
በትግራይ የተረጋጋ ሕዝባዊ ሰላምና አስተዳደርን ለማረጋገጥ ሁሉም እገዛ እንዲያደርግ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አብርሃም በላይ ጥሪ አቀረቡ፡፡
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አብርሃም በላይ በማኅበራዊ የትስስር ገጻቸው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ዶክተር አብርሃም ያስተላለፉት መልዕክት ቀጥሎ ቀርቧል፡፡
የትግራይ ሕዝብን ማእከል ያደረገ የተረጋጋ ሕዝባዊ ሰላምና አስተዳደርን ለማረጋገጥ የቀረበ ጥሪ በማስቀደም በሀገራችን ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ከጥቅምት 24 ጀምሮ በተከሰተው ግጭት መነሻነት በተፈጠሩት መጠነ ሰፊ ጉዳቶች በወገኖች ላይ የደረሰው የሞት፣ የአካል ጉዳተኝነት ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ፣ መፈናቀሎች ፣ ጥልቅ የስነ ልቡና ጉዳቶች ፣ የንብረት ዘረፋ መጥፋትና ውድመት፣ አላስፈላጊ መገፋፋትና የተካረሩ አመለካከቶች በአጠቃላይም ውጥረት በሕዝቦች ዘላቂ ትብብርና በሰላምና መረጋጋት የመኖር ፍላጎት ላይ የጋረጠውን ጉልህ አደጋ በተመለከተ በግልጽና በመተማመን ተገቢውን ፍትሕ መስጠት ይፈልጋል ብለዋል።
የሚደርሰው ጉዳትና ቁስልን በመቀነስና በመሻር እንዲሁም መሬት ላይ ያለውን ሁኔታ በተግባር በመቀየር በይቅርታ መንፈስና የቁርጠኛ የሰላም ወዳድነት ማረጋገጫ እርምጃዎችን በመውሰድ ሀገሬንና ሕዝቦቿን እንዳገለግል በተሰጠኝ በዚህ ትልቅ ኃላፊነት ተመድቤ ሥራዬን ስጀምር በክልሉ ሕዝብ ፣ በፌደራል መንግሥት፣ በመላው የሀገራችን ሕዝቦች ፣ በዲያስፖራ ኮምዩኒቲው እና በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ጭምር ለዚህ ወሳኝ ተልእኮዬ ስኬት ሙሉ ድጋፍና እገዛ እንደማገኝ ከወዲሁ በሙሉ ልብ በመተማመን ነው።
በትግራይ ክልል ያለው ወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታ በተለይም ችግሮችን ነቅሶ በማውጣትና መፍትሔን በመፈለግ ሒደት የችግሮችን ስሪተ ነገር የመረዳት ፣የተያያዥ መሰረታዊ ጉዳዮችን ተፅእኖ መለየትና ከሙሉ ስእል እይታ ያልጎደሉ ደረጃ በደረጃ የሚተገበሩ የመፍትሔ ሀሳቦችን ማፍለቅና በሕዝባዊ ይሁንታ በርብርብና በድፍረት በተግባር የመፈፀም ቁርጠኝነትን የሚጠይቁ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል።
ባለፋት ወራቶች በትግራይ ያለውን አጠቃላይ ሁኔታ ለመቀየር በተሠሩ በርካታ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤቶችን ለማስመዝገብ ጉልህ ተግዳሮቶች የመኖራቸው እውነታ ለፖለቲካ ትክክለኝነት የማይመቹ ከመሆናቸውም በላይ ቅድሚያ ለሚሰጠው የሰው ልጆች ህይወት ማዳን ሰብዓዊ ቀውስ እንዳይባባስ የመሥራት አንገብጋቢ ጉዳይና በአካባቢው የተሻለ አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋትን የማረጋገጥ ሥራውን ፈታኝ በማድረግ ለተጨማሪ የከፋ ጉዳት የሚዳርጉ ጉልህ ችግሮች መሆናቸውን መገንዘብም አስፈላጊ ነገር ነው።
በሕግ ማስከበር ዘመቻ ምእራፍና አንዳንድ ግጭትና ጥቃቶች በንጹሐን ዜጎችና በግፊትና በቆሞ ሞት እምቢተኝነት በርካታ ወጣቶች ሴቶች እድሚያቸው ያልደረሱ ታዳጊዎች ጭምር የሞት የአካል ጉዳት አደጋና የንብረት ውድመትም ጭምር የተጋለጡበትን ሁኔታ መቀየር አስፈላጊና አንገብጋቢ ወቅቱ የሚጠይቀው የአመራር እርምጃ ነው።
እዚህ ላይ በፌደራል መንግሥት በሕግ የማስከበር ምእራፉ የተወሰዱት ጉልህ እርምጃዎች የመንግሥትን ሕጋዊ ኃላፊነትና ግዴታዎች ለመወጣት የተፈፀሙና በሰላምና ፀጥታ ኃይላት የተሠሩ ሥራዎችም በሀገር አንድነት እና ሰላም ላይ የተቃጡ አደጋዎችን ለመቀልበስ አስፈላጊነታቸው ታምኖባቸው የተፈፀሙ ግዳጆች ናቸው። በዚህም ምክንያት በክልሉ በአሁኑ ወቅት የተገኘውን አንፃራዊ መረጋጋት በማረጋገጥ ረገድ የውድ ህይወት የመስዋእትነት ዋጋ ጭምር የተከፈለባቸው እና እየተከፈለባቸው የተረጋገገጡ መሆናቸውን በክልሉ ያለውን ጉዳይ ለመከታተል በተሰጡኝ ልዩ ተልእኮዎች ውስጥ ያረጋገጥኩት መሆኑን ግልፅ ለማድረግ እወዳለሁኝ። ነገር ግን በግጭቶችና ጥቃቶች በእነዚህ የስድስት ወራት ጊዜያቶች በትግራይ ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ ዜጎች በታጠቂ ኃይሎች የተፈፀሙ ናቸው በተባሉ እርምጃዎች የበርካታ ንጹሐኖች ደም ፈስሷል ፣ዜጎች ለአካል ጉዳተኝነት ተዳርገዋል ፣ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተፈፅመዋል፣ ሴቶችና ህፃናት ተደፍረዋል በቢሊዮን ብሮች የወጣባቸው የግልና የመንግሥት የልማት ተቋማት ንብረቶች መሰረታዊ አገልግሎት የሚሰጡ የጤናና የትምህርት ተቋማትም ጭምር ወድመዋል ተዘርፈዋል ፣ ተግዘው ተወስደዋል፣ የአርሶ አደሮች በሬ በጎች ፍየሎች እና የድሆች የእለት ምግብና የቤት መገልገያ ጥቃቅን ንብረቶችን ሳይቀር ጠፍተዋል ተዘርፈዋል።
በተለይ በእኔ እምነት በከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊነቶች ላይ እያለሁ ይህ እጅግ አሳዛኝ ጥፋት በሕዝብ ላይ ሲደርስ ቀዳሚ የሚሆነው ጉዳቱን በሚቀንሱና ሌላ ተጨማሪ አደጋ በሕዝቡ ላይ እንዳይደርስ በሚከላከሉ ህይወት አድን ሥራዎች በፍጥነት በመሳተፍ መሥራት ፣በሀገር ደኅንነት ላይ የተጋረጠውን ጉልህ አደጋ መቀልበስና ሀገሪቱን በአጠቃላይ ወደ ሰላምና መረጋጋት ለመመለስ በሚጠቅሙ ተግባራት ላይ ማተኮር በዚህም በርካቶችን ከተጨማሪ ሞት እና የእጅግ የከፋ ጉዳት ለማዳን አቅም የተቻለውን ሁሉ ማድረግ መሆኑን ብገነዘብም ፤ ባለፋት ስድስት ወራት በነበሩ እጅግ ፈታኝና ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሹ ሁኔታዎች በግሌ ለትግራይ ሕዝብና ለመላው የሀገራችን ሕዝቦች በነበረኝ አገልግሎት ውስጥ በማናቸውም መልኩ ውስንነቶች መኖራቸውን ባለመካድ መቆሜንና ሕዝቡ ለዘላቂ ሰላሙ እና መረጋጋቱ አሁንም ቅድሚያ በመስጠት ከፊታችን ያለውን ወሳኝ የህይወት አድን ሥራ ፣ ሰላም ግንባታና መልሶ ማቋቋም ተልእኮ በስኬታማነት እንድወጣ እንዲያግዘኝ በትህትና እማፀናለሁ።
በትግራይ የተከሰተውን ግጭት በማስቆም ሰብዓዊ ቀውስን የመግታት ጉዳይ ቀደም ሲል እንዳስቀመጥቁት የችግሮችን ስሪተ ነገርን መረዳትንና ሚዛናዊ አቋም መያዝን የሚጠይቅ፣ የችግሮችን ተያያዥነትና ተፅእኖዎችን በጥንቃቄ መለየትን የሚሻ እንዲሁም የመፍትሔ አሰጣጥንም በተመለከተ የሙሉ ስእል እይታን ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ፣ ለህይወት ማዳን ሰላምና መረጋጋት ቀዳሚ አጀንዳነት የተለየ ቁርጠኝነት የሚጠይቅ መሆኑን በሚገባ መረዳት ለዘላቂ መፍትሔ አሰጣጥ ውጤታማ አቀራረብ ሲሆን በዚህ ውስጥም የሕዝብ ፍላጎትና ምልአተ ተሳትፎም አስኳል ጉዳይ መሆኑን መገንዘብን የሚጠይቅ ነው።
በአሁኑ ሰአት በትግራይ ክልል ቀደም ሲል በተከሰቱ ችግሮችና በየቦታዉ በሚያጋጥሙ ልዩ ልዩ ጥቃቶች ለዜጎች አስፈላጊውን መሰረታዊ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እና አስተማማኝ ፀጥታና ሰላምን ለማረጋገጥ በሕዝብ ተሳትፎ ላይ የተለየ ሥራ መሥራትን የሚጠይቅ ሁኔታ መኖሩን መረዳት የሚያስፈልግ ነው። በዚህ ረገድ በመንግሥት በኩል የሕዝቡን ፍላጎት የእለት ተእለት ችግሩንና ሁነኛ ስጋቱንም ጭምር በሚገባ በማድመጥ ሳይውል ሳያድር ለመፍታትና በሒደትም ለዘላቂ ሰላምና መረጋጋት መሰረት የሚጥሉ አፋጣኝ ሥራዎችን መሥራት ላይ ትኩረት ማድረጉን በመልካም እድገትነት ሊወሰድ የሚገባ መሆኑን ሰላም ወዳድ ኃይሎችና በተለይም የሰላሙ ባለቤትና ዋና የሆነው የትግራይ ሕዝብ በአስተውሎት እንዲገነዘቡት ያስፈልጋል።
በሌላ በኩል በግጭቶችና የጸጥታ መደፍረስ ጊዜ እነዚህ ጉዳቶች ተጠባቂ ናቸው የሚሉ የአጠቃላይ ድምዳሜዎች አዝማሚያና በወገኖች ላይ ለደረሱ አሳዛኝ ጉዳቶች የተለየ እና አስቸኳይ ትኩረት እንዳልተሰጠ የሚያስመሰሉ ክፍተቶች በፌደራል መንግሥትና በጊዜያዊ አስተዳደሩ በተጨባጭ የተሠሩ ሥራዎችን መና ለማድረግ ለሚሠሩ የውስጥና የውጭ የቅርብና የሩቅ ሴረኞች ምኞት ተጋላጭም የሚያደርጉ በመሆናቸው መለየትና መታረምም ይገባቸዋል።
በትግራይ በተከሰተው ችግር ላይ በግልፅ ወጥቶ ለመናገር እና ሁኔታውን በሚቀይር ሥራ በመሳተፍ የመፍትሔው አካል የመሆን ጉዳይ የፖለቲካና የዘር ወገንተኝነትን አይጠይቅም። በመሆኑም ዜጎች በሁሉም ቦታ ለወገኖቻቸው እንዲደርሱ ከጥላቻ ንግግር ሰላባነት ወገኖቻቸውን በሥራና በማኅበራዊ አካባቢዎቻቸው በሙሉ እንዲጠብቁ በግልና በቡድን ጭምር ርህራሔና አቃፊነትን በመላበስ ለዜጎቻቸው የሰላም ወዳጅነታቸውን በተግባር እንዲያሳዩ ልዝበት እንዲፈጠር አበክረው እንዲሠሩ በመደበኛና በማኅበራዊ ሚዲያ ከሚቀነቀኑ ተንኳሽ ንግግሮችና በቅርብ የተለመዱ መጠሪያዎችን ከመጠቀም እንዲቆጥቡ ከዚህ የጠብ ገበያ ለማትረፍ ያሰፈሰፉ ኃይላትንም እንዲያሳፍሩ በአጠቃላይ ክልሉን ወደ ሰላምና መረጋጋት ለመመለስ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ሰብዓዊ ጥሪዬንም አቀርባለሁ።
መላው የሀገራችን ሕዝቦች!
ሰላም የጀግኖች አጀንዳ ነው ! ብዙ መታገስን ፣ አስፍቶ ማሰብን ፣ ብዙ አይቻልሞችን መድፈርን ፣ ነገን ማየትንና በትላንት እውነታዎች ላይ ግልፅ መሆንንና መጨከንን የሚጠይቅ! ከቅርብ ግዜ ወዲህ በወንድማማች ሕዝቦች መካከል ውጥረትን ለመፍጠር ለዓመታት የተሠሩ ሥራዎችና በቸልተኝነትና በእልህ በተተው ጉዳዮች የሰውን ህይወት ማጥፋትና ከኖረበት ቀዬው ማፈናቀል የመሳሰሉ መራራ የጥላቻ ፍሬዎችን እየተመለከትን ቢሆንም ለዓመታት ከተገነባው የአብሮነት እና የመተሳሰብ መልካም ዘመናት የጉዞ ታሪካችን ጋር የማይወዳደር በመሆኑ እንደ ሕዝቦች ወደ ማስተዋል እና ስክነት ለመመለስ ሳንውል ሳናድር መስራት በመጀመር ለትውልዶች የምንሰንቀውን ስንቅ ከቂም ከጥላቻና ከበቀል ይልቅ መተማመን ፣ ይቅር መባባል ፣ መደጋገፍንና አብሮነትን ለማጎልበት የሚበጁ መሆናቸውን የማረጋገጥ የትውልድ ኃላፊነት አለብን።
በዚህ አጋጣሚ በትግራይ ጸጥታና ሰላምን በማስፈን ፣ ፍትሕን በማረጋገጥና ዘላቂ ሰላምን በማምጣት፣ ሰብዓዊ እገዛ በማድረግና መልሶ ግንባታ ሒደት መላው የሀገራችን ሕዝቦች በተለይም የአጎራባች ክልሎችና የኤርትራ ሕዝቦች፣ የፌደራል መንግሥት ፣ የዲያስፖራ ኮሚዩኒቲ አባላት፣ምሁራን፣ ባለሀብቶች፣ የኮሚዩኒቲ ማእከሎች፣ የሙያ ማኅበራት፣ የኪነ-ጥበብ ሰዎች፣ ተፅእኖ ፈጣሪ ተቋማትና ግለሰቦች ፣ የሚዲያ አካላት ማኅበረሰብ አንቂዎች ፣ የሃይማኖት አባቶች ፣ የሀገር ሽማግሌዎች ፣ የወጣት እና ሴቶች አደረጃጀቶች፣ በግል እና በመንግሥት ሥራ የምትተዳደሩ ዜጎች ለዚህ አንገብጋቢ ተልእኮ ልባችሁን፣ ግዜአችሁን፣ ድጋፋችሁን እና አቅማችሁ የሚፈቅደውን ሁሉ በማድረግ እንድትሳተፉ የአደራ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ።
በመጨረሻም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የትግራይን ወቅታዊ ችግር በሁሉም መስክ በዘለቄታ ለመፍታት በሚያግዙ ገንቢና ሰላማዊ እንዲሁም ሕጋዊ የአሠራርና የመፍትሔ አማራጮች ካላቸው አካላት ጋር በቅርበት ለመሥራት ሙሉ በሙሉ ዝግጅት ያለው መሆኑን ስገልፅ በዚህ የታሪክ ኃላፊነት ወቅት ዜጎች የበኩላቸውን ለማድረግ እንዲረባረቡ የአደራ መልእክቴን በማስተላለፍ ጭምር ነው።
አብርሃም በላይ በርሀ
የትግራይ ብሔራዊ ክልል መንግሥት ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈፃሚ