“በተለያዩ ጊዜያት በተዘጋጁ የአፍጥር መርኃግብሮች ላይ ልዩነቶቻችን ሳይገድቡን ማዕድ የተጋራንባቸው መድረኮች የአብሮነታችን ውኃ ልክ ትክክለኛ ማሳያዎች ነበሩ” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

88
“በተለያዩ ጊዜያት በተዘጋጁ የአፍጥር መርኃግብሮች ላይ ልዩነቶቻችን ሳይገድቡን ማዕድ የተጋራንባቸው መድረኮች የአብሮነታችን ውኃ ልክ ትክክለኛ ማሳያዎች ነበሩ” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን
ባሕር ዳር: ግንቦት 04/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ለእስልምና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
አቶ ደመቀ ያስተላለፉት መልዕክት ቀጥሎ ቀርቧል።
ለመላው የሀገራችን ሙስሊሞች፤
~~~~~~~
ለ1 ሽህ 442ኛ ጊዜ በድምቀት ለምናከብረው የኢድ አልፈጥር በዓል እንኳን በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
ታላቁ የረመዳን ፆም በአማኞቹ ዘንድ ልዩ ሃይማኖታዊ ትርጉም ያለው ሲሆን፤ በአንድ ወር የፆም~ፀሎት ጊዜ ከዕምነቱ ውጪ ያሉ ወገኖቻችንን ጋር አንድነታችንን ይበልጥ ለማጥበቅ መልካም አጋጣሚ የፈጠረ ነበር።
መልካም አጋጣሚዎችን ተከትሎ በተለያዩ ጊዜያት በተዘጋጁ የኢፍጠር መርኃግብሮች ላይ ልዩነቶቻችን ሳይገድቡን ማዕድ የተጋራንባቸው መድረኮች የአብሮነታችን ውኃ ልክ ትክክለኛ ማሳያዎች ነበሩ።
በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር ተሰባስበን አንድነታችንን ይበልጥ የሚያጠብቁ እና የሚያደምቁ መርኃ ግብሮችን ሀገራዊ መሠረት እና ይዘት እንዲኖራቸው የበለጠ መሥራት ይጠበቅብናል።
ባሳለፍናቸው ጊዜያት በዜጎቻችን ላይ ያጋጠሙ አሳዛኝ ጥፋቶች እንዳይደገሙ እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ ከውስጥ እና ከውጭ ከገጠመን ፈተና በጥበብ ለመሻገር በፅናት መረባረብ ይኖርብናል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በተለየ የዜጎቿ ደኅንነት እንዲጠበቅ፣ አንድነታቸው እንዲጠናከር እና እንዲደምቅ የሻተችበት ወቅት ላይ እንገኛለን።
ይህ ታሪካዊ የለውጥ ጉዞ በልዩነቶቻችን ላይ ቆሞ ከመሳሳብ ይልቅ፤ አንድነታችንን በሚያፀኑ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ተጎጂ ወገኖችን የመደገፍና ዘላቂ ሰላም እውን ማድረግ ቀዳሚው ኃላፊነታችን ይሆናል፡፡
በመጨረሻም በታላቁ የረመዳን ወር ከአንድነታችን የሚቀዳው መደጋገፍ፣ መተሳሰብ እና መረዳዳት ኢትዮጵያዊ መሠረቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አደራ ለማለት እወዳለሁ።
መልካም በዓል!
Previous articleየታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት ኢጋድ የድርሻውን ሚና እንደሚወጣ የኢጋድ የግጭት ተንታኙ ገለጹ፡፡
Next article“የኢድ አልፈጥር በዓል ስናከብር ሃይማኖታዊ አስተምህሮቱ በሚያዘውና በሚፈቅደው መሠረት ስለሀገራችን ሰላምና አንድነት እየተጋን የራሳችንንም አስተዋፅኦ እያበረከትን ሊሆን ይገባል” ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር