
ኢድ አልፈጥር በዓል አከባበር በተለያዩ የዓለም ሀገራት
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 05/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ኢድ አልፈጥር የቅዱሱ ረመዳን ወር ፆም መፍቻ በዓል ነው፡፡ በዓሉ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የዓለም ሀገራት በሃይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ እየተከበረ ነው፡፡ የተወሰኑትን ሀገራት የኢድ አልፈጥር በዓል አከባበር እንመልከት፡፡ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ኢድ አልፈጥርን በአደባባይ እና በዋና በዋና ጎዳናዎች በፆሎት እና በስግደት ያከብራሉ፡፡
በኢድ አልፈጥር በሥራ እና በልዩ ልዩ ምክንያቶች የተለያዩ ቤተ ዘመዶች ተሰባስበው በዓሉን በጋራ ያከብራሉ፡፡ በኢድ አልፈጥር አንድም ሙስሊም አጥቶ እና ከፍቶት እንዳይውል ጥረት ይደረጋል፡፡ የአፍጣር መርኃግብሮች የሚከናወንባቸው አደባባዮች የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዝግጅቱ የሚካሄድበት ሲያጸዱ ማስተዋል የተለመደ ነው፡፡
እንኳን አደረሳችሁ መባባል፣ ስጦታዎችን መለዋወጥ እና እንግዶችን ጠርቶ በቤት ውስጥ መጋበዝ የኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች የኢድ አልፈጥር አከባበር መለያዎች ናቸው፡፡
አፍሪካዊቷ ሀገር ሞሮኮ እስልምናን ቀድመው ከተቀበሉ የዓለም ሀገራት መካከል አንዷ ነች፡፡ በሞሮኮ በኢድ አልፈጥር በዓል ጠዋት ላይ ወንዶች ከመስጅድ ሲመለሱ ሴቶች ያዘጋጁትን “ባንጋህሪር” እና “መልዊ” የተባሉ ባህላዊ ምግቦችን ቁርስ ላይ እየቀማመሱ ሀሴት ማድረግን ይጀምራሉ፡፡ ወዳጅ ዘመድ ይጠይቃሉ፣ ድሆችን ይጎበኛሉ፣ በሆስፒታል እና በሕግ ጥላ ስር ያሉ ወገኖችም በቀኑ እንኳን አደረሳችሁ ይባላሉ፡፡ በበዓሉ እንደ አብዛኛዉ የዓለም ሀገራት ስጦታ መለዋወጥ በሞሮኮ የተለመደ አይደለም፡፡
ቱኒዝያዊያን የኢድ አልፈጥር በዓልን “ኢዱል ፊትሪን” ሲሉ ይጠሩታል፡፡ የሀገሪቱን ሕዝብ 98 በመቶ የሚሸፍኑት የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ኢድ አልፈጥርን በልዩ ሁኔታ ያከብሩታል፡፡ “ካክ” የተሰኘ የኬክ ዓይነት እና “ባክላዋ” የሚባል ልዩ ብስኩት የኢድ አልፈጥር በዓል ልዩ እና ተወዳጅ ምግቦች ናቸው ለቱኒዚያዊያን፡፡
በሀገረ ሕንድ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላቸው የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ናቸው፡፡ ሕንዳዊያን ሙስሊሞች የኢድ አልፈጥር በዓልን ለማክበር ከቤታቸው ወጥተው በአደባባይ ተሰባስበው በጋራ ለአላህ ምስጋና ያቀርባሉ፡፡ ወደ አደባባይ ለሶላት ከመውጣታቸው በፊት ግን ‹‹ሽር ኩመራ›› የተሰኘ ምግብ ከጣፈጭ ነገሮች እና ከሩዝ ከበዓሉ በፊት ባለው ምሽት ይዘጋጃል፡፡ በኢድ አልፈጥር ጠዋት ይህን ምግብ ተሰባስበው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ይቀምሳሉ፡፡ ሕንዳዊያን ሙስሊም ሴቶች እጆቻቸውን እና እግሮቻቸውን በሂና በማስዋብ በባህላዊ አልባሳት ደምቀው ያሳልፋሉ፡፡ በኢድ አልፈጥር ስጦታዎችን መለዋወጥ እና የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ለወዳጅ ዘመድ ማስተላለፍ ለሕንዳዊያን ሙስሊሞች የተለመደ ነው፡፡
በቱርክ ኢድ አልፈጥርን “ራመዳን ባይራም” ይሉታል፡፡ ቱርካዊያን ሙስሊሞች በኢድ አልፈጥር በዓል ወደ መቃብር ቦታዎች በመሄድ ከዚህ ዓለም ያለፉትን ሰዎች የእረፍት ቦታ በአበባ በማስጌጥ እና በፆሎት ያስባሉ፡፡ ሕፃናት ወደ ጎረቤቶቻቸዉ በመሄድ እንኳን አደረሳችሁ ይላሉ፡፡ ጣፋጭ ነገሮችን እና ገንዘብም ይቀበላሉ፡፡
የዘንድሮው የኢድ አልፈጥር በዓል ታዲያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የኮሮናቫይረስ ስርጭት ተከትሎ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል በማድረግ በአደባባይ የሚደረገው ሦላት እና ስግደት የተወሰነ ቁጥር ባላቸው ተከታዮች ብቻ እንዲከበር አድርጓል፡፡ ኢንዶኔዥያ ኢድ አልፈጥርን ምክንያት በማድረግ ከፓኪስታን ወደ ሀገሪቱ የሚደረግን ጉዞ ላልተወሰነ ጊዜ ከልክላለች፡፡
በተጨማሪም ማሌዥያና ፓኪስታንን ጨምሮ በርካታ የመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢዎች በአደባባይ የሚከበረውን የኢድ አልፈጥር አከባበር በውስን ሰዎች ብቻ እንዲካሄድ እና ከቤት ውጭ የእንቅስቃሴ እገዳ እስከ ግንቦት 17 ቀን 2021 (እ.አ.አ) ድረስ መጣሉ ተዘግቧል፡፡
ሮይተርስ፣ ቢቢሲ እና አልጀዚራን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል
ኢድ ሙባረክ!
በታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ