“የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ “ሐቅ” መሆኑን ለዓለም ማኅበረሰብ እናስረዳለን” የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች

170

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 05/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ ከሚያደርጉት ድጋፍ ባሻገር ግድቡ የኢትዮጵያ ሐቅና መብት መሆኑን ለዓለም ማኅበረሰብ እንደሚያስረዱ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ገለጹ።

1 ሺህ 442ኛው የኢድ አልፈጥር በዓልን በአዲስ አበባ ያከበሩ የሃይማኖቱ ተከታዮች ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁሉንም ኢትዮጵያውያንን አንድ የሚያደርግ ነው ይላሉ።

አስተያየት ሰጪዎቹ አሁን አሁን ግድቡን መነሻ በማድረግ ኢትዮጵያ ላይ ጫናዎች እየበረቱ መሆኑንም ጠቅሰዋል። ከዚህም ከዚያም የሚነሱ የሀገር ጠላቶችን ማሳፈር የሚቻለው ለግድቡ ግንባታ የሚደረገውን አስተዋጽኦ በማጠናከር እንደሆነም ተናግረዋል።

ወጣት አብዱራዛቅ አብደላ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ለግድቡ ግንባታ ከምናደርገው ድጋፍ ባሻገር የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ “ሐቅ” መሆኑን ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ለዓለም ሕዝብ መናገር አለብን ነው ያለው።

ለግድቡ የሚያስፈልገውን ድጋፍ ለማድረግ ሕዝበ ሙስሊሙ ከመንግሥት ጎን እንደሚቆም እምነት አለኝ ያሉት ደግሞ ሼህ ዓሊ ሙሃመድ ናቸው።

ሙስሊሙም ይሁን ክርስቲያኑ ሁሉም ያለ ልዩነት “ከሁሉም በላይ ግድቡ የእኛ የኢትዮጵያዊያን እንጂ የማንም አለመሆኑን አውቀን የራሳችንን ሃብት የመጠቀም መብታችንን ማረጋገጥ አለብን” ብለዋል።

የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያዊያን ከድህነት መውጫ መንገዳቸው መሆኑን አውቀው ሊተባበሩ እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ አቶ መሐመድ ሁሴን ናቸው።

ኢትዮጵያዊያን በስደት የሚሰቃዩበት ድህነት እንዲወገድ በውስጥም በውጪም ያለው ሙስሊም ማኅበረሰብ መተባበር አለበት ነው ያሉት።

ወጣት ኢብራሂም ከድር በበኩሉ የሀገር ጠላት ካልሆነ በቀር ማንም በግድቡ ጉዳይ አይደራደርም ብሏል። የሕዳሴ ግድብ የአሁኑን ትውልድ የኤሌክትሪክ ፍላጎት የሚያሟላና ለመጪውም ትውልድ የሚተላለፍ ሃብት በመሆኑ ይህን ጠቃሚ የልማት ውጥን ከግብ እንዲደርስ መሥራት እንደሚገባ መገለጹን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleበአጣዬና አካባቢዉ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም የሚደረገዉ ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር አስታወቀ፡፡
Next articleሼህ ሰኢድ መሀመድ የኢድ አልፈጥር በዓልን ምክንያት በማድርግ በፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተገኝተው ሕሙማንን ጠየቁ፡፡