ኢዜማ ከባሕር ዳር ከተማ እና አካባቢው ከሚገኙ የሲቪል ማኅበራት ጋር ዉይይት አካሄደ፡፡

155
ኢዜማ ከባሕር ዳር ከተማ እና አካባቢው ከሚገኙ የሲቪል ማኅበራት ጋር ዉይይት አካሄደ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 30/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ከባሕር ዳር ከተማ እና አካባቢው ከሚገኙ የሲቪል ማኅበራት ጋር ውይይት አድርጓል፡፡ ውይይቱም በቀጣይ በሚካሄደው ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ኢዜማ አሸናፊ ቢሆን ለሙያ ማኅበራት ተግባራዊ የሚያደርገውን የሙያና ሲቪል ማኅበራት ፖሊሲ አስተዋውቋል፡፡
ለውይይት በቀረበው መነሻ ሃሳብ እንደተገለጸው የኢዜማ የሠራተኛና ሙያ ማኅበራት ፖሊሲ እያንዳንዱ ዜጋ እንደ አቅሙ እና ችሎታው ሠርቶ ራሱንና ቤተሰቡን ሊያሥተዳድር የሚያስችል ገቢ የሚያገኝበት ሁኔታ ይፈጠራል፤ ምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ ጥቅሞቹ የሚጠበቁበት እና በሀገራዊ አጠቃላይ እድገት ሠራተኛውና የሙያ ማኅበራት የድርሻቸውን የሚያበረክቱበት ዐቢይ ምጣኔ ሃብታዊና ፖለቲካዊ ከባቢ መፍጠር ታሳቢ ያደርጋል ተብሏል፡፡
የሥራ ዕድል ፈጠራን ማበረታታት፣ የተቋማት ግንባታ ማጠናከር፣ የሠራተኛውን ምርታማነትና ተወዳዳሪነት ማሻሻል፣ የኢንዱስትሪ ሠላም የሰፈነበት የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት መፍጠር፣ የሥራ እድል እንዲኖር ማበረታታት እና መሰል የፖሊሲው ዓላማዎች ተብራርተዋል፡፡
የኢዜማ የክልል ምክር ቤት ዕጩ ተወዳዳሪ ወይዘሮ ዓባይነሽ ጥጋቡ እንደገለጹት ኢዜማ መንግሥት ኾኖ ቢመረጥ የሴቶች፣ የወጣቶችና ልዩ ልዩ የሙያ ማኅበራት አደረጃጀቶች ከማንኛውም መንግሥታዊና ሃይማኖታዊ ተጽዕኖ ነፃ ሆነው እንዲሠሩ ይደረጋል፡፡ ማኅበራት የመደራጀት ሙያዊ ነጻነት በመጠቀም ለባለሙያዎች ጥቅም ከመቆማቸው አኳያ ብዙ ክፍተቶች እንደሚታይባቸውም ጠቅሰዋል፡፡
የኢዜማ ባሕር ዳር ምርጫ ወረዳ ሊቀመንበር ካሳዬ ሰይድ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ወደ ሥራ በሚሠማራበት ሀገር ይህንን ሊያስተናግድ የሚችልና ጠንካራ የሙያ ማኅበራት አደረጃጀት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ኢዜማ ማኅበራቱ ሙያዊ ነጻነታቸው ተጠብቆ የአባሎቻቸው ሙያዊ ብቃት እንዲረጋገጥ ያደረጋል ብለዋል፡፡ ኢዜማ ብቃት ያለው የሠራተኛና የሙያ ማኅበራት መኖር በማኅረሰቡ ውስጥ ሊኖር የሚገባውን የሀብት ክፍፍል በማመጣጠን በሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፍ ሚዛናዊ የሆነ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ያደርጋል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ ፡- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleኢትዮጵያዊያን በተለያዩ ዘውጎች ሊከፋፍሉ ከሚችሉ አስተሳሰቦች በመውጣት ለሰላምና ሉዓላዊነት በጋራ እንዲቆሙ ተጠየቀ።
Next articleየፌዴራል ፖሊስ ለ19ኛ ዙር በጦላይ ያሰለጠናቸውን ከ6 ሺህ በላይ የምልስ እና የምልምል ሰልጣኞችን አስመረቀ።