“በወርሃ ሻዕባን ፍፃሜ ተብሲር ኢድ አልፈጥር ይባባላሉ”

302
“በወርሃ ሻዕባን ፍፃሜ ተብሲር ኢድ አልፈጥር ይባባላሉ”
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 05 /2013 ዓ.ም (አሚኮ) ኢስላም ውስጥ ታላቅ ክብር ከሚሰጣቸው ወራት መካከል አንዱ ነው፡፡ በኢስላማዊያን ዘንድ የዓመቱ መልካም ሥራዎች ወደ አላህ የሚደርሱበት ወር ተደርጎም ይወሰዳል፡፡ የረመዳን ወር ሙሉ በጾም እና መልካም ሥራዎች ያልፋል፡፡ ፆም እና ሶላት፤ ምፅዋት እና እዝነት የሻዕባን ወር መለያዎች ናቸው፡፡
በእስላማዊ የዘመን አቆጣጠር ሒጅራ መሠረት ሙስሊሞች የረመዳን ፍቺ፣ የወርሃ ሻዕባን ፍፃሜ የመጀመሪያዋን ቀን “ኢድ አልፈጥር” ወይም “መልካም የፆም ፍቺ” በመባባል ያሳልፋሉ፡፡ የኢስላም መሰረቶቹ አምስት ናቸው፡፡ የአላህን ብቸኛ አምላክነት እና የሙሐመድን መልዕክተኛነት በልቦና አምኖ በአንደበት መመስከር፣ ሦላትን አስተካክሎ መስገድ፣ ዘካ ማውጣት፣ ሐጅ ማድረግ እና የሮመዳን ጻም ናቸው፡፡
እነዚህን የሃይማኖቱን መሰሶዎች ማንኛውም ኢስላም ሊፈፅማቸው ግድ ይላል ያሉን የሀረሪ ሕዝብ ክልል ባህል፣ ቅርስ እና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኀላፊ አቶ አዩብ አብዱላሂ ናቸው፡፡ “ኢድ አልፈጥር” የቃሉ ቀጥተኛ ትርጓሜ የፆም ፍቺ እና ለድሆች የሚደረግ እዝነትን አስተሳስሮ የያዘ ሃሳብ ነው ያሉን አቶ አዩብ አብዱላሂ በዚሁ ቀን ሦላት ከመሰገዱ በፊት ባለፀጎች ካላቸው ላይ ምንም ለሌላቸው ለማካፈል በነፍስ ወከፍ ያሰባሰቡትን ሁሉ ለድሆች ያደርሳሉ፡፡
በኢድ አልፈጥር ቀን ተቸግሮ፣ ከፍቶት እና አዝኖ የሚውል ኢስላም እንዳይኖር ሁሉም ለሁሉም የቻለውን ያደርጋል ነው ያሉት፡፡ አቶ አዩብ እንደሚሉት ቅዱስ ወር ሮመዳን በሙሉ የእዝነት፣ የመተሳሰብ፣ የሕብረት እና ራስን ለአላህ የማስገዛት ወር ሆኖ ያልፋል፡፡ የዚህ ወር ፍፃሜ እና የፆም ፍቺ በሆነችው ኢድ አልፈጥር የሚደረግ እዝነት ሁሉ ደግሞ የወሩ በጎ ነገር ማሰሪያ ገመድ ተደርጎ ይወሰዳል ይላሉ፡፡
በሮመዳን ወቅት በእስልምና አስተምህሮ ውስጥ ልዩነት ፈጣሪ የሆኑ ክስተቶች ተስተናግደውበታል ያሉት የኢስላማዊ አስተምህሮ ታሪክ ምሁሩ አዩብ አብዱላሂ ከነዚህ መካከል አንዱ የኢስላማዊ አስተምህሮ መመሪያ የሆነው “ቅዱስ ቁርዓን” ከአላህ መውረዱን በዋናነት ያወሳሉ፡፡
የዚህ ቅዱስ ወር ፍፃሜ ማብሰሪያ በሆነችው ኢድ አልፈጥር ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ካለአንዳች ልዩነት በነቂስ ከተለመደው ውጭ የጠዋት ስግደታቸውን ከመስጂዶች ወጥተው በአደባባይ ያከብራሉ፡፡ በዚሁ ቀን ከመስጂድ ወጥቶ በአደባባይ የሚከበረው የጠዋት ስግደት የተለየ ምክንያት ካለው ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት አቶ አዩብ በኢድ አልፈጥር ከመስጂድ ወጥቶ በአደባባይ የሚደረግ ስግደት ዓላማው የኢስላምን ሰላም፣ ትብብር፣ አንድነት፣ ሕብረት፣ መከባበር እና መተሳሰብን ለቀሪው ዓለም በገሃድ ማሳየት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ወደ አደባባይ በጠዋት የሚተሙት የሃይማኖቱ ተከታዮች በልዩ ሕብረ ዝማሬ እና ኢስላማዊ አለባበስ ደምቀው አላህን እያመሰገኑ ያልፋሉ፡፡ ከሶላት ምላሽ ደግሞ በመጡበት ሳይሆን ሌላ መንገድ ፈልገው በመመለስ እዝነትን፣ ምስጋናን እና በጎ ነገርን ሁሉ ለቀሪው ዓለም ያደርሳሉ ነው ያሉት አቶ አዩብ፡፡
በዚህ ዓመት የረመዳን ወቅት ኢትዮጵያዊያን የሃይማኖት ልዩነት ሳያሰናክላቸው የሙስሊም ወንድሞቻቸውን በዓል በተለያዩ ከተሞች በአደባባይ አፍጥር ሲያከብሩ ተስተውሏል ያሉት አቶ አዩብ አብዱላሂ ይህ በጎ ተግባር እና መከባበር የአንድ ወቅት ብቻ ሳይሆን ተጠናክሮ መዝለቅ ይኖርበታል ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያዊያን መካከል በረመዳን ወቅት ያዩት መከባበር እና መደጋገፍ፤ ሕብረት እና አንድነት አልነጃሽ በእንግድነት የተቀበሏቸውን እና ሀረርን የጎበኙትን እነዚያን ጥንታዊ ኢስላሞች ዳግም አስታውሶኛል ብለዋል፡፡ በመጨረሻም አቶ አዩብ አብዱላሂ ለዓለም ኢስላም እና ለኢትዮጵያዊያን ሁሉ እንኳን ለ1 ሺህ 442ኛው የዒድ አልፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበኢስላማዊው ሕግ የተደነገጉና በዒድ ዕለት የሚከናወኑ ተግባራትን በጥቂቱ እናስቃኛችሁ፡፡
Next articleየኢድ በዓልን በአብሮነት እያሳለፉ እንደሆነ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ የእስልምና እና የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ተናገሩ፡፡