የወቅቱ የዝናብ ሁኔታ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ውኃ ሙሌት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር የዘርፉ ምሁር ገለጹ፡፡

161

የወቅቱ የዝናብ ሁኔታ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ውኃ ሙሌት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር የዘርፉ ምሁር ገለጹ፡፡
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 30/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፈው 2012 ዓ.ም ሐምሌ ወር ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የኢትዮጵያ
ታላቁ የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውኃ ሙሌት የመጠናቀቁ ብስራት ተከትሎ የኢትዮጵያውያን እና ወዳጆች ልብ በሀሴት
የሞላ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
በዘንድሮው የክረምት ወቅትም ኢትዮጵያዊ ሁሉ እንደ ዓይኑ ብሌን የሚመለከተው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀት ታላቅ ኹነትን
ያስተናግዳል፡፡ ኢትዮጵያ የክረምቱ ወቅት መግባቱን ተከትሎ የሁለተኛ ዙር ውኃ ሙሌት ዝግጅት እያደረገች ነው፡፡
የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ስለሺ በቀለ የህዳሴ ግድቡን 10ኛ ዓመት በማስመልከት በሰጡት መግለጫ በቀጣዩ
ክረምት ቀጠሮ የተያዘለት ሁለተኛው ዙር የውኃ ሙሌት በምንም ዓይነት መልኩ እንደማይራዘም ገልጸዋል።
አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ያነጋገራቸው በአሜሪካ የውኃ ምህንድስና ባለሙያ ጥሩሰው አሰፋ (ዶክተር) እንደገለጹት በመጪው
ወቅት ያለው የአየር ንብረት እና የዝናብ ሁኔታ ኢትዮጵያ ላቀደችው የሁለተኛ ዙር የታላቁ የህዳሴ ግድብ ውኃ ሙሌት ምቹ ነው፡፡
ዶክተር ጥሩሰው በመጭው ክረምት ወራት ግድቡ ውኃ ለመያዝ የሚያስችለው ምቹ የአየር ትንበያ መኖሩን ገልጸዋል፡፡
የአሜሪካ ብሔራዊ የውቅያኖስና የከባቢ አየር አሥተዳደር እና የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ ምርምር ተቋም የአየር ንብረት
መረጃዎችን በዋቢነት የጠቀሱት ምሁሩ በምዕራብ ኢትዮጵያ እና ሱዳንን ጨምሮ እስካሁን በዚህ ወቅት እንኳን በአማካይ
ከሚገኘው ዝናብ ከ200 እስከ 400 በመቶ በላይ ዝናብ እያገኙ ነው፡፡
የቀጣይ ወራት የዝናብ ሁኔታ ትንበያ በተመለከተም ከአማካይ በላይ እንደሚሆን ትንበያዎች እንደሚያሳዩ ገልጸዋል፡፡ ይህ ደግሞ
ለኢትዮጵያ እቅድ ስኬት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል፡፡
የውኃ ሙሌቱ በግብጽ እና ሱዳን ላይ የሚያደርሰው ተጽዕኖ አለመኖሩንም ነው ዶክተር ጥሩሰው ያስረዱት፡፡ ባለፉት ዓመታት
በቀጣናው ይጥል በነበረው ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ በሱዳን በሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት
ማድረሱን ምሁሩ አንስተዋል፤ ሁለተኛው ዙር የህዳሴ ግድብ ውኃ ሙሌት በዘንድሮው የክረምት ወቅት ይህንን አይነት አደጋ
በመቀነስ ረገድ ለሱዳን የሚሠጠው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በወቅቱ በግብጽ ከፍተኛ ክምችት ያለው ውኃ ስለሚኖር የውኃ ሙሌቱ ተጽእኖ እንዳይኖረው ከሚያደረጉት ምክንያቶች አንዱ
መሆኑንም ዶክተር ጥሩሰው ገልጸዋል፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ባሳለፍነው ሐምሌ 2012 ዓ.ም ለመጀመሪያ ዙር የታቀደለትን 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር
ውኃ እንዲይዝ መደረጉ ይታወሳል፡፡
ዘጋቢ፡- የማነብርሃን ጌታቸው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleየባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር ሂሩት ካሳው (ዶክተር) ለፍቼ ጫምባላላ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ።
Next articleለ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በመራጮች ምዝገባ ሂደት ለሚያጋጥሙ ችግሮች መፍትሔ እየሰጠ መሆኑን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገለጸ።