
የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ በትምህርት ቤቶች የዲጅታል ቤተመጽሐፍት በማቋቋም የማጣቀሻ መጽሐፍትን ችግር ለመፍታት እየሠራ መሆኑን ገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 02/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የዲጅታል ቤተመጽሐፍት ተጠቃሚ መሆናቸው መጽሐፍትን በቀላል መንገድ ለማግኘት እንዳስቻላቸው የአምባ ጊዮርጊስ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ አይሲቲ አሰልጣኝ ይንገስ ቢልልኝ ተናግረዋል። ኮሌጁ በተዘጋጁ ሞጁሎች ብቻ ሥልጠና ሲሰጥ ቆይቷል ያሉት አቶ ይንገሥ በዚህም ምክንያት ተማሪዎች ተጨማሪ መጽሐፍትን ለማጣቀሻነት ለመጠቀም ይቸገሩ እንደነበር አንስተዋል፡፡
ይሁን እንጅ ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የዲጅታል ቤተመጽሐፍት በማቋቋሙ ችግሩ መቃለሉን ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ለዚሁ ዓላማ የሚያገለግሉ 15 ኮምፒውተሮችን ለኮሌጁ ድጋፍ አድርጓል ብለዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ሰልጣኞች በእጅ ስልካቸው ጭምር በቀላል መንገድ መጠቀም መቻላቸውን ነው የነገሩን፡፡
የዲጅታል ቤተመጽሐፍት መቋቋሙ የወረቀት ፍጆታን አስቀርቷል፤ ጊዜን የመቆጠብ ሚናው የላቀ ነው ብለዋል፡፡ የተለያዩ ማጣቀሻ መጽሐፍትን ለማግኘት ማስቻሉንም አቶ ይንገሥ ገልጸዋል፡፡
የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የማኀበረሰብ አገልግሎት እና የኢንዱስትሪ ትስስር ዳይሬክተር አምባቸው ወረታው እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ከትምህርት ሥራ በተጨማሪ የማኅበረሰብ አቀፍ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛል።
በዞኑ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የሚታየውን የመጽሐፍ ችግር ለመፍታት በተያዘው ዓመት ከ4 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በ7 ወረዳዎች ለሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ ለከፍተኛ ትምህርት መሰናዶዎች እና ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች 14 የዲጂታል ቤተመጽሐፍት ማቋቋም ተችሏል፡፡
ለዚህም 175 ኮምፒውተሮችን ማሰራጨት መቻሉን ዳይሬክተሩ ነግረውናል፡፡ እያንዳንዱ ዲጅታል ቤተ መጽሐፍትም እስከ 90 ሺህ መጽሐፍትን እንደሚይዝም ነግረውናል፡፡ በድምጽ እና በምስል የተዘጋጁ የትምህርት አይነቶችንም ለመጠቀም ያስችላል ተብሏል፡፡ በ200 ሜትር ክልል ውስጥ በመሆን በኮምፒውተርም ሆነ በእጅ ስልክ መጠቀም ያስችላል፡፡ በኔትወርክ እና ያለኔትወርክ እንደሚሠራም ጠቁመዋል፡፡
ዲጅታል ቤተመጽሐፍቱ የመጽሐፍትን ብልሽት ያስቀራል፡፡ በየጊዜው ለህትመት የሚወጣውን ወጭ ያስቀራል፡፡ ተማሪዎች በሚመቻቸው ቦታ ሆነው በቀላሉ እንዲጠቀሙ ያስችላል፡፡ ወደ ፈለጉበት ቋንቋ በመተርጎም እንዲጠቀሙም ያደርጋል፡፡
በተለይም ደግሞ መጽሐፍትን ገዝተው መጠቀም ለማይችሉ ተማሪዎች ጥቅሙ የጎላ መሆኑን ዳይሬክተሩ አንስተዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ በሌሎች ትምህርት ቤቶች አገልግሎቱን እንደሚያሰፋና ሌሎች የማኅበረሰብ አገልግሎቶችንም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ