
ዘካተል ፊጥር ምንድን ነው? መቼ ይሰጣል?
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 03/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ዘጠነኛው ወር የረመዷን ወር ተብሎ
ይጠራል፡፡ በዚህ ወቅት የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ወሩን የተለያዩ ሃይማኖታዊ ተግባራት ፆም፣ ስግደት እና ምጽዋት
ይፈጸማሉ፡፡
በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የተለያዩ የምጽዋት ዓይነቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ የምጽዋት ዓይነቶች መካከል ዘካተል ፊጥር
አንዱ ነው፡፡ ለመሆኑ ዘካተል ፊጥር ምንድን ነው? መቼ ነው ተግባራዊ የሚደረግ?
ዘካ ዘካተል ሚል እና ዘካተል ፊጥር ተብሎ በሁለት ይከፈላል፡፡ ዘካተል ሚል በዓመት አንድ ጊዜ የሚሰጥ ሀብታሞች የሚያወጡት
ሲሆን ዘካተል ፊጥር ማንኛውም የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ የሆነ ራሱን እና ቤተሰቦቹን መመገብ የሚችል ሰው የሚያወጣው
ነው፡፡ ዘካተል ፊጥር ማለት ማንኛውም ሙስሊም የረመዷንን ወር ደርሶ የዒድ ሌሊትን ያገኘ የሆነ
ሰው ለድሆች ሊሰጠው የሚገባ የተመጠነ የምግብ አይነት ነው።
በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል የሃይማኖቱ መምህር የሆኑት ኡስታዝ ባህሩ ዑመር ዘካተል ፊጥር በረመዳን ወቅት
ፆመኞች ፆመው ከማጠናቀቃቸው በፊት የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡ እንደ ኡስታዝ ባህሩ ገለጻ ዘካተል ፊጥር አንድ የእስልምና
እምነት ተከታይ በፆም ወቅት ፆሙን የሚያጎሉበት ስህተት ቢፈጽም ያን ስህተት ለማስፋቅ እና ጾሙን ሙሉ ለማድረግ የሚሰጥ
ስጦታ ነው፡፡ ሥጦታው ደግሞ ለምስኪኖች እና ለጾም አዳሪዎች ነው፡፡
እያንዳንዱ ሰው ካለው ነገር ላይ እንዲሠጥ ተወስኗል፡፡ የስጦታው መጠንም በመካከለኛ እድሜ ባለ ሰው እፍኝ አምስት ወይም
ሁለት ነጥብ አምስት ኪሎ ግራም የሚመዝን ነገር እንዲሰጥ የነብዩ ሙሐመድ (ሶዐወ) ተከታዮች ወስነዋል፡፡
ዘካ ግዴታ ነው፤ ማንኛውም የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ የሆነ ሁሉ ሊያወጣው የሚገባ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ኡስታዝ
ባህሩ እንዳሉት ዘካተል ፊጥር እንደሚሰጠው ስጦታ የሚሠጥበት ቀን ይለያያል፡፡ የሚሠጠው ነገር ወደ ምግብነት ያልተቀየረ
ከሆነ ተቀባዩ የተቀበለውን ነገር ወደ ምግብነት ቀይሮ እንዲጠቀም ከአንድና ከሁለት ቀን ቀድሞ መሠጠት አለበት ብለዋል፡፡
የሚሠጠው ደግሞ የኢድ ሶላት ተሰግዶ ከማለቁ በፊት ነው፡፡ ከዚህ ካለፈ ምጽዋት ተደርጎ ይቆጠራል ብለዋል፡፡
ነብዩ ሙሐመድ (ሶዐወ) ከተሠደዱ ከሁለት ዓመት በኋላ መሠጠት የተጀመረ መሆኑንም ኡስታዝ ባህሩ ነግረውናል፡፡ ኡስታዝ
ባህሩ እንዳሉት በጾም ወቅት ለተፈጠረ ሥህተት ማካካሻ የሚሰጠው ዘካተል ፊጥር ተሚር፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ ዘቢብ እና ሌሎች
ለምግብነት የሚያገለግሉ የእህል ዘሮች ሊሆኑ ይችላል፡፡ የእህል ዓይነት መስጠት ያልቻለ በገንዘብ ተምኖ መስጠት
እንደሚችልም ገልጸዋል፡፡
ኡስታዝ ባህሩ ዘካተል ፊጥር ምስኪን እና ችግረኛ ሰዎች የኢድ አል ፈጥር በዓልን በቤታቸው እንዲውሉ ለማድረግ የሚሠጥ ነው፤
የሰጠው ሰውም ህሊናው ሰላም ያገኛል፡፡ በፈጣሪው ዘንድም ውዴታ ያገኝበታል፡፡በስጦታው ወቅት ሁሉም ሰው ለአንድ ሰው
መሥጠት ይችላል፡፡ የአንድን ሰውም ለብዙ ሰው መሥጠት ይቻላል ብለዋል፡፡
በትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m