
የኢድ በዓልን በአብሮነት እያሳለፉ እንደሆነ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ የእስልምና እና የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ተናገሩ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 05/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በአብሮነት ዘመናትን የዘለቁ የእስልምና እና የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዛሬም እንደ ጥንቱ ኢድ አልፈጥርን በጋራ እያሳለፉ ነው፡፡ አሚኮ ያነጋገራቸው በባሕር ዳር የሚኖሩ የሁለቱ የሃይማኖት ተከታዮች ኢድ አልፈጥርን በጋራ እያሳለፉ እንደሆነ ነው የጠቀሱት፡፡
እንድሪስ ሙሐመድ የኢድ አል ፈጥር በዓልን በመተዛዘንና በመተጋገዝ እያሳለፍት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የረመዳን ወርን ሁሉ የታመሙትን በመጠየቅና የተቸገሩትን በመርዳት እንዳሳለፉት ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ የሠላም መደፍረሶች እንዲወገዱ አጥብቀው እንደሚጸልዩም አቶ እንድሪስ ተናግረዋል፡፡ በእስልምና ሃይማኖት የሚከበሩ ታላላቅ በዓላት ወቅት ከክርስትና ሃይማኖት ተከታይ ጓደኞቻቸውና ጎረቤቶቻቸው ጋር በጋራ እንደሚያሳልፉም አስታውሰዋል፡፡
በ1 ሺህ 442ኛውን የኢድ አልፈጥር በዓልም ከክርስቲያን ወገኖቻቸው ጋር በጋራ እያከበሩ እንደሆነ ነው አቶ እንድሪስ የነገሩን፡፡ “ሰው መዋደድ እንጂ ያለበት ጥላቻ የትም አያደርሰንም፤ ከጠብ ይልቅ ፍቅር ነው የሚበልጠው” ብለዋል፡፡
ኢሳ አማን የተባሉ ነዋሪ ደግሞ በዓሉን በየዓመቱ እንደሚያደርጉት ሁሉ ዘንድሮም በአብሮነት እያከበሩት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የእስልምናም ሆነ የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች በየበዓላቶቻቸው በመጠራራት በጋራ ያከብራሉ ያሉት አቶ ኢሳ ይህ አብሮነት እሴት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው ያሉት፡፡
አቶ አብዱልቃድር አብዲ የተባሉ ነዋሪ ወደ ሶላት ሲሄዱ ነበር ያገኘናቸው፡፡ አቶ አብዱልቃድር እንደነገሩን የእስልምናና የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች በዓላት የጋራ በመሆናቸው አብረው ነው የሚያሳልፉት፡፡
አቶ ሶፋው መሐመድ አላህ ከፈቀደ የዘንድሮውን የኢድ አልፈጥር በዓል አቅማቸው በቻለው ሁሉ ሃይማኖት ሳይለዩ ተጠራርተው፣ በመጨዋዎት በጋራ እንደሚያከብሩም ተናግረዋል፡፡
በሀገሪቱ የሚታየው የሠላም እጦት ተስተካክሎ በሰላም ለመኖር ሁሉም በየዘርፉ ሊተጋ እንደሚገባ አቶ ሶፋው መልእክታቸዉን አስተላልፈዋል፡፡
ወይዘሮ ተስፋነሽ እንደሻው የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ ናቸው። ከሙስሊም ወገኖቻቸው ጋር በዓሉን እያሳለፉ እንደሆነ ተናግረዋል። የቆየ አብሮነታቸውን የበለጠ ለማጠናከር ዛሬም ከሙስሊም ጓደኞቻቸው ጋር እያሳለፈ እንደሚገኙ ነው የተናገሩት።
“ከሙስሊም ጓደኞቼ ጋር ሆኜ በዓሉን በጋር እያሳለፍን ነው” ብለዋል። ለመላው የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች መልካም በዓል እንዲሆንላቸውም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡- ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ