
በምርጫ ሂደቱ ሊከሰቱ የሚችሉ የጸጥታ ችግሮችን በመለየት እርምጃ እየወሰደ መሆኑን መንግሥት አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 02/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማእከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋለው የጸጥታ ችግር በምርጫ እንቅስቃሴው ላይ እንከን መፍጠሩን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መንግሥት የምርጫውን ሰላምና ጸጥታ ማረጋገጥ ዋንኛ ትኩረት አድርጎ እንዲሠራ ሲጠይቅ መቆየቱንም አስታውሰዋል።
በአንዳንድ አካባቢዎች ያለው የጸጥታ ችግር የምርጫ ቁሳቁሶችን ወደ ምርጫ ጣቢያዎች የማጓጓዝ፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች በነፃነት ተንቀሳቅሰው ለመሥራት እንቅፋት ፈጥሮ መቆየቱን ተናግረዋል። በመሆኑም መንግሥት ከቦርዱ ጋር በመነጋገር የጸጥታ ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ በጋራ እየሠሩ መሆኑን ዶክተር ቢቂላ ገልጸዋል።
በጸጥታ ችግር ምክንያት የመራጮች ምዝገባ ባልተጀመረባቸው አካባቢዎች የምርጫ አስፈጻሚዎች ስልጠና እየተሰጠ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ዜጎች በምርጫው ላይ ያለጸጥታ ስጋት ተሳትፎ እንዲያደርጉ መንግሥት ሰላምና ጸጥታ ማስከበር ሥራውን በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በ2013 ዓ.ም ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ይካሄዳል ተብሎ ይፋ ከተደረገበት ጊዜ አንስቶ መንግሥት ሀገራዊ እቅድ አውጥቶ እየሠራ ነው ብለዋል።
በዚህ ረገድም የፖሊስና ደኅንነት ተቋማትን ያቀፈ ብሔራዊ የደኅንነት ግብረ ኃይል ተቋቁሞ በቅድመ ምርጫ ሂደት ሊከሰቱ የሚችሉ የጸጥታ ችግሮችን በመለየት እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በምርጫ ዕለትና ከምርጫው በኋላ የግጭት መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉ ሁኔታዎችን የመለየትና የመተንተን ሥራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል።
በሌላ በኩል ዓለም አቀፍ ተቋማት ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ቢታዘቡ መልካም እንደሆነ የገለጹት ዶክተር ቢቂላ የታዛቢዎቹ መቅረት በምርጫው ሂደት ላይ የሚያሳድረው ጉዳት እንደማይኖር ተናግረዋል።
ምርጫው ስኬታማ እንዲሆን የሚያደርገው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንጂ ሌላ የውጭ አካል አይደለምም ነው ያሉት።
ምርጫው ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡም ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ የጸጥታ ችግር ባለባቸው ቦታዎች ልዩ እቅድ እና ዝግጅት በማድረግ ከየክልሎቹ የጸጥታ ተቋማት ጋር በትብብር እየሠራ እንደሚገኝ ገልጿል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ