ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ ዘውጎች ሊከፋፍሉ ከሚችሉ አስተሳሰቦች በመውጣት ለሰላምና ሉዓላዊነት በጋራ እንዲቆሙ ተጠየቀ።

101
ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ ዘውጎች ሊከፋፍሉ ከሚችሉ አስተሳሰቦች በመውጣት ለሰላምና ሉዓላዊነት በጋራ እንዲቆሙ ተጠየቀ።
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 29/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያዊያን በዘር፣ በቋንቋና በሃይማኖት ሊከፋፍሉ ከሚችሉ አስተሳሰቦች በመውጣት ለሀገራቸው ሰላምና ሉዓላዊነት መከበር በጋራ እንዲቆሙ ተጠየቀ።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በየወሩ የሚያዘጋጀው ‘ቱባ ወግ’ የውይይት መድረክ “ሉዓላዊነታችንን በጋራ የማስከበር ታሪካችን” በሚል መሪ ሃሳብ ተካሂዷል።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው በወቅቱ እንደገለጹት፤ ትውልዱ መልካም ዜጋ እንዲሆንና ሀገሩንና ባህሉን እንዲያከብርና እንዲወድ መስራት ይገባል።
በመተባበርና ወንድማማችነትን በማጠናከር የሀገሩን ሰላምና አንድነት ማስጠበቅ የሁሉም ኀላፊነት መሆን እንዳለበትም ተናግረዋል።
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኀበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ በበኩላቸው “እያንዳንዱ ሰው የተለያየ ሃሳብና አመለካከት ያለው ቢሆንም በሀገር ጉዳይ ግን አንድ ሊሆን ይገባል” ብለዋል።
ጠንካራ እና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባትም አንድነትን ማጠናከርና መተባበር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ “ኢትዮጵያ ለዘመናት ሉዓላዊነቷ ተከብሮ፣ ታሪኳና ዳር ድንበሯ ተጠብቆ የኖረች ታላቅ ሀገር መሆኗን ትውልዱ በቅብብሎሽ ሊገነዘበው ይገባል” ብለዋል።
“ኢትዮጵያውያን ይህንን ሉዓላዊነት አስጠብቀው ዳር ድንበሯንም ጠብቀው የማስቀጠል ኀላፊነት ያለባቸው በመሆኑ በየትኛውም ጊዜና ወቅት ሀገራቸውን ከጠላት ወራሪ ነቅተው መጠበቅ ይገባቸዋል” ነው ያሉት።
ኢትዮጵያዊያን በዘር፣ በቋንቋና በሃይማኖት ሊከፋፍሉ ከሚችሉ አስተሳሰቦች በመውጣት ለሀገራቸው ሰላምና ሉዓላዊነት መከበር በጋራ መቆም እንዲሁም የጋራ ሃብቶችን ለትውልዱ ማስተላለፍ እንደሚገባም ገልጸዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎችም በኢትዮጵያ የታሪክ አረዳድና አመዘጋገብ ውስጥ ትውልዱ ተቀርጾ እንዲያድግ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ከፋፋይ ከሆነ የፖለቲካ እንቅስቃሴ መቆጠብ ተገቢነት እንዳለውም ገልጸዋል።
በመድረኩ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች፣ የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ የታሪክ ምሁራን እና ሌሎችም መሳተፋቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየዲጂታል ኢትዮጵያ 2025ን ለመተግብር የሚያስችል የ200 ሚሊየን ዶላር የብድር ስምምነት ተፈረመ።
Next articleኢዜማ ከባሕር ዳር ከተማ እና አካባቢው ከሚገኙ የሲቪል ማኅበራት ጋር ዉይይት አካሄደ፡፡