
“መጪው ጊዜ ክረምት በመሆኑ ሁኔታው የከፋ እንዳይሆን ለተፈናቃዮች መጠለያ ለመገንባት ቁሳቁስ እየሰበሰብን ነው” ‹‹እኔ
እያለሁ ወገኔ አይራብም›› የኮምቦልቻ ከተማ በጎፈቃደኛ ወጣቶች
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 03 /2013 ዓ.ም (አሚኮ) የተሻለ የኑሮ ደረጃ የነበራቸው ሰዎች በማንነታቸው ምክንያት በተቃጣባቸው
ጥቃት ተፈናቅለው የወገናቸውን እጅ ይጠብቃሉ፤ ቤታቸው ሙሉ የነበሩትም አንድ ጊዜ በልተው ስለቀጣይ ያስባሉ፡፡ በአርጎባ ልዩ
ወረዳ መዲና ተብላ በምትጠራ ቀበሌ የሚገኙ ተፈናቃዮች በችግር ውስጥ ይገኛሉ፡፡
የኮምቦልቻ ከተማ ‹‹እኔ እያለሁ ወገኔ አይራብም›› በጎፈቃደኛ ወጣቶች ተፈናቃዮቹ ከሸራ በተሠራ መጠለያ ውስጥ እንደሚገኙ
ታዝበዋል፡፡ ከላይ ለዝናብ፣ ከታች ለጎርፍና ብርድ እየተጋለጡ መሆኑን በቦታ ተገኝተው በመመልከትም ኃላፊነታቸውን ለመወጣት
ወደ ድጋፍ ማሰባሰብ ተግባር ገብተዋል፡፡ ለተፈናቃዮች ድጋፍ ለማሰባሰብም የሚያስተባብሩትን 10 የኮሚቴ አባላት ጨምሮ 100
ወጣቶች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
የኮሚቴው ሰብሳቢ አብዱሰላም ኤሳው “መጪው ጊዜ ክረምት በመሆኑ ሁኔታው የከፋ እንዳይሆን ኮሚቴው በግንቦት ወር
መጠለያ ለመገንባት የሚያስችል ቁሳቁስ ለመሰብሰብ እየተንቀሳቀሰ ነው” ብሏል።
ምክትል ሰብሳቢዋ ኬሪያ ሰዒድ እንዳለችው ደግሞ የአካባቢው መስተዳደር ለቤት መሥሪያ ቦታ ፈቅዷል፤ ቆርቆሮና ሚስማር
የሚገኝ ከሆነም እንጨት ለማቅረብ ቃል ገብቷል፡፡ በዕቅዱ መሠረት ኮሚቴው በአራት ሳምንታት ከ1 ሺህ 600 እስከ 2ሺህ
ቆርቆሮ፣ 200 ካርቶን ሚስማርና 200 ኩንታል ሲሚንቶ ያቀርባል፡፡
የመጀመሪያው ሳምንት ቅስቀሳ የሚደረግበት ነው፡፡ ነገር ግን ሰዎች የገንዘብ፣ የአልባሳትና የምግብ ድጋፍ ማድረግ ጀምረዋል
ነው ያለችው፡፡ እናቶች የቤት እቃቸውን ሳይቀር እያመጡ ስንመለከት ሞራል አግኝተናል” ብላለች ምክትል ሰብሳቢዋ፡፡
በሁለተኛው ሳምንት የተዘጋጀው ባለ 50፣ ባለ 100፣ ባለ 200 እና ባለ 500 ብር ኩፖን ይሸጣል፡፡ ሦስተኛው ሳምንት በከተማዋ
የሚገኙ ትላልቅ ተቋማት ድጋፍ እንዲያደርጉ የሚጠየቁበት ጊዜ ነው፡፡
የመጨረሻውና አራተኛው ሳምንት በሀገር ውስጥና በውጪ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ የሚያደርጉበት ጎፈንድሚ
(የሂሳብ ቁጥር) ይከፈታል፡፡ የበጎ ፈቃደኛ ወጣቶቹ ዋነኛ ትኩረት መጠለያ መገንባት ቢሆንም ሌሎች የድጋፍ አይነቶችንም
የሚያሰባስቡ ይሆናል፡፡ ይሕንን ለማድረግም ሙሉ ጊዜያቸውን ሰጥተው የሚሠሩ ወጣቶች እንዳሉ ተመላክቷል፡፡
“እኛን ብለው ለመጡት ወገኖቻችን እኔ እያለሁ ለምን ይራባሉ የሚል ቁጪት ሊፈጠርብን ይገባል” ያለችው ወጣት ኬሪያ ችግርን
በጋራ ለመጋፈጥ ወጣቶች በአንድነት መሥራት እንደሚገባቸው መክራለች፡፡ ድጋፉ በቀጣይም በሌሎች አካባቢዎች
እንደሚቀጥል አስታውቃለች፡፡ ለወጣቶቹ ከተማውና ዞኑ ሕጋዊ ፈቃድ በመስጠት ተገቢውን ድጋፍ እያደረገ እንደሆነ ነግራናለች፡፡
ዘገቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m