ፈረንሳይ በቅርስ ጥበቃና ልማት እንዲሁም በከተሞች መሠረተ ልማት ዝርጋታ ዘርፎች በአማራ ክልል እያደረገች ያለውን ድጋፍ አጠናክራ እንድትቀጥል ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር ጠየቁ፡፡

113
ፈረንሳይ በቅርስ ጥበቃና ልማት እንዲሁም በከተሞች መሠረተ ልማት ዝርጋታ ዘርፎች በአማራ ክልል እያደረገች ያለውን ድጋፍ አጠናክራ እንድትቀጥል ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር ጠየቁ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 02/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ ጋር ተወያይተዋል።
ኢትዮጵያ ከፈረንሳይ ጋር ያላትን ከ100 ዓመታት በላይ የዘለቀ የዳበረ ወዳጅነትን ለማስቀጠል በምታደርገው ጥረት ፈረንሳይ በአማራ ክልል የተለያዩ የፕሮጀክት ድጋፍ እያደረገች መሆኗ በውይይቱ ተነስቷል።
ፈረንሳይ በቅርስ ጥበቃና ልማት እንዲሁም በከተሞች መሠረተ ልማት ዝርጋታ ዘርፎች በአማራ ክልል እያደረገች ያለውን ድጋፍ አጠናክራ እንድትቀጥል ርእሰ መሥተዳድሩ ጠይቀዋል።
በአመራር ጥበብ ዙሪያ ፈረንሳይ ለክልሉ ስልጠናዎችን እንድታመቻችም በውይይታቸው አንስተዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር ስለ ስደስተኛው ሀገራዊ አጠቃላይ ምርጫ ለፈረንሳዩ አምባሳደር ማብራሪያ ሰጥተዋቸዋል።
በአማራ ክልል 18 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለመወዳደር ተመዝግበው የምረጡኝ ቅስቀሳ ላይ መሆናቸውን ገልጸውላቸዋል። የመራጮች ምዝገባ እየተከናወነ ነው፤ በምዝገባ ሂደቱ ያጋጠሙ የምርጫ ካርድ በፍጥነት አለመዳረስና ሌሎች ችግሮች በፍጥነት እንዲፈቱ እያደረግን መጥተናል፤ እስከ ምዝገባ ማጠናቀቂያ ጊዜውም ችግር እንዳያጋጥም ከምርጫ ቦርድ ጋር በትብብር እየሠራን ነው ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ።
የክልሉ መንግሥት ጤናማ የምርጫ ሂደት ተግባራዊ እንዲደረግ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ ስለመሆኑም አረጋግጠውላቸዋል።
በሰሜን ሸዋና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ሰፊ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ለአምባሳደሩ አብራርተውላቸዋል።
አማራ ክልል ሁሉም ኢትዮጵያዊ በነጻነት ተንቀሳቅሶ ሐብት ማፍራት የሚችልበት ሰላማዊ ክልል ነው፤ የአማራ ሕዝብም ከአጎራባች ክልል ሕዝቦች ጋር በወንድማማችነት የሚኖርና በትብብር የሚያምን መሆኑንም ርእሰ መሥተዳድሩ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ በበኩላቸው ፈረንሳይ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የረጅም ዓመታት ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ለማጠናከር እየሠራች ነው ብለዋል። በአማራ ክልልም በከተሞች መሰረተ ልማትና ሌሎች ዘርፎች ድጋፍ ለማድረግ ሀገራቸው ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠውላቸዋል።
ከተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ አማራዎች ድጋፍ እንዲያገኙም ጥረት እናደርጋለን ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያና ፈረንሳይ በወታደራዊ፣ በኢኮኖሚ፣ በባሕላዊና በሌሎች መስኮች ያላቸውን ትብብር አጠናክረው መቀጠላቸውም በውይይቱ ተገልጿል።
ፈረንሳይ የቅዱስ ላሊበላ አብያተ-ክርስቲያናትን ጥገና ለማድረግ እና ለማስተዋወቅ ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባቷ ይታወቃል፡፡
ዘጋቢ፡- ስማቸው እሸቴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየደባርቅ ዩኒቨርሲቲ በትምህርት ቤቶች የዲጅታል ቤተመጽሐፍት በማቋቋም የማጣቀሻ መጽሐፍትን ችግር ለመፍታት እየሠራ መሆኑን ገለጸ፡፡
Next article“ምርጫው የተሳካ እንዲሆን ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት” ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር