በአጣዬ ከተማ የወደሙ ቤቶችን መልሶ ለመገንባት የመዋቅራዊ ፕላን ጥናት እየተሠራ መኾኑን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

129
በአጣዬ ከተማ የወደሙ ቤቶችን መልሶ ለመገንባት የመዋቅራዊ ፕላን ጥናት እየተሠራ መኾኑን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 02 /2013 ዓ.ም (አሚኮ) ከአጣዬና አካባቢው የተፈናቀሉ ወገኖችን በዘላቂነት ማቋቋም የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ መኾኑን የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር አስውቋል፡፡ በአጣዬና አካባቢው በተፈጸመ የተደራጀ ጥቃት የተፈናቀሉ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም በዞኑ ዋና አስተዳዳሪ የሚመራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሀብት የማሰባሰብ ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡ መንግሥታዊ፣ መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት እና ልዩልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችም ድጋፍ ለማድረግ ርብርብ እያደረጉ ነው ተብሏል፡፡
ከዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የተገኘ መረጃ እንደሚያመላክተው ተፈናቃዮችን ወደ አካባቢያቸው ለመመለስ እና በዘላቂነት ለማቋቋም በሚያስችል መልኩ እየተሠራ ነው፡፡ ለዚህም በተደራጀና በታቀደ መልኩ በተፈጸመው ጥቃት የወደመና የተቃጠለ ቤት፣ ሀብትና ንብረት መጠን ምን ያህል እንደኾነ ለመለየት ጥናት ተጀምሯል፡፡ የቤት ግንባታን ጨምሮ በዘላቂነት ለማቋቋም ምን ያህል ሀብት እንደሚያስፈልግም መሀንዲሶች እና የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት የተካተቱበት ቡድን ጥናት እያካሄደ ነው፡፡
በተለይ በአጣዬ ከተማ የወደሙ ቤቶችን መልሶ ለመገንባትም የመዋቅራዊ ፕላን ጥናት እየተጠናቀቀ መኾኑንም የጽሕፈት ቤቱ ኀላፊ ወርቃለማሁ ኮስትሬ አስታውቀዋል፡፡ ጅምር እንቅስቃሴው በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ እንዲኾን አካባቢያቸውን ጥለው የሄዱ ሰዎች ወደቀያቸው ተመልሰው ሂደቱን መከታተል፣ ማገዝ፣ ግንባታው የሚጀመር ከሆነም የሀብታቸውን መጠን ጨምሮ አስፈላጊ መረጃዎችን ለባለሙያዎች መስጠት እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በአጣዬና አካባቢዋ ያለው ሁኔታ ወደ ሰላም መመለሱን ከግምት ውስጥ በማስገባት የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ጥሪ አድርጓል። ይህንን ተከትሎም ሰዎች ወደ አካባቢያቸው እየተመለሱ ነው ብለዋል አቶ ወርቃለማሁ፡፡ ወደቀያቸው መመለሳቸውም መልሶ ለማቋቋምና ቤት ለመገንባት ሂደቱ ወሳኝ መኾኑን ጠቅሰዋል።
በአጣዬና አካባቢው በተፈጸመ የተደራጀ ጥቃት ሰዎች አካባቢያቸውን ጥለው ከሸሹበት ጊዜ ጀምሮ መንግሥት አስፈላጊ የድጋፍ አይነቶችን በመለየት የእለት ደራሽ ድጋፍ እያደረገ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡ የየአካባቢው ነዋሪዎች እና ልዩልዩ አደረጃጀቶችም የተለያዩ ድጋፎችን ማቅረባቸውን እና በዘላቂነት መልሶ በማቋቋም ጥረቱ ከፍተኛ ተሳትፎ እያደረጉ መኾኑን ነው አቶ ወርቃለማሁ የተናገሩት፡፡ ይሁን እንጂ የሚደረገው ዕለታዊ ድጋፍ ሁሉንም የድጋፍ አይነቶች ያካተተ አለመኾኑ በክፍተት ተነስቷል። የተፈናቃዮች የቤተሰብ ቁጥር በትክክል አለመታወቁም በፍትሐዊነት ሀብት ለማከፋፈል ፈተና እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ችግሮችን በመለዬት ለማስተካከል እየተሠራ እንደሆነ ጠቅሰዋል። በተለይ ጥሪውን ተከትሎ ሰዎች ወደ አካባቢያቸው የሚመለሱ ከሆነ የተጠቀሱትን ችግሮች ለመፍታት ምቹ መደላድል እንደሚፈጠር የጽሕፈት ቤት ኀላፊው አረጋግጠዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“ምርጫው የተሳካ እንዲሆን ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት” ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር
Next articleአዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማላመድ እና በመጠቀም የኅብረተሰቡን ችግር በመፍታት ረገድ እየሠራ መሆኑን የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ገለጸ፡፡