በአዲስ አበባና በአንዳንድ የኦሮሚያ ከተሞች የተቀናጀ የሽብር ጥቃት ለመፈፀም አቅደው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የሽብር ቡድን አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የደኅንነትና ጸጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ።

354
በአዲስ አበባና በአንዳንድ የኦሮሚያ ከተሞች የተቀናጀ የሽብር ጥቃት ለመፈፀም አቅደው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የሽብር ቡድን አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የደኅንነትና ጸጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ።
የደኅንነትና ጸጥታ የጋራ ግብረ ኃይል ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በአዲስ አበባና በአንድ አንድ የኦሮሚያ ከተሞች ሁከት፤ ሽብርና ትርምስ በመፍጠር ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳቸውን ለማሳካት በሚንቀሳቀሱ የውጭ እና የውስጥ ፀረ-ሰላም ኃይሎች የሚደገፉ የሸብርተኞቹ የህወሓትና የሸኔ ቡድን አባላት በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ ሴራ ወጥነው ወደ እንቅስቃሴ ለመግባት በዝግጅት ላይ እንዳሉ በጋራ ግብረ ኃይሉ በተደረገባቸው ጥብቅና የተቀናጀ ክትትል በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ይሄንን እኩይ የጥፋት ሴራ ለመፈጸም ከውጭ በተለያዩ አካላት በሚደረግላቸው የፋይናንስና የሎጀስቲክስ ድጋፎች ተልዕኮ ተቀብለው ሲንቀሳቀሱ የነበሩት የሸብርተኞቹ የህወሓትና የሸኔ ቡድን አባላት ከከባድ እስከ ቀላል የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎችን ከመሰል ጥይቶች፣ ቦንቦችና
ተቀጣጣይ ቁሶች ጋር ለጥቃት ሊጠቀሙባቸው ያዘጋጇቸው ቢሆንም፤ የታቀደውን የጥፋት ተልዕኮ ማክሸፍ መቻሉን መግለጫው አትቷል።
መግለጫው አክሎም፣ለሸብርተኞቹ በአዲስ አበባ ቦሌ ኤርፖርትና በሌሎችም አካባቢዎች ጭምር የተለያዩ ሀገራት የብር ኖቶች በህገወጥ መንገድ ሊተላለፉ እንደነበር ጠቁሞ፤በተደረገ ጥብቅ ክትትልና ፍተሻም ለጥፋት ተልዕኮ መፈፀሚያቸው ሊጠቀሙበት የነበረ ከ305 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላር እና ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ የኢትዮጵያ ገንዘብ መያዙን አስታውቋል፡፡
መግለጫው እንዳብራራው፤ ይሄንን የጥፋት ተግባር ለመፈፀም ቀደም ሲል ትግራይ ድረስ ታጣቂዎቹን መልምሎ በመላክ ከሽብርተኛው የህወሓት ቡድን ስልጠና እንዲወስዱ በማድረግ በንፁሃን ዜጎች ላይ ብሄር ተኮር ጥቃቶችን ሲፈፅም የቆየው የአሸባሪው የሸኔ ቡድን፤ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን ጨምሮ የፋይናንስና የሎጀስቲክስ ድጋፎችን ሲያገኝ እንደቆየና፤በቡድኑ ላይ የመንግስት ፀጥታ አካላት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እየወሰዱበት ባለው ተከታታይ እርምጃ እየተዳከመና ከባድ ኪሳራ እያጋጠመው መምጣቱን ተከትሎ፤መሰረተ ልማቶችን
እንዲያወድሙ እንዲሁም በታዋቂ ሰዎች፤በከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና በዜጎች ላይ በተደራጀና በተጠና መንገድ ግድያ እንዲፈፀሙ አባ ቶርቤ በሚል የሰየማቸውን የከተማ ክንፍ አሸባሪዎች ወደ ተለያዩ ከተማዎች አሰማርቶ ነበር ብሏል፡፡
ለእነዚህ የሽብር ቡድኖች የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችን፣ ቦንቦችን፣ ለፍንዳት ስራ የሚውሉ ተቀጣጣይ ቁሶችን እንዲሁም ሰነዶችን በስውር ለመስጠት ሲያጓጉዙ የነበሩ በርካታ የቡድኑ ተጠርጣሪ አባላት መያዛቸውን የጋራ ግብረ ኃይሉ በመግለጫው አመልክቷል፡፡
ከተጠርጣሪዎች መካከልም አብዲሣ ጣፋ ቆጮልቴ እና ኤብሣ ተረፋ ቶኮሣ የተባሉት ግለሰቦች ከአማራ ክልል ሁመራ አካባቢ በኮድ ሁለት የታርጋ ቁጥር A70977-አአ ሚኒባስ መኪና የውስጥ አካል የተለያዩ የጦር መሳሪዎችንና ጥይቶችን ሰግስገውና ደብቀው መዳረሻቸውን ምዕራብ ኦሮሚያ አድርገው በደሴ በኩል አዲስ አበባ ሊገቡ ሲሉ ለገጣፎ ላይ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጿል።
በተመሳሳይ አርጆ አለማየሁ ዋቆ የተባለች የሸኔ ቡድን አባል ሶላር የተገጠመላቸው ዓለምአቀፍ የሳተላይት ስልኮችን በሞያሌ በኩል በማስገባት ወደ ተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በድብቅ ለማሰራጨት ስትሞከር ቡራዩ ከታ ላይ እጅ ከፍንጅ መያዟን የጠቆመው የጋራ ግብረ ኃይሉ መግለጫ፤ ራቢራ ዊርቱ ሞሲሳ፣ ደረጄ ዱጋሳ ሆርዶፋ እና ወንደሰን መግራ ታደሰ የተባሉ ሌሎች የሽብር ቡድኑ አባላትም ተጨማሪ የሳተላይት ስልኮችን ከአዳማ ወደ አዲስ አበባ ለማስገባት ሲሞክሩ፤በነበረው ሚስጥራዊ ክትትል በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቅሷል፡፡
ሸብርተኛው የሸኔ ቡድን በተደራጀና በተጠና መንገድ ግድያ እንዲፈፅሙ አዲስ አበባና በአንድ አንድ የኦሮሚያ ከተሞች ያሰማራቸው የአባ ቶርቤ ቡድን አባላት ተመሳስለው ጥቃት የሚፈፅሙባቸው የመከላከያ ሰራዊት የቀድሞው ደንብ ልብሶችንና እና የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችንም ጭምር በድብቅ ሲጓጓዙ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን መግለጫው አትቷል። አበራ ሙለታ፣ለሊሳ አዳሙ፣ አበራ ጌታ፣ሙሌ ስዩሜና አብርሃም አቡ የተባሉ የቡድኑ አባሎችና የድርጊቱ ተዋናዮች እንዲሁም አሽከርካሪውና ረዳቱም መያዛቸውን መግለጫው ጠቁሟል፡፡
የሽብር ቡድኑ በጅማ ከተማ ጥቃት ለመፈጸም ስምሪት የሰጣቸው ኢያሱ ለማ፣ካሊድ ሰይድ፣አብደላ አባ በላይ፣ሰይፉ በላይ እና ነጋሳ ኬኔሳ የተባሉ ተጠርጣሪዎችም ከታጠቋቸው የእጅ ቦንቦችና እና ሽጉጦች እንዲሁም ከሌሎች የጥፋት ተልዕኮ መፈጸሚያ ቁሶች ጋር መያዛቸውን መግለጫው አመልክቷል፡፡
በተለያዩ የውጭ ሀገራት የሚኖሩና ለአሸባሪው የሸኔ ቡድን የፋይናንስና የሎጀስቲክስ ድጋፎች የሚያደርጉ ኢትዮጵያዊያንና ትውልድ ኢትዮጵያዊያን መኖራቸውን ያመለከተው የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል መግለጫ፤ እነርሱም ጀምበሩና አበበ አሜሪካ፤ ገመቹ
፣አብደላ እና ተርፋ አውስትራሊያ ዱጋሳ ኖርዌይ እንዲሁም ቶለሸ ታምሩ ወይንም ገቢሴ፣ገመቹ አቦዬ፣ለማ ረጋሳ ወይንም ቢቂላ እና ጃራ ቱለማ ኬንያ የሚኖሩ መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡ እነዚህን የሽብር ቡድኑን እንቅስቃሴ እየደገፉ ያሉትን በድምሩ 15 ተጠርጣሪዎችን ማንነትን በማጣራትም ለህግ ለማቅረብ ከወዳጅ ሀገራት ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልጿል፡፡ በሀገር ውስጥ እስካሁን የቡድኑን የሽብር እንቅስቃሴ ለመግታት በተወሰደው እርምጃ የከተማ ሴል አባላትን ጨምሮ 71 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ብሏል፡፡
መግለጫው አክሎም፤ ለሽብር ቡድኑ የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩ የ80 ተጠርጣሪ ግለሰቦች የፋይናንስ ስርዓት እንዲቋረጥ የተደረገ መሆኑን እያሳወቀ፤ከዚሁ ጋር በተያያዘ የቡድኑ ዋና ዋና የገንዘብ አስተላላፊ ተብለው የተጠረጠሩ 6 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ሌሎችንም በህግ ተጠያቂ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን አመልክቷል፡፡
ከአሸባሪው የሸኔ ቡድንና ከሌሎች ፀረ-ሰላም ሃይሎች ጋር በመቀናጀት ሀገር የማፍረስ ተልዕኮ ይዞ ሲንቀሳቀስ የነበረው የሽብርተኛው የሕወሓት ቡድን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ አባላት ላይ የፈፀመውን የሀገር ክህደት ወንጀል ተከትሎ፤ መንግስት በወሰደው የህግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻ የቡድኑ ቁልፍ አመራሮች እርምጃ ሲወሰድባቸውና ገሚሶች ደግሞ እጃቸውን በሰላማዊ መንገድ ሲሰጡ፤ ጥቂት የታጠቁ የቡድኑ ሃይሎች በተንጠባጠበ መልኩ በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች እንደሚንቀሳቀሱ የገለፀው የጋራ ግብረ ኃይሉ፤ቡድኑ የተወሰደበትን ተከታታይ እርምጃ መቋቋም ባለመቻሉ ‹‹ክብሪት›› የሚል መጠሪያ የሰጠውን ገዳይ ቡድን በክልሉ ዋና ዋና ከተሞችና በአዲስ አበባም ጭምር ለማሰማራት መሞከሩን አትቷል፡፡
በአሜሪካ የሚኖሩ ጀነራል ፍስሃ ማንጁስ ፣ካህሳይና ወዲ ምጉላት የተባሉ ግለሰቦች፣ በሆላንድ የሚኖሩ ተክላይ እና አታክልቲ፣ እንግሊዝ የሚኖረው ታከለ፣ ስዊድንና ደቡብ ሱዳን የሚኖሩት ተስፋይ ንጉስና ሰይፈ አምባዬ የተባሉ ተጠርጣሪዎች ሽብርተኛውን የሕወሓት ቡድን በገንዘብ የሚደግፉ መሆናቸው በማስረጃ የተረጋገጠ መሆኑን የገለፀው የጋራ ግብረ ኃይሉ፤ግለሰቦቹን በህግ ተጠያቂ የማድረግ እንቅስቃሴ
መጀመሩንም አስታውቋል።
በሀገር ውስጥ ሆነው ለቡድኑ የገንዘብና የሎጀስቲክስ ድጋፎችን ሲያደርጉ የነበሩ 32 የቡድኑ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም አመልክቷል፡፡ በቡድኑ ለሽብር ድርጊቱ ሊውሉ የነበሩ የቡድንና የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎች፣የሬድዮ መገናኛዎች እና ሌሎች ተቀጣጣይ ቁሶችም መያዛቸውን ጠቁሟል፡፡
እነዚህ ሽብርተኛ ቡድኖች ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳቸውን ለማሳካት ሀገሪቱን ወደ ሽብርና ትርምስ ውስጥ በማስገባት የህዝቡን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል ሴራ ወጥነው ለመንቀሳቀስ እየሞከሩ ቢሆንም፤ የደህንነትና የፀጥታ አካላት ከህዝቡ ጋር በቅንጅት በመስራት ሴራቸውን አስቀድሞ ማክሸፍ መቻሉን የጋራ ግብረ ኃይሉ ገልጿል።
የሸኔና የህወሓት ሽብርተኛ ቡድን አባላት በመንግስት ጸጥታ ኃይሎች እየተወሰደባቸው ባለው ተከታታይ እርምጃ በርካታ የቡድኑ አባላት መደምሰሳቸውንና መያዛቸውን እንዲሁም ለሽብር ተልዕኳቸው
የሚጠቀሙባቸው የተለያዩ የጦር መሣሪያዎች፣የእጅ ቦንቦች፣ለፍንዳታ ስራ የሚውሉ ተቀጣጣይ ቁሶችና ሰነዶች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቋል። ይህን ተከትሎም የሽብር ቡድኖቹ ከፍተኛ ኪሳራና የስነልቦና ጫና ውስጥ መግባታቸውን መግለጫው አመልክቷል፡፡
የጋራ ግብረ ኃይሉ የውስጥና የውጭ ጸረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ተቀናጅተው ሀገሪቱን ወደ ለየለት ትርምስ ለመክተትና ለማፍረስ እየሰሩ ቢሆንም፤ በርካታ ሴራዎችን አስቀድሞ በማወቅ ማክሸፍ መቻሉንና የትኛውም ሴራ ከመንግስት እንዲሁም ከደህንነትና ጸጥታ አካላት እይታ የተሰወረ አለመሆኑንም ገልጿል።
ኢትዮጵያ በያዝነው ወር መጨረሻ ላይ ሀገራዊ ምርጫ ለማከናወን እንዲሁም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ለማካሄድ ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገች ባለችበት በአሁኑ ጊዜ በአንድ አንድ የውጭ ሀይሎች በቀጥታ ከሚደርስባት ጫና ባሻገር፤ ከተመቻቸው በጥቂት ተላላኪዎቻቸው የሸኔና የህወሓት ሽብርተኛ ቡድኖች ጥቃት በመሰንዘር ካልተመቻቸው በህቡዕ የተለያዩ አጀንዳዎችን በመፍጠር ሀገሪቱ ወደትርምስ እንድትገባ የተለያዩ እኩይ ሴራዎች እየተጠነሰሱ መሆናቸውን ህዝባችን ሊገነዘብ ይገባል ብሏል የጋራ ግብረ ኃይሉ በመግለጫው፡፡
በመሆኑም ህዝባችን፤ሰላሙንና ደህንነቱን ለመጠበቅ እንዲሁም የሀገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም ለማረጋገጥ ሴራዎቹን በማክሸፍ ለአፍታም አይን በማያስከድን ስራ ላይ የተሰማሩ የመረጃና ደህንነት እንዲሁም የጸጥታ ተቋማትና አካላትን የተቀናጀ እንቅስቃሴ በመደገፍ እያደረገ ላለው ትብብር የጋራ ግብረ ኃይሉ ላቅ ያለ ምስጋናውን ያቀርባል፡፡ ተመሳሳይ ሀገር የማፍረስ እኩይ ሴራዎችን በማክሸፍ በኩል እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን በቀጣይ ለህዝቡ የማሳወቅ ስራው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን መግለጫው አረጋግጧል፡፡
የፌደራል የደኅንነትና የጸጥታ የጋራ ግብረ ኃይል እና የኦሮሚያ ፀጥታ ተቋማት ፡
ግንቦት 2፣ 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ
Previous articleበምርጫ ሂደቱ ሊከሰቱ የሚችሉ የጸጥታ ችግሮችን በመለየት እርምጃ እየወሰደ መሆኑን መንግሥት አስታወቀ፡፡
Next article“ለሌላው መኖር ለምን ተሳነን”