በኢስላማዊው ሕግ የተደነገጉና በዒድ ዕለት የሚከናወኑ ተግባራትን በጥቂቱ እናስቃኛችሁ፡፡

175
በኢስላማዊው ሕግ የተደነገጉና በዒድ ዕለት የሚከናወኑ ተግባራትን በጥቂቱ እናስቃኛችሁ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 05 /2013 ዓ.ም (አሚኮ) የዒድ ሠላትን በተመለከተ ኢስላም፣ ሙስሊሞች ከሴቶችና ሕፃናት ጋር በመሆን በአንድነት ወጥተው ሠላት እንዲሰግዱ ያስተምራል፡፡ በጎንደር ከተማ እስልምና ምክርቤት ዋና ጽሕፈት ቤት ምክትል ጸሃፊ ሃጅ እስማኤል አህመድ እንደነገሩን የመስገጃ ጊዜው፣ ፀሐይ ወጥታ የጦር ዘንግ ያክል ከፍ ካለችበት ቅጽበት ጀምሮ ከሰማይ መሐከል እስከምታዘነብልበት ጊዜ ያክል ይሆናል፡፡
እንደ ሃጅ እስማኤል ገለጻ አፈፃፀሙ የዒድ ሠላት ሁለት “ረከዓ” ነው፤ ኢማሙ ሲያሰግድ ቁርኣን የሚያነበው ድምፁን ከፍ አድርጎ ሲሆን ከሠላቱ በኋላም ሁለት “ኹጥባዎችን” ያደርጋል፡፡ በዒድ ሠላት “አላሁ አክበር” የሚለውን ቃል በእያንዳንዱ “ረከዓ” መጀመሪያ ላይ ደጋግሞ ማለት ያስፈልጋል፡፡
በመጀመሪያው “ረከዓ” ላይ “ፋቲሓን” ማንበብ ሳይጀምር፣ ከመጀመሪያው የሠላት መግቢያ “ተክቢራ” ሌላ ስድስት ጊዜ “አላሁ አክበር” ይላል፡፡ በሁለተኛው “ረከዓ” ላይ ደግሞ ከመጨረሻው “ሱጁድ” ሲነሳና ሲቆም ከሚለው ተክቢራ ሌላ አምስት ጊዜ ‹‹አላሁ አክበር›› ይላል፡፡ የጾም ፍች ምጽዋት(ዘካተል ፊጥር) ሌላው ተግባር ነው፤ አላህ (ሱ.ወ) በዒድ ዕለት፣ ቀንና ሌሊቱን ከሚበላው የሚተርፍ ነገር ያለው ሰው አገሬው ከሚመገበው አንድ ቁና ለሙስሊም ድሆችና ችግረኞች እንዲሰጥ ግዴታ ጥሎበታል ይላሉ ሃጅ እስማኤል፡፡ ይህም ድሆችና ችግረኞች በዒድ ዕለት ተቸግረው እንዳይውሉ ያደርጋቸዋል፡፡
የዘካተል ፊጥር መስጫ ጊዜን በተመለከተ የመጨረሻው የረመዳን ቀን ፀሐይ ከጠለቀችበት ሰዓት ጀምሮ፣ የዒድ ሠላት እስከሚሰገድበት ወቅት ድረስ ይሆናል፡፡ ከዒዱ አንድ ወይም ሁለት ሌሊት ቀደም ብሎ መስጠትም ይቻላል፡፡ ዓይነትና መጠኑ ከሀገሬው ምግብ አንድ ቁና ነው፡፡ ቁና የመስፈሪያ ልክ ነው፡፡ ነገር ግን በዘመናዊ የሚዛን ልኬት ሲሰላ በግምት ሁለት ተኩል ኪሎግራም ይሆናል፡፡ ሃጅ እስማኤል እንደነገሩን ማንኛውም ሙስሊም ለራሱ፣ ለሚስቱ፣ ለልጆቹ እንዲሁም ቀለብ ለሚሰፍርላቸውና ለሚያስተዳድራቸው ሰዎች የመክፈል ግዴታ አለበት፡፡
በእናቱ ማህፀን ውስጥ ላለ ፅንስ ማውጣትም ይወደዳል፡፡ ለእያንዳንዱ ሰው ከሀገሬው ምግብ አንድ ቁና ይወጣለታል፡፡ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ይህን ሲደነግጉ፣ ምጽዋቱ፣ ጾመኛው በማላገጥና በመጫወት ምክንያት የሚያገኘውን ወንጀል እንዲያጠፋለትና ለችግረኞች ቀለብ ይሆን ዘንድ ነው፡፡ ከሠላት በፊት ለፈጸመ ሰው ተቀባይነት ያላት ምጽዋት ትሆናለች፡፡ ከሠላት በኋላ ላደረሳት ደግሞ እንደማንኛውም “ሠደቃ”፣ “ሠደቃ” ነች ተብሎ ይወሰዳል ብለዋል ሃጅ እስማኤል፡፡
በተፈቀዱ መንገዶች ሁሉ በመጠቀም፣ በተቻለ መጠን፣ በቤተሰብ ውስጥ፣ ትልቁንም፣ ትንሹንም፣ ወንዱንም፣ ሴቱንም፣ እንዲደሰትና እንዲዝናና ማድረግ በኢስላም የተደነገገ ተግባር ነው፡፡ የሚያምር ልብስ መልበስም እንዲሁ የተወደደ ነው፡፡ በዒድ ቀን መጾም ክልክል ነው፡፡ በዒድ ቀን የሚወደደው፣ በመብላትና በማፍጠር ለአላህ መገዛት እንደሆነም ሃጅ እስማኤል ጠቁመዋል፡፡
በኢድ ዋዜማ ሌሊቱን፣ እንዲሁም ወደ ዒድ ሠላት ሲወጣ፣ “አላሁ አክበር” በማለት አላህን ከፍ ማድረግ ኢስላም የደነገገው ተግባር ነው፡፡ የዒድ አልፊጥር ሠላት ተሰግዶ ሲያበቃ የተክቢራው ጊዜ ይጠናቀቃል፡፡ ይህ የሚደረገው፣ አላህ (ሱ.ወ) ወደ ጾም በመምራት፣ የተባረከውን የረመዳንን ወር ጾም ለማጠናቀቅ ስላበቃቸው፣ ለዋለላቸው ጸጋ እርሱን ለማመስገንና ደስታቸውን ለመግለጽ ነው፡፡
አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡- ‹‹ቁጥሮችንም ልትሞሉ፣ አላህንም ቅኑን መንገድ ስለመራችሁ ታከብሩትና ታመሰግኑት ዘንድ (ይህንን ደነገግንላችሁ)›› (አል በቀራ 185) የተክቢራ አባባል፡ ‹‹አላሁ አክበር፤ አላሁ አክበር፤ ላኢላሃ ኢለላህ፤ አላሁ አክበር፤ አላሁ አክበር፤ ወሊላሂልሐምድ›› የሚል ነው፡፡ እንዲሁም፡ ‹‹አላሁ አክበሩ ከቢራ ወልሐምዱሊላሂ ከሲራ ወሱብሓነላሂ ቡክረተን ወአሲላ›› ይባላል፡፡ ወንዶች፣ ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ፣ ሰዎችን በማይረብሽ ወይም በማያስቸግር መልኩ ተክቢራን መመላለሳቸው የተደነገገ ተግባር ነው፡፡ ሴቶች ግን ድምፃቸውን ዝቅ ማድረግ አለባቸው፡፡
በምስጋናው ብርሃኔ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበኩር ጋዜጣ ግንቦት 02/2013 ዓ.ም ዕትም
Next article“በወርሃ ሻዕባን ፍፃሜ ተብሲር ኢድ አልፈጥር ይባባላሉ”