
“ቴምርና ሃይማኖታዊ ትስስሩ”
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 04/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ቴምር ቅዱስ ወር በመባል በሚታወቀው የረመዳን ጾም ወቀት በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በብዛት ለምግብነት የሚውል ልዩ ማፍጠሪያ ነው፡፡
ምግቡ ሃይማኖታዊ ይዘት እንዳለው የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ይገልጻሉ፡፡
ከሃይማኖታዊ ፋይዳው አንዱ በረመዳን ወር ነበዩ መሐመድ በሚያፈጥሩበት ጊዜ ቴምርን ይጠቀሙ ነበር፤ በመሆኑም የእምነቱ ተከታዮች ነቢዩ መሐመድ ያስቀመጡላቸውን ሕግጋት መተግበር ስለአለባቸው በቴምር የአፍጥር ሥነ ሥርዓት እንደሚከወን በአዲስ አበባ የአቅፋ መስጂድ መምህር መሐመድ አሚን ተናግረዋል፡፡
የነቢዩ መሐመድን አስተምህሮ መከተል ደግሞ ጽድቅን ያስገኛል ተብሎ ስለሚታመን ምዕመናን በረመዳን ወር በልዩ ሁኔታ ቴምርን እንደሚጠቀሙ ነው ያስረዱት።
እንደ መምህር መሐመድ ገለፃ የእምነቱ ተከታዮች ቴምርን በቅርበት ማግኘት ካልቻሉ ደግሞ በውኃ ማፍጠር ይችላሉ፡፡ የሃይማኖቱ ተከታዮች ቴምር በሌለበት በውኃ የሚያፈጥሩበት ዋናው ዓላማ “እያንዳንዱ ሕይወት የተመሰረተው ከውኃ ነው” ተብሎ በቅዱስ ቁራን ስለተፃፈና የነበዩ መሐመድም አስተምሮ ስለሆነ ነው ብለዋል መምህር መሐመድ፡፡
ከቴምርና ከውኃ በተጨማሪም ሳምቡሳና ሾርባም የአፍጥር ምግቦች ሊሆኑ እንደሚችሉ የገለጹት መምህሩ በዋናነት ግን ቴምር ተመራጭ መሆኑን አስረድተዋል። ቴምር የእምነቱ ተከታዮች በፆም ወቅት ምንም ምግብ ሳይመገቡ የዋለው ሰውነታቸው ተሎ ከድካም እንዲላቀቅ የማድርግ ኀይል እንዳለውም ተናግረዋል።
ቴምር ሲመገቡ ጉልበትና ብርታት እንደሚሆናቸውም አስረድተዋል።
ቴምር የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች በብዛት በረመዳን ወር በጋራ በመኾን ለማፍጠሪያ የሚጠቀሙበት ምግብ መሆኑን የተናገሩት መምህር መሐመድ የአብሮነት፣ የመተሳሰብና የአንድነት መገለጫ ነውም ብለዋል፡፡
የእምነቱ ተከታዮች 1፣3፣5፣7፣9….. የመሳሉትን ኢተጋማሽ የቴምር ፍሬዎች በማቅረብ በጾም ወራት እንደሚያፈጥሩም ተናግረዋል። ኢተጋማሽ ቁጥሮችም ማሕበራዊ ትስስሮችን የሚያሳዩና የአንድነት ተምሳሌቶች ናቸው ብለዋል የሃይማኖቱ መምህር፡፡
በረመዳን ወቅት በእምነቱ ተከታዮቹ ኢተጋማሽ የቴምር ፍሬዎችን መጠቀም ጽድቅን ያስገኛል ተብሎ እንደሚታመንም ገልጸዋል፡፡ በታላቁ ረመዳን ወር በአፍጥር ወቅት ገንዘብ ያላቸው ገንዘብ ለሌላቸው ቴምር በመግዛት በጋራ ማፍጠርም የተለመደ ተግባር መሆኑን አስገንዝበዋል።
መምህር መሐመድ የቴምር ዓይነቶችም የተለያዩ መኾናቸውን ተናግረዋል። ከሁሉም በላይ ግን “እሸት” ቴምር ተመራጭ መኾኑን ነው የነገሩን። ከዚህ ሌላ “አጅዋን” የሚባል ቴምር ውድና በባህላዊ መድኃኒትነት ጭምር የሚያገለግል ነው ብለዋል።
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባበው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ