሰው ልጆች እዘኑ ይላል›› ያለው ወጣቱ በሆሰፒታሉ በመገኘትም ሙስሊም፣ ክርስቲያን ሳይባል ለሁሉም ታማሚዎች ግብዣ መደረጉን አስረድቷል፡፡

የሆስፒታሉ ሠራተኞችም ቤት መዋል እየቻሉ ከታማሚዎች ጋር በዓሉን ሲያሳልፉ ማየት ለሌላ በጎ ዓላማ ያነሳሳል ብሏል ወጣት ሰይድ፡፡

በሆስፒታሉ ህሙማንን እያስታመመች ያገኘናት ወጣት ሃያት አብዲ እንደገለጸችው የሃይማኖት አባቶች ከቤታቸው በዓል ማሳለፍ እየቻሉ ከህሙማን ጋር ማሳለፋቸው እንዳስደሰታት ተናግራለች፡፡
በተለይም ከዚህ በፊት እንደዚህ ዓይነት ትልቅ በዓል ሲኾን በሆስፒታል አሳልፋ እንደማታውቅ የተናገረችው ወጣት ሃያት ትልልቅ የሃይማኖት አባቶች ሆስፒታል በመገኘት ታማሚዎችንና አስታማማዎችን መጠየቃቸው ከቤታቸው እንዳሉ እንዲሰማቸው ያደርጋል ነው ያለችው።

ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous article“የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ “ሐቅ” መሆኑን ለዓለም ማኅበረሰብ እናስረዳለን” የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች
Next articleምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ መኾናቸውን በደቡብ ጎንደር ዞን የስማዳ ወረዳ የብልጽግና ፓርቲ ደጋፊዎች ተናገሩ፡፡