የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ኡመር እድሪስ ለእስልምና እምነት ተከታዮች ለኢድ አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ።

284
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ኡመር እድሪስ ለእስልምና እምነት ተከታዮች ለኢድ አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ።
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 03 /2013 ዓ.ም (አሚኮ) ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ኡመር እድሪስ ባስተላለፉት መልእክት የጾም ፍች ወቅት ዘካተል ፊጥር ከሶላት በፊት መስጠት፣ ተክቢራና ሶላት ማድረስ፣ አቅመ ደካሞችንና ህመምተኞችን መጠየቅ ሃይማኖታዊ ተግባር በመሆኑ መተግብር አለብን ብለዋል።
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ በዓሉ በሰላም እንዲጠናቅ ሁሉም ኀላፊነቱን እንዲወጣም ጠይቀዋል። በበዓሉ እስልምና የሚጠይቀውን መከባበርና መተዛዘን ማሳየት አለብንም ብለዋል።
ሀገሪቱ የተደቀነባትን የሰላም እጦት በጋራ ለመሻገር በአንድነት በመቆም ወደ ፈጣሪ መቅረብ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን በአንድ በመቆም በመቀራረብና በመተባባር በጋራ እንዲሠሩም ጠይቀዋል። የነብዮን (ሰአወ) አስተምህሮትን በመከተል ሁሉም ለሰላምና ለአንድነት እንዲሠራም ነው ያሳሰቡት፡፡
በዓሉ በአደባባይ እንደመከበሩ የኮሮናቫይረስ ጥንቃቄን በተከተለ አግባብ እንዲሆንም ሐጅ ሙፍቲ ጠይቀዋል።
የዛሬውን የአዲስ አበባ የአደባባይ ፊጥራ በተመለከተ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር መመካከራቸውን ያወሱት ሐጅ ሙፍቲ አብሮነትንና አንድነትን ለማሳደግ በሚደረገው በዚህ ትልቅ የአደባባይ ፊጥራ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣም አስገንዝበዋል።
ከዚህ በፊት በአዲስ አበባ የተጠራውን የጎዳና ላይ የአፍጥር ፕሮግራም በኛ በኩል እውቅና አልነበረውም፤ የዛሬውን የጎዳና ላይ አፍጥር በተመለከተ ግን የተሳካ እንዲሆን ለማድረግ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በጋራ እየሠሩ መሆናቸውን ተቀዳሚ ሙፍቲ ተናግረዋል፡፡ “እለቱም የኛ አብሮነት እና የወንድማማችነት ጎልቶ የሚታይበት እንዲሆን ሁሉም ለጋራ ስኬቱ በጋራ መቆም አለበት” ብለዋል።
በዓሉ ዛሬ ማታ ጨረቃ ከታየች በ29ኛው ቀን ረቡዕ ይሆናል፤ ዛሬ ማታ ካልታየች ግን በዓሉ ሐሙስ እንደሚሆን ነው ሐጅ ሙፍቲ በመግለጫቸው ያስታወቁት።
ዘጋቢ፡- ጋሻው ፈንታሁን- ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበትግራይ የተረጋጋ ሕዝባዊ ሰላምና አስተዳደርን ለማረጋገጥ ሁሉም እገዛ እንዲያደርግ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አብርሃም በላይ ጥሪ አቀረቡ፡፡
Next article“ረመዳን ሕዝበ ሙስሊሙ፣ በመተዛዘን፣ በመደጋገፍና በመረዳዳት በፆምና በሶላት የሚያሳልፍበት የተቀደሰ ልዩ ወር ነው” የአማራ ክልል እስልምና ጉዳይ ከፍተኛ ምክር ቤት የእርዳታና ልማት ዘርፍ ኀላፊ ሐጂ አሕመድ አሊ።