ማልታ ስደተኞችን ለመቀበል ተስማማች፡፡

210

 

ባሕር ዳር፡ መስከረም 7/2012 ዓ.ም (አብመድ) በጣልያን ባሕር ዳርቻ ጠባቂዎች ሕይወታቸው የተረፉ 90 ስደተኞችን ማልታ ለመቀበል ተስማማች፡፡

በቀጣዩ ሳምንት ደግሞ በአዲስ የስደተኞች መከፋፈያ አሠራር ዘዴ ላይ የአውሮፓ ኅብረት ሊመክር ነው፡፡

የማልታ የሕይወት አድን ትብብር ማዕከል በጠየቀው መሠረት ትናንት የጣልያን ባሕር ዳርቻ ጠባቂ ቡድን ስደተኞቹን ታድጓል፡፡ ከሊቢያ የባሕር ክልል ውጭ እየሰመጠች ከነበረች ጀልባ ነው ስደተኞቹን ማትረፍ የተቻለው፡፡ ማልታ በመጀመሪያ ስደተኞቹን ወደ ሀገሯ ለማስገባት ፈቃደኛ አልሆነችም ነበር፡፡

ማልታ ስደተኞች ደኅንነቱ ወደ ተጠበቀ የወደብ ስፍራ መወሰድ እንዳለባቸው ፅኑ አቋም አላት፡፡ ለመፍትሔነትም የጣልያን ደሴት ላምፔዱሳ እንደ አንድ ቦታ ይጠቆማል፡፡

የአውሮፓ ኅብረት የሀገር ውስጥ ሚኒስትሮች በቀጣዩ ሳምንት በመገናኘት አዲስ የስደተኞች መከፋፈያ አሠራር ዘዴ ላይ የሚመክሩ ይሆናል፡፡

ከዓለማችን የሕዝብ ቁጥር የስደተኞች ቁጥር በፍጥነት እያደገ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ ያሳያል፡፡ በዓለማችን አጠቃላይ የስደተኞች ቁጥር 272 ሚሊዮን ደርሷል፤ ከዚህም ግማሾቹ ስደተኞች ሴቶች ናቸው፡፡ 74 ከመቶ የሚሆኑት ደግሞ መሥራት በሚችሉ የዕድሜ ክልል ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡

የስደተኞችና የጥገኝነት ጠያቂዎች ቁጥር ከአውሮፓውያኑ 2010 – 2017 በ13 ሚሊዮን ጨምሯል፡፡ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት ስደተኞችን በመቀበል ትልቅ ሚና እየተጫወቱ ቢሆንም አሁንም ከምዕራብና ምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት በርካቶች ይሰደዳሉ፡፡ አውሮፓ ከፍተኛውን የስደተኞች ቁጥር ያስተናግዳል፡፡

ምንጭ፡- ሲ ጂ ቲ ኤን

በኪሩቤል ተሾመ

Previous articleበርዕሰ መስተዳድሩ የተመራ የሥራ ኃላፊዎች ልዑክ የስንዴ ኩታ ገጠም ማሳዎችን እየጎበኘ ነው፡፡
Next articleየአከባቢውን ዘመናዊ የግብርና ሽግግር ማነቆዎች ለመፍታት እንደሚሠሩ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ።