“የኢድ አል ፈጥር በዓል ሲከበር በዘር ፖለቲካና ቀውስ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በጊዜአዊ መጠለያ የሚገኙ ወገኖችን በማሰብና በመደገፍ ሊሆን ይገባል” የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት

330
“የኢድ አል ፈጥር በዓል ሲከበር በዘር ፖለቲካና ቀውስ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በጊዜአዊ መጠለያ የሚገኙ ወገኖችን በማሰብና በመደገፍ ሊሆን ይገባል” የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት
ከፍተኛ ምክር ቤቱ ለ1 ሺህ 442ኛ የኢድ አል ፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 03/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ ምክር ቤቱ የ1 ሺህ 442ኛው ሂጅራ፤ የ2013 ዓ.ም የኢድ አል ፈጥር በዓልን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ ነው ለመላው የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፈው፡፡
የኢድ አልፈጥር በዓል ሲከበር ከኢድ ሶላት በፊት ግዴታ የሆነዉን ዘካተል ፍጥር በማውጣትና ለሚገባቸው በመስጠት እንዲሁም ቤተሰብና ጎረቤቶችን በመዘየር፣ የተቸገሩትን በማብላትና በማጠጣት ሊሆን እንደሚገባ መግለጫዉን የሰጡት የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሰኢድ መሀመድ ተናግረዋል፡፡
‹‹ከኢድ ሶላት መልስ በየቤታችን ሆነን ለሀገራችንና ለሕዝባችን ሰላምና ደኅንነት ከምንጊዜውም በላይ ዱአ በማድረግ ልናከብረው ይገባል›› ብለዋል፡፡ በተከበረዉ የረመዳን ወር የታየዉ መልካም ባህሪና መልካም ሥራ ጥንካሬ በሌሎችም ወራት፣ በአጠቃላይ በሕይወት ዘመን ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል ፕሬዝዳንቱ ሼህ ሰኢድ።
የኢድ አልፈጥር በዓል ሲከበር በኢትዮጵያ በሚስተዋለው የዘር ፖለቲካና ቀውስ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በዳስ ተጠልለው የሚገኙ ወገኖችን በማሰብና በመደገፍ ጭምር ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በዓሉ በጥሩ ሁኔታ የሚከበረው ቀየው ሰላም ሲሆን ነዉ ያሉት ፕሬዝዳንቱ “በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች ዜጎች በጭካኔ እየተገደሉና ከቤት ንብረታቸዉ እየተፈናቀሉ ነዉ፤ በመሆኑም ከፍተኛ ምክር ቤቱ እንዲህ አይነቱ አስነዋሪ ተግባር በእጅጉ አሳዝኖታል፣ አውግዞታልም” ብለዋል፡፡
“ጎረቤት ሰላም ካልሆነ፣ አንተም ሰላም አትሆንም” ያሉት ፕሬዝዳንቱ ሰላም ሲጠፋ የሚጎዳዉ ሁሉም በመሆኑ ሰላም የሰፈነባትና የበለፀገች ሀገር ለመጪው ትውልድ ማስረከብ የሁሉም ኀላፊነት ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ የሃይማኖት አባቶችና ሰባኪዎች ስለ ሰላም፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ ሀገር አንድነት ሊያስተምሩና ሊመክሩ እንደሚገባም አሳስበዋል ሼህ ሰኢድ በመግለጫቸው፡፡
ሙስሊሙ ኅብረተሰብ የረመዳን ፆም፣ ሶላትና መልካም ሥራን ሲያከናውን ራሱንና ቤተሰቡን ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በመከላከል ላበረከተው መልካም ተግባር ከፍተኛ ምክር ቤቱ አመስግኗል፡፡
ዘጋቢ፡- ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“ረመዳን ሕዝበ ሙስሊሙ፣ በመተዛዘን፣ በመደጋገፍና በመረዳዳት በፆምና በሶላት የሚያሳልፍበት የተቀደሰ ልዩ ወር ነው” የአማራ ክልል እስልምና ጉዳይ ከፍተኛ ምክር ቤት የእርዳታና ልማት ዘርፍ ኀላፊ ሐጂ አሕመድ አሊ።
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ሲሼኬዲ ጋር ተወያዩ።