በርዕሰ መስተዳድሩ የተመራ የሥራ ኃላፊዎች ልዑክ የስንዴ ኩታ ገጠም ማሳዎችን እየጎበኘ ነው፡፡

258

በአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህ የተመራ ልዑክ በምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤልያስ ወረዳ የስንዴ ኩታ ገጠም ማሳዎችን እየጎበኘ ነው፡፡

በክልሉ በስንዴን በኩታ ገጠም በማምረት ከሚታወቁ አካባቢዎች ደብረ ኤልያስ አንዱ ነው፡፡ በወረዳው 21 ሺህ 500 ሄክታር ማሳ በኩታ ገጠም በስንዴ ሰብል ተሸፍኗል። ከ12 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችም ተሳታፊ ሆነዋል። አዘራሩ የተቀናጀ የግብርና አሠራሮችን የተከተሉ በመሆኑ ለግብርና ውጤታማነት ማሳያ እንደሆነ ይታመናል፡፡

ስንዴ እና ሌሎች የሰብል አይነቶችን በኩታ ገጠም መዝራት (ተመሳሳይ ሰብሎችን በአንድ አካባቢ መዝራት) ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሮችን ህይወት ያሻሽላል፤ ከኢንዳስትሪዎች ጋር ቀጥተኛ የገበያ ትስስር ለመፍጠርም አመቺ ነው፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ እና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የአካባቢውን የምርት ሁኔታ እና የአመራረት መንገዶችን መጎብኘታቸውም በዘርፉ የሚታዩ ውስንነቶችን ለመፍታት እንደሚያግዝ ይታመናል፡፡

በአማራ ክልል ግብርናውን ለማዘመን የተቀናጀ እና ዘመናዊ አስተራረስ በሙከራ ደረጃ እየተተገበረ ይገኛል፡፡
ርዕሰ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህ በዚህ ዓመት በክልሉ ትኩረት ከሚደረግባቸው ተግባራት መካከል ግብርናውን ማዘመን መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል፡፡

ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ – ከደብረ ኤልያስ

Previous articleርዕሰ መስተዳድሩ ለቢሮ እና የተለያዩ ተቋማት ኃላፊዎች ሹመት ሰጡ፡፡
Next articleማልታ ስደተኞችን ለመቀበል ተስማማች፡፡