አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማላመድ እና በመጠቀም የኅብረተሰቡን ችግር በመፍታት ረገድ እየሠራ መሆኑን የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ገለጸ፡፡

141
አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማላመድ እና በመጠቀም የኅብረተሰቡን ችግር በመፍታት ረገድ እየሠራ መሆኑን የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 02 /2013 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ “የሳይንስና ቴክኖሎጂ እድገት ለዘላቂ ልማት” በሚል መሪ ሃሳብ የምርምር ጉባኤ እያካሄደ ነው። በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ተቋም አዘጋጅነት ለሁለተኛ ጊዜ እየተካሄደ ያለው የምርምር ጉባኤ ችግር ፈቺ በሆኑ ምርምሮች ላይ ያተኮረ መሆኑን የተቋሙ ዳይሬክተር አበበ ተስፋሁን (ዶክተር) ተናግረዋል።
የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ተቋም ከተቋቋመ አጭር ጊዜ ያስቆጠረ መሆኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ የኅብረተሰቡን ጉልበት ሊቆጥቡ የሚችሉ የበቆሎ መፈልፈያ፣ የማጨጃ እና መውቂያ ማሽኖችን አምርቶ ለዞኑ ቴክኒክና ሙያ ልማት ኢንተርፕራይዞች ማሸጋገሩንም ገልፀዋል።
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ደረጀ እንግዳ (ዶክተር) እንዳሉት የምርምር ጉባኤዎች የምርምር ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎች ልምዳቸውን የሚጋሩበት ነው። ልምዳቸው ወደ ተግባር ለመቀየር እና የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ዩኒቨርሲቲዎች ከኢንዱስትሪዎች ጋር በጋራ መሥራት ይገባቸዋል ብለዋል።
ዘመኑ የሳይንስና ቴክኖጂ ወቅት በመሆኑ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማላመድ በጤና፣ በግብርና እና በትምሕርት ዘርፍ በመጠቀም የኅብረተሰቡን ችግር መፍታት ይገባል ያሉት ደግሞ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ታፈረ መላኩ (ዶክተር) ናቸው። በምርምር ጉባኤው ላይ የሚቀርቡት የምርምር ሥራዎች በሀገሪቱ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እና የምርምር ተቋማት የተመረጡ፣ በተግባራዊ ምርምር ላይ ያተኮሩ እና የኅብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ ፣ በአጭር ጊዜ ወደ ሥራ ሊገቡ የሚችሉ የምርምር ሥራዎች መሆናቸውንም ነው ፕሬዝዳንቱ የተናገሩት።
በጉባኤው ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት ተመራማሪዎችም የምርምር ጉባኤ መካሄዱ ለወደፊት ለሚያካሂዷቸው ጥናቶች ግብዓት የሚያገኙበት እና ሥራቸውም ወደ ተግባር እንዲለወጥ በር የሚከፍትላቸው መሆኑን ገልጸዋል። የምርምር ጉባኤው ለኹለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን በተግባራዊ ምርምር ላይ ያተኮሩ እና የኅብረተሰቡን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ ከ20 በላይ ምርምሮች ይቀርባሉ ተብሎም ይጠበቃል።
ዘጋቢ፦ አማረ ሊቁ – ከደብረ ማርቆስ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበአጣዬ ከተማ የወደሙ ቤቶችን መልሶ ለመገንባት የመዋቅራዊ ፕላን ጥናት እየተሠራ መኾኑን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ፡፡
Next articleበምርጫ ሂደቱ ሊከሰቱ የሚችሉ የጸጥታ ችግሮችን በመለየት እርምጃ እየወሰደ መሆኑን መንግሥት አስታወቀ፡፡