የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር ሂሩት ካሳው (ዶክተር) ለፍቼ ጫምባላላ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ።

433

የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር ሂሩት ካሳው (ዶክተር) ለፍቼ ጫምባላላ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ።

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 30/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር ሂሩት ካሳው (ዶክተር) የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል ለሆነው የፍቼ ጫምባላላ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።

ሚኒስትሯ በመልእክታቸው “የሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ ፍቼ ጨምበላላ በዓል የሰብዓዊነት ጥግ የሚታይበት በዓል ነው፤ የሰብዓዊነት ጥጉ ራስን በሌሎች ጫማ ውስጥ መመልከት፣ መተባበር፣ መከባበር፣ በአብሮነት መኖር ፍቅር ደስታ እና ሰላም ነው” ብለዋል።

በእነዚህ መስፈሪያዎች ሲዳማ ሲሰፈር ሞልቶ ተትረፍርፎ የሚፈስ የመልካም እሴቶች ባለቤት ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ፍቼ ጫምባላላ በትውልድ መስተጋብር በዘመን ሠረገላ ተሸጋግሮ፣ በትውልድ ቅብብሎሽ ተጠብቆ፣ በሕዝቦች መካከል ሰንሰለት ሠርቶ፣ ያለፈውን ትውልድ አሁን ካለው ትውልድ ያገናኘ እንቁ የአብሮነታችን መገለጫ፣ የኩራታችን ምንጭ የሆነ ባህላዊ እሴታችን ነው ሲሉ ነው የገለጹት።

በዓሉ የሲዳማ ማኅበራዊ፣ ማኅበረሰባዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ መገለጫም እንደሆነም ገልጸዋል።

ሀገርን እንደ ምሰሶ ተሸክመው የቆሙ እንደዚህ ዓይነት በዓላት ሳይሸራረፉ ተጠብቀው ለሚቀጥለው ትውልድ ሊሸጋገሩ እንደሚገባ ጠቁመው፣ ሀገራችን ለጀመረችው አንድ ኢኮኖሚያዊ ማኅበረሰብ ግንባታ ማኅበረሰባዊ ትስስር ከመፍጠር አልፈው የኢኮኖሚ አማራጭ ሆነው መውጣት ይኖርባቸዋል ብለዋል።

ዓለም ስለእነዚህ በዓላት ግንዛቤ እንዲኖረው ተመራማሪዎች፣ የታሪክ ሰዎች እና ምሁራን ስለፍቼ ጫምባባላ ብዙ ጥናት እና ምርምር ሊያደርጉ እንደሚገባ ሂሩት ካሳው (ዶክተር) አሳስበዋል።

የሲዳማ ሽማግሌዎች የብሔሩን ታሪክን በመመርመር ከጥንት ዘመን ጀምሮ በሀገር ወረርሽኝ እና ተላላፊ በሽታ ሲከሰት፣ የጎሣ መሪዎች በሞት ሲለዩ በዓሉ ወደሚከበርበት ልዩ ስፍራ ‘ጉድማሌ’ ሳይወጣ የፍቼ ጫምባላላን በዓል ማክበር የነበረ የባህሉ እሴት እና ሥርዓት መሆኑን በመገንዘብ የኮሮናቫይረስ ሥርጭትን ለመገደብ ኅብረተሰቡ በዓሉን በየቤቱ እንዲያከብረው መወሰናቸው የሲዳማ ሽማግሌዎች የሄዱበት የማስተዋል ርቀት ክብር እና ዕውቅና ሊቸረው የሚገባ ሀገራዊ ኀላፊነትን የመወጣት በጎ እሳቤ መሆኑን ጠቅሰዋል። ዘገባው የኢብኮ ነው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous article“የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ምርጫዉን ለመታዘብ ዝግጅታቸውን አጠናቅቀዋል” አምባሳደር ዲና ሙፍቲ
Next articleየወቅቱ የዝናብ ሁኔታ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ውኃ ሙሌት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር የዘርፉ ምሁር ገለጹ፡፡