የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት ኢጋድ የድርሻውን ሚና እንደሚወጣ የኢጋድ የግጭት ተንታኙ ገለጹ፡፡

100
የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት ኢጋድ የድርሻውን ሚና እንደሚወጣ የኢጋድ የግጭት ተንታኙ ገለጹ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 04/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) የግጭት ተንታኙ ዶክተር ሰንዳይ ኦኬሎ ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ልዩ ቃለመጠይቅ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ በርካታ ውስብስብ ችግሮች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡
“ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን ውዝግብም ኢጋድ በሚገባ ተረድቷል፣ የሌሎች ሀገራት ፍላጎትና ጣልቃ ገብነት ምን እንደሚመስልም ጠንቅቀን እናውቃለን፤ ኢጋድም ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለው ነው” ብለዋል፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ አዲስ አይደለም ያሉት ተንታኙ በከፍተኛ ጥንቃቄ ሊታይ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡ ለዓመታት በጠረጤዛ ላይ ያለ ነገር ግን በሁኔታዎች መለዋወጥ ምክንያት ድርድሩ በጥሩ መልኩ መጠናቀቅ የተሳነው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ኢጋድ የግድቡን ነባራዊ ሁኔታ በመዳሰስ፣ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገት ያለውን ፋይዳ እና አስፈላጊነት በጥንቃቄ በመተንተን ለሚመለከተው አካል ያደርሳልም ብለዋል፡፡
“የግድቡ ጉዳይ የኢትዮጵያ ብቻ አይደለም፤ ቀጣናዊ ብቻም አይደለም፤ በብዙ መመዘኛ ዓለም ዓቀፍ ይዘት ያለው ጉዳይ ነው” ብለዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ የሚደረግ ድርድር፣ ንግግር እና ስምምነት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲከናዎንም ኢጋድ የሚጠበቅበትን ይወጣል ብለዋል፡፡ ድርድሩ ሁሉንም የተፋሰሱን ሀገራት አሸናፊ በሚያደርግ መልኩ መቀጠል እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡
በሕዳሴ ግድቡ ላይ የኢጋድ አባል ሀገራት ተሳትፎና ሚና በአፍሪካ ሕብረት ማዕቀፍ ውስጥ እንደሚሆንም ገልጸዋል፡፡ ኢጋድ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ያለውን የድንበር ውዝግብ በጥልቀት መመልከቱንም ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የስደተኞች ሰብዓዊ ቀውስ ልዩ ትኩረት የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡ በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለውን የሕግ ማስከበር ዘመቻ እና ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን ተጽዕኖና በሀገሪቱ እየተስተዋለ ያለውን ብሔር ተኮር ጥቃትም ኢጋድ ይገነዘባል ብለዋል፡፡
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ጨምሮ ሌሎች ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ችግሮች፣ ተደራራቢ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች መኖራቸውን በመግለጽም ከስድስተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ጋር ተያይዞ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን ከመተንተን ጀምሮ ለችግሮቹ የመፍትሔ አካል እንደሚሆን ጠቅሰዋል፡፡
በእነዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሁሉም የኢጋድ አባል ሀገራት የጋራ ጥረታቸውን እንዲያደርጉ ሳምንታዊና ወርሃዊ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ በመረጃ ላይ የተመሠረተ ትንታኔ ይሠራልም ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየኢድ አልፈጥር በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ ዝግጅት ማድረጉን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።
Next article“በተለያዩ ጊዜያት በተዘጋጁ የአፍጥር መርኃግብሮች ላይ ልዩነቶቻችን ሳይገድቡን ማዕድ የተጋራንባቸው መድረኮች የአብሮነታችን ውኃ ልክ ትክክለኛ ማሳያዎች ነበሩ” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን