“የአውሮፓ ሕብረት በድህረ ምርጫ ከምርጫ ቦርድ በፊት መግለጫ መስጠት አለብኝ ብሎ ማቅረቡ የምርጫ ቦርድን ስልጣንና የሀገራችንን ሉዓላዊነት በእጅጉ የሚዳፈር ሆኖ አግኝተነዋል” የአማራ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የጋራ ምክር ቤቱ ዛሬ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ያደረገውን ውይይት አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል።

155

“የአውሮፓ ሕብረት በድህረ ምርጫ ከምርጫ ቦርድ በፊት መግለጫ መስጠት አለብኝ ብሎ ማቅረቡ የምርጫ ቦርድን ስልጣንና
የሀገራችንን ሉዓላዊነት በእጅጉ የሚዳፈር ሆኖ አግኝተነዋል” የአማራ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት
የጋራ ምክር ቤቱ ዛሬ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ያደረገውን ውይይት አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል።
የመግለጫው መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል።
6ኛውን ሃገራዊና ክልላዊ ምርጫ ታሳቢ በማድረግ በሀገራችን የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በሀገርና በክልል እንዲሁም ወደታች
እስከ ወረዳ ድረስ መመስረታቸው በየጊዜው በየደረጃው የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታትና በተከታዮቻችን ዘንድም እንደ ሀገርና
እንደ ክልል የተቀመጡ የምርጫ ግቦችን በጋራ ትግል ለማሳካት የማይተካ ድርሻ አላቸው፡፡
በዚህ እምነታችን መሰረት በአማራ ክልል የምንገኝ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሚያዝያ 16/2013 ዓ.ም ገዥውን ፓርቲ
ጨምሮ በክልሉ በምንቀሳቀስ 9 ፓርቲዎች ተወያይተን በተስማማንበት መሰረት መቋቋሙ ይታወቃል፡፡
በጋራ ምክር ቤቱ ሕገ ደንብ መሰረት በየ15 ቀኑ መደበኛ ስብሰባ አድርገን መወያየት ስለሚገባን ሚያዝያ 30/2013 በተለያዩ
አጀንዳዎች ላይ ውይይት አድርገን የሚከተለውን ባለ 4 ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተናል፡፡
በክልላችን የዲሞክራሲ ምህዳሩን በማስፋትና ሁሉም ፓርቲዎች በነፃነት እንዲቀሰቅሱ፤ በምርጫም እንዲሳተፉ የክልሉ
መንግሥትና በገዥው ፓርቲ በኩል ያለው መሻሻልና ተስፋ ሰጭ ጅምር እንዲሁም አንፃራዊ ዴሞክራሲያዊነት እስካሁን ባለው
ሁኔታ በውይይታችን እውቅና የሰጠነውና የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው፡፡ ይህ ጅምር ጥንካሬ እንዳለ ሆኖ ደግሞ
በሁሉም ፓርቲዎች ዘንድ በሚባል ሁኔታ በየምርጫ ክልሉ እና በጣቢያ ደረጃ በታችኛው የሁሉም ፓርቲዎች መዋቅር በማወቅም
ሆነ ባለማወቅ የሚፈፀሙ አሁን ላይ ጥቃቅን የሚመስሉ ነገር ግን በዚህ ከቀጠሉ የምርጫውን ዴሞክራሲያዊነት ላይ አሉታዊ
ጥላ ሊያጠሉ የሚችሉ ለአብነት ባለተፈቀዱ ቦታዎች እንደ ገበያና የእምነት ተቋማት የመሳሰሉት ላይ የምርጫ ቅስቀሳ ማካሄድ፣
የምርጫ ምልክቶችን መቅደድ ወይም ማንሳት/ማስነሳት፣ በጥቂት አካባቢዎች በተለያዩ ሰበቦች ፓርቲዎች ቅስቀሳ እንዳያደርጉ
ለመከልከል መሞከር ወዘተ የመሳሰሉትን በዝርዘር የገመገምን ሲሆን ሁሉም ፓርቲዎች የታችኛውን መዋቅራቸውን እንዲፈትሹና
እንዲያስተካክሉ፤ በብልጽግና ፓርቲ በኩልም እንደ መንግሥትና እንደ ፓርቲ ተደራራቢ ኃላፊነቱን ካሁኑ በላቀ ንፅህና እንዲፈፅምና
በክልላችን የመጀመሪያውን ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ እንድንችል ሁላችንም የተጣለብንን ታሪካዊ ኃላፊነት
ለመወጣት ለሕዝባችን ቃል እንገባለን፡፡
በሀገርና በክልል ደረጃ የተቀመጠውን የምርጫ ግብ ለማሳካት ከሁሉም በላይ ደግሞ አሳታፊነትን ለማረጋገጥ በክልላችን
የሚገኝ የመራጭነት መስፈርት የሚያሟላ ዜጋ ሁሉ በምርጫው መሳተፍ ሲችል ነው፡፡ ከዚህ አኳያ በክልላችን የመራጮች
ምዝገባ በሚፈለገው መጠን እየሄደ አለመሆኑን ተረድተናል፡፡ ስለዚህ ካሁን በፊት በመንግሥት በኩል ሕዝቡን በመቀስቀስና
ምርጫ ቦርድን በመደገፍ የተደረጉ ጥረቶችን እያደነቅን ካሁን በኋላ በምርጫ ቦርድ በተጨመሩ ጥቂት ቀናት መንግሥትና እኛ
የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ሕዝቡ በመውረድ አስፈላጊውን ሁሉ ሕዝብን የማንቃትና በመራጭነት እንዲመዘገብ የመቀስቀስ ሥራ
ለመስራት ቃል እየገባን ምርጫ ቦርድም በተደጋጋሚ በተለይ ከምርጫ አስፈፃሚዎች በተለያዩ ምክንያቶች በምርጫ ጣቢያ
አለመገኘትና ሌሎች ኅብረተሰቡን ሊያጉላሉ ከሚችሉ ችግሮች ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ድጋፍና ክትትል በማድረግ የላቀ አገልግሎት
እንዲሰጥ ጥሪ እያስተላለፍን እኛም ከቦርዱ ጎን በመቆም ለጋራ ስራ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናችንን
እናረጋግጣለን፡፡
ባለፈው 15 ቀን በነበረው የምክር ቤቱ መመስረቻ ስብሰባ ለሁሉም ፓርቲ እኩል መልዕክት በምርጫ ቦርድ በኩል የተላለፈ
ቢሆንም፤ በአንዳንድ ወገኖቻችን ሁኔታውን ባልተገባ መንገድ የአንዳንድ ፓርቲዎችን ስም በማንሳት ጥሪ እንዳልተደረገ አስመስሎ
መጠቀሚያ ለማድረግ የነበረውን ሙከራ እያወገዝን በዛሬው ውይይት ካሁን በፊት ካልተሳተፉት ውስጥ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ/
አብን/ ተገኝቶ የአባልነት ፊርማ ማስቀመጡን እያደነቅን ሌሎች እስካሁን የምክር ቤቱ አባል ያልሆኑ በክልላችን የሚንቀሳቀሱ
ፓርቲዎችም በራችን ዘወትር ክፍት በመሆኑ አሁንም አባል እንዲሆኑ ጥሪያንን እናስተላልፋለን፡፡
ለአንድ ሀገር ምርጫ ዴሞክራሲያዊነት የውጭና የሀገር ውስጥ ታዛቢዎች ሚና ትልቅ እንደሆነ እንረዳለን፤ በ6ኛው ሀገራዊና
ክልላዊ ምርጫ የተሟላ የታዛቢዎች ሽፋን እንዲኖርም ፍላጎታችን ከፍተኛ ነው፡፡ በዚህ ረገድ መንግሥት ያሉ አማራጭ እድሎችን
ሁሉ እንዲጠቀምም ግፊት እናደርጋለን፡፡ ነገር ግን ሰሞኑን የአውሮፓ ሕብረት ወደ ሀገራችን ገብቶ ለመታዘብ እንደማይችል
የገለፀበት መንገድ አነስተን የተወያየን ሲሆን የአውሮፓ ሕብረት በሀገራችን ካሁን በፊት በተደረጉ ነገር ግን በተግባር ሲታዩ
የይስሙላ የነበሩ፤ ሥርዓቱም የአፈና በነበረበትና ሀገራችን ተስፋ ባጣችበት ሰዓት አሁን ያስቀመጠውን ቅድመ ሁኔታ ሳያስቀምጥ
ያለማንገራገር ወደ ሀገር ገብቶ ታዝቦ እያለ አሁን በአንፃራዊነት የተሻለ የምርጫና የዴሞክራሲ ድባብ ባለበት ሁኔታ አልታዘብም
ማለቱ ሌላ ተጨማሪ የፖለቲካ ፍላጎት ያለው ስለሚያስመስል የአውሮፓ ሕብረት ምርጫውን ለመታዘብ ሌላ ተጨማሪ
የኮምዩኒኬሽን መሣሪያ መጠቀም ይፈቀድልኝ የሚለው ከሀገር ሉዓላዊነትና ነፃነት ጋር ይጋጫል ብለን ስለምናምን ሕብረቱ
በድህረ ምርጫ ከምርጫ ቦርድ በፊት መግለጫ መስጠት አለብኝ ብሎ ያቀረበውም የምርጫ ቦርድን ስልጣንና የሀገራችንን
ሉዓላዊነት በእጅጉ የሚዳፈር ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ በመሆኑም በነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ላይ መንግሥትና ምርጫ ቦርድ የወሰዱትን
አቋም እያደነቅን የአውሮፓ ሕብረት ያቀረባቸውን ያልተገቡ ቅድመ ሁኔታዎች በማስተካከል የሀገራችን መንግሥትና ምርጫ ቦርድ
ባስቀመጡትና ሌሎችም በሚገዙበት መስፈርት ገብቶ በክልላችንም ምርጫችንን እንዲታዘብ ጥሪ እያቀረብንን በዚሁ ጉዳይ
መንግሥት የያዘውን አቋም የምንደግፍ መሆኑን እናረጋግጣለን፡፡
የ6ኛውን ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ግብ በማሳካት ለሕዝባችን ታሪክ እንሠራለን!!
የአማራ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት
ሚያዝያ 30/2013 ዓ.ም
ባሕር ዳር

Previous articleለ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በመራጮች ምዝገባ ሂደት ለሚያጋጥሙ ችግሮች መፍትሔ እየሰጠ መሆኑን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገለጸ።
Next articleቺርቤዋ ማንዚ 30 ጌርክ 2013 ም. አ(አሚኮ)