ብልጽግና ፓርቲ በመካነ ኢየሱስ ከተማ የማኒፌስቶ ገለጻ፣ እጩ ተወዳዳሪዎች ትውውቅ እና የምርጫ ቅስቀሳ አካሄደ፡፡

263

ብልጽግና ፓርቲ በመካነ ኢየሱስ ከተማ የማኒፌስቶ ገለጻ፣ እጩ ተወዳዳሪዎች ትውውቅ እና የምርጫ ቅስቀሳ አካሄደ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 03/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብልጽግና ፓርቲ በደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ ወረዳ መካነ ኢየሱስ ከተማ
የማኒፌስቶ ገለጻ፣ እጩ ተወዳዳሪዎች ትውውቅ እና የምርጫ ቅስቀሳ አካሂዷል፡፡
በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ መርሃ ግብር መሠረት መጭው ስድስተኛ ሀገራዊ ምርጫ በተያዘው ግንቦት ወር መጨረሻ ይካሄዳል።
ለ6ኛ ሀገራዊ ምርጫ በአማራ ክልል ከሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከልም አንዱ የብልጽግና ፓርቲ ነው፡፡
ፓርቲው ለምርጫው ያቀረባቸውን እጩ ተወዳዳሪዎች በሚወዳደሩባቸው የተለያዩ አካባቢዎች እየተንቀሳቀሰ በማስተዋወቀ ላይ
ይገኛል፤ ማኒፌስቶውን ለሕዝብ በማስተዋወቅ የምረጡኝ ዘመቻም እያካሄደ ነው፡፡
ፓርቲው ዛሬ በደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ ወረዳ መካነ ኢየሱስ ከተማ የማኒፌስቶ እና የእጩ ተወዳዳሪዎች ትውውቅ እንዲሁም
የምርጫ ቅስቀሳ አካሂዷል፡፡
በቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ሕዝቡን የስልጣን ባለቤት ከማድረግ በሻገር ሀገር እንደ ሀገር የምትቀጥልበት፣ ስጋቶችን የምትሻገርበት
እና ታላቋን ኢትዮጵያ ለትውልድ ለማስተላለፍ መሠረት የሚጣልበት መሆኑን የመካነ ኢየሱስ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል
ከንቲባ ክንድየ ንጉሴ ገልጸዋል፡፡ ብልጽግና ፓርቲ በምርጫው ለማሸነፍ ከመወዳደር በላይ ምርጫው ትዓማኒ እና ፍትሐዊ ሆኖ
እንዲጠናቀቅ እየሠራ መሆኑን የተናገሩት ከንቲባው ሕዝቡ ስልጡን፣ በሃሳብ የበላይነት የሚያምን እና ችግሮችን በመነጋገር
ለመፍታት የሚታትር መሆን ይኖርበታል ብለዋል፡፡
ምርጫው የሚፈለገውን ዓላማ እንዲያሳካ የሕዝብ እና የሀገር ሰላም አስፈላጊ በመሆኑ ከመንግሥት ጎን በመቆም ለጋራ ሰላም
በጋራ እንዲሰራም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
“ብልጽግና ለዘመናት በአማራ ሕዝብ ላይ የተዘራውን የተሳሳተ ትርክት እያረመ የሚገኝ ፓርቲ ነው” ያሉት የደቡብ ጎንደር ዞን
ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኅላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ ናቸው፡፡ ያጋጠሙ ሀገራዊ ፈተናዎች ከዓቅማችን በላይ አይደሉም ያሉት
የጽሕፈት ቤት ኅላፊው ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት ሕብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትን በጽኑ ኢትዮጵያዊ መሰረት ላይ
ለማጽናት ፓርቲያቸው እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በማኒፌስቶ ትውውቁ እና በምርጫ ቅስቀሳው ላይ የተገኙት የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ቀለመወርቅ ምሕረቴ ምርጫው
ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሀገር ሰላም ግድ ነው ብለዋል፡፡ ምርጫም ሆነ ሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ከሀገር እና ከሕዝብ
ደኅንነት በኋላ የሚመጡ ናቸው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው የምርጫውን ሂደት ያወክን መስሏቸው ሀገርን እና ሕዝብን አደጋ ላይ
የሚጥሉ ኃይሎችን በቅንጅት መታገል ይገባል ብለዋል፡፡
የአማራ ሕዝብ ሥነ ልቦና በፍትሕ እና በእኩልነት ማመን፣ በኢትዮጵያዊነት እና ኢትዮጵያ ላይ አለመደራደር እና ለእውነት እና ሀቅ
መታገል ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ከዚህ የሥነ ልቦና ከፍታ ላለመውረድ በትብብር መቆም ይኖርብናል ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ፓርቲያቸው በምርጫ ከመወዳደር ባለፈ ምርጫው ተዓማኒ እና ፍትሐዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እየሠራ መሆኑን አቶ
ቀለመወርቅ ገልጸዋል፡፡
ብልጽግና ፓርቲ በደቡብ ጎንደር ዞን በሚገኙ 19 የምርጫ ማዕከላት እና 1 ሺህ 455 የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ የሚወዳደሩ
19 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና 38 የክልል ምክር ቤት እጩዎችን እንዳቀረበም ተገልጿል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው – ከመካነ ኢየሱስ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleዘካተል ፊጥር ምንድን ነው? መቼ ይሰጣል?
Next articleየኢድ አልፈጥር በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ ዝግጅት ማድረጉን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።