
“የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ምርጫዉን ለመታዘብ ዝግጅታቸውን አጠናቅቀዋል” አምባሳደር ዲና ሙፍቲ
ባሕር ዳር:ሚያዚያ 30/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸው በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር፣ በኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይ እንዲሁም በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ላይ ትኩረት አድርገዋል።
ኢትዮጵያ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ በምክንያታዊነትና በፍትሐዊነት በጋራ የመጠቀም መብት አክብራ እየሰራች እንደሆነ ገልጸዋል። ከዓባይ ውኃ 86 ከመቶ በላይ የምታመነጭ ሀገር በቅኝ ግዛት ዘመን በተደረጉ ስምምነቶች አሁንም ኢትዮጵያን ባገለለ መልኩ የመጠቀም ተግባር ተቀባይነት የሌለዉ መሆኑን ኢትዮጵያ ስትገልጽ መቆየቷን አስታውሰዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የታችኛዉ ተፋሰስ ሀገራት በማይጎዳ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን አምባሳደር ዲና ተናግረዋል።
አምባሳደር ዲና ኢትዮጲያ ከመጀመሪያው የውኃ ሙሌት ጀምሮ መረጃ ለመለዋወጥ ያላትን ፍቃደኛነት መግለጿን አስታውሰዋል። አሁንም ሀገራቱ ባለሙያዎችን በመሰየም የሁለተኛው ዙር የግድቡን የውኃ ሙሌትን በተመለከተ አስፈላጊው መረጃ መለዋወጥ እንዲቻል ያላትን ፍላጎት ቀደም ብሎ በይፋ ማሳወቋን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ “ለአፍሪካዊ ችግሮች፤ አፍሪካዊ መፍትሔ” በሚለው መርህ በአፍሪካ ሕብረት አስተባባሪነት የሦስትዮሽ ድርድሩ እንዲቀጥል ያላትን ፍላጓት በተለያየ መንገዶች እየገለጸች መሆኑን ጠቅሰዋል።
በሱዳንና ግብጽ በኩል ግን ጉዳዩ ዓለምአቀፋዊ ይዘት እንዲኖረዉ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል። ይህም ኢትዮጵያ ከምትከተለው መርህ ውጭ መሆኑን አመልክተዋል።
የግድቡ ግንባታ ሂደት እና ሁለተኛው ዙር የውኃ ሙሌት በታቀደለት ጊዜ እንደሚከናወን አስታውቀዋል።
የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይን በተመለከተ በመሪዎች እንዲሁም በጋራ የድንበር ኮሚቴዎች ደረጃ በተለያየ ጊዜ ውይይቶች ሲያደርጉ መቆየታቸዉን አስታዉሰዋል።
ሱዳን በትግራይ ክልል የተከናወነውን የሕግ ማስከበር ዘመቻን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛትን በመውረር የቁስ እና ሰብዓዊ ሀብት ውድመት መፈጸሟን አምባሳደር ዲና በመግለጫቸው አመልክተዋል።
በሱዳን በኩል በግድቡ ዙሪያ እና በድንበር ጉዳይ ላይ የሚነሳዉ ጥያቄ የሚያመለክተዉ የሦስተኛ ወገን ፍላጎት ያለበት መሆኑን እንደሆነ ገልጸዋል። በኢትዮጵያ በኩል ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እየሰራች መሆኑን አስታውቀዋል።
የ6ኛው ብሔራዊ አቀፍ ምርጫን በተመለከተም “ምርጫውን ለመታዘብ ጥያቄ ያቀረቡ የአገር ዉስጥ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ዝግጅታቸውን አጠናቅዋል” ብለዋል።
የአውሮፖ ሕብረት ታዛቢዎችን የመላክ እቅድ እንደሰረዘ ያስታወቀ ቢሆንም አሁን ግን ምርጫዉን የሚታዘቡ ኤክስፐርቶችን የመላክ ፍላጎት እንዳለዉ ማሳወቁን አምባሳደር ዲና አብራርተዋል።
ሀገራዊ ምርጫውን የመታዘብ ሂደት ቀደም ሲል በኢትዮጵያ በኩል የተቀመጡትን ቅድመ ሁኔታዎች ታሳቢ ባደረገ ሁኔታ የሚፈጸም መሆኑን መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ ጽሕፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m