ለክልሉ ብሎም ለሀገር ሠላም መረጋገጥ ሁሉም የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዲወጣ የሶማሌ ክልል የሠላምና አንድነት መድረክ ጥሪ አቀረበ፡፡

157
ለክልሉ ብሎም ለሀገር ሠላም መረጋገጥ ሁሉም የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዲወጣ የሶማሌ ክልል የሠላምና አንድነት መድረክ ጥሪ አቀረበ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 04/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የሶማሌ ክልል የሠላምና አንድነት መድረክ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ የሀገሪቱንና የክልሉን ወቅታዊ ጉዳዮች አስመለክቶ የጋራ አቋም መግለጫ አውጥቷል።
የመድረኩ አባላት የሆኑት የክልሉ የሀገር ሽማግሌዎች ዛሬ በጅግጅጋ ከተማ ባደረጉት አስቸኳይ ስብሰባ ባወጡት የጋራ አቋም በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ ባለፉት 30 ዓመታት የነበሩ ዘርፈ ብዙ ችግሮችና መከራዎች ብዙ ዋጋ ማስከፈላቸውን ገልጸዋል፡፡ ከለውጡ በኋላ በተለይ ባለፉት ሦስት ዓመታት የታየው ሠላምና ለውጥ በማስጠበቅ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ አለብን ብለዋል። መድረኩ ባወጣው መግለጫ የዜጎችን አንድነትና ወንድማማችነት የማስጠበቅ ኃላፊነት የሁሉም መሆኑን አሳስቧል፡፡
የክልሉንም ሆነ የሀገሪቱን ሠላምና ፀጥታ ለማወክ የሚንቀሳቀሱ አካላትና ኃይሎች ከተግባራቸው እንዲቆጠቡ የሶማሌ ክልል የሠላምና አንድነት መድረክ ጥሪ አቅርቧል። ባለፉት 30 ዓመታት በሶማሌ ክልል የነበረው እጅግ የከፋ ጭቆናና አፈና ከለውጡ በኋላ በመወገዱ ዜጎች አስተማማኝ ሠላም በማግኘታቸው ክልሉ ሠላምና ፀጥታ የሰፈነበት በመሆን ለሀገሪቱም ተምሳሌት መሆን በመቻሉን መድረኩ ጠቅሷል፤ ይህንን ለማወክ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን በጋራ መታገል እንደሚገባም አሳስቧል።
በሶማሌ ክልል ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው አስተማማኝ ሠላምና ፀጥታ የበለጠ ለማስጠበቅ መንግሥት ኃላፊነት እንዳለበት በመገንዘብ ፀጥታውን ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱት ኃይሎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ አለበት ብለዋል። ይህንን አስመልክቶ የሶማሌ ክልል የሠላምና አንድነት መድረክ የሚከተለውን ባለ አምስት ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቷል:-
1. የሶማሌ ክልል ሕዝብ፣መንግሥት እንዲሁም በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች የክልሉን ብሎም የሀገሪቱን ሠላምና ፀጥታ በጋራ የመጠበቅ ኃላፊነት ስላለባቸው ይህንኑ ኃላፊነት እንዲወጡ መድረኩ አሳስቧል።
2. ማንኛውም የሶማሌ ክልል ነዋሪ የክልሉ ሠላም፣ አንድነት፣ ወንድማማችነትና ከክልሉ ጎረቤቶች ጋር በሠላም ለመኖር ኃላፊነት ስላለበት ይህንን ለማረጋገጥ የበኩሉን መወጣት እንዳለበት የሶማሌ ክልል ሠላምና አንድነት መድረክ አሳስቧል።
3. በመጪው ግንቦት 28 በሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ላይ እስካሁን በሶማሌ ክልል ከ3 ሚልዮን በላይ ዜጎች የመራጭነት ካርድ ወስደዋል፤ ምርጫው በሠላማዊ ሁኔታ እንዲካሄድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስርዓት በጠበቀ መልኩ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉና ኃላፊነታቸውን መወጣት ይገባቸዋል።
4.ማንኛውም በሶማሌ ክልል በፀጥታ ማስከበር ላይ የተሰማራ የፀጥታ አካልና ኃይሎች የክልሉ ሠላምና ፀጥታን የማስጠበቅ ተግባርና ኃላፊነት ስላለበት ይህንኑ የሚያውኩ አካላት እና ኃይሎች በንቃት በመጠበቅ የተጣለበትን ሀገራዊ እና ክልላዊ ኃላፊነት እንሰዲወጡ መድረኩ ያሳስባል።
5. መድረኩ ለሶማሌ ክልል ሕዝብ በነገው እለት የሚከበረውን 1 ሺህ 442ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል እንኳን በሠላም አደረሳችሁ እያለ በዓሉ በሠላም እንዲጠናቀቅ የክልሉ ሕዝብ እና የፀጥታ አካላት በጋራ በመሥራት የበዓሉን ድምቀት ማስከበር አለባቸው ብሏል።
መድረኩ ለኃይማኖቱ ተከታዮች በሙሉ “እንኳን ለ1 ሺህ 442 የኢድ አልፈጥር በዓል በሠላም አደረሳችሁ” የሚል መልእክት አስተላልፏል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“በዒድ አል ፈጥር በዓል ዋዜማ ላይ ሆነን ስለ ምሕረት፣ ስለ ይቅርታ እና ስለ ፍቅር እንጂ፣ ስለ ጠብና ጥላቻ ማሰብ ያስቸግራል፤ ቀጣይ ጊዜያትም ስለ አንድነት እንጂ ስለ መለያየት የምንዘምርባቸው ጊዜያት እንደማይሆኑ ተስፋ አደርጋለሁ” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
Next articleየሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር ነዋሪዎችን እና የመስህብ መዳረሻዎችን ተደራሽ የሚያደርግ የ207 ኪሎ ሜትር መንገድ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ።