የፊታችን ዕሁድ ወልድያ ላይ ስለሚካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ሀገረ ስብከቱ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

384

ባሕር ዳር፡ መስከረም 6/2012 ዓ.ም (አብመድ) የሰልፉ አስተባባሪዎች ከሚያዘጋጇቸው መልዕክቶች ውጭ ማሳተምም ሆነ ማስተላለፍ እንደማይቻል ሀገረ ስብከቱ አሳስቧል፡፡

በኦርቶዶክስ ኃይማኖት ተከታዮች እና በዜጎች ላይ የሚፈጸመውን ግፍና በደል ለማውገዝ ጸሎተ ምህላ እና ሰላማዊ ሰልፍ በወልድያ ከተማ የፊታችን እሁድ መስከረም 11/2012 ዓ.ም ለማካሄድ ዝግጅት ማድረጉን የሰሜን ወሎ ዞን ሀገረ ስበከት አስታውቋል፡፡

የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ህሩያን ሃዋዝ ብዙነህ አድማስ ዛሬ በሰጡት መግለጫ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ለሀገር ግንባታ ያበረከተችውን አስተዋጽዖ ግምት ውስጥ ያላስገባና በህገ መንግስቱ የተረጋገጠውን የሀይማኖት ነጻነት በሚጻረር መልኩ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቤተ ክርስቲያኗ እና በተከታዮቿ ላይ ግድያ፣ ጥቃት እና ቃጠሎ እየተባባሰ መምጣቱን አመላክተዋል፡፡

በመሆኑም ድርጊቱን ለማውገዝ ሰላማዊ ሰልፉ መዘጋጀቱን ሥራ አስኪያጁ አስታውቀዋል፡፡ የሃገሪቱ መንግስት ለሁሉም ዜጎች ጥበቃ እንዲያደርግ፣ ሁሉም ሰው ያለምንም ስጋት በነጻነት ወጥቶ እንዲገባ፣ ዜጎች በሃገራቸው በነጻነት ሰርተው እንዲኖሩ፣ የሀይማኖት ነጻነት እንዲከበር መስራት አንዳለበትም ነው በመግለጫቸው ያስገነዘቡት፡፡

የተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናት እንዲሰሩ፣ ለተጎዱ ምዕመናን እና ካህናት ካሳ ለቤተሰቦቻቸው እንዲከፈል፣ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀድሞ መኖሪያ ቀያቸው እንዲመለሱ እና ለወደመባቸው ንበረት ካሳ እንዲከፈልል በሰልፉ ጥያቄ እንደሚቀርብም ነው የገለጹት፡፡

ቤተ ክርስቲያኗ የውስጥ ችግሮቿን ለመፍታት የሚያስችል መንፈሳዊ ፍርድ ቤት እንድታቋቁም ተደጋጋሚ ጥያቄ ብታቀርብም ምላሽ ስላላገኘች አሁን ላይ ምላሽ እንዲሰጣት ጥያቄ ማቅረብም ሌላው ዓላማ ነው፡፡ ብሄርን፣ ዘርን እና ቋንቋን ምክንያት በማድረግ የሚደርሱ ጥቃቶች እንዲቆሙ ሕዝበ ክርስቲያኑ በሰልፉ ወቅት እንደሚያወግዝም ነው ሥራ አስኪያጁ የጠቆሙት፡፡

ሀይማኖታዊ አለባበስን በመከተል ከጠዋቱ 12፡00 ላይ በከተማዋ ካሉ አብያተ ክርስቲያናት በመነሳት ሰልፉ ይጀመራል፡፡ ከዚያም ወልዲያ ታቦት ማደሪያ ጎን ከሚገኘው የድሮው ኳስ ሜዳ የሰልፉ ማጠቃለያ መርሀ ግብር እንደሚከናወን ነው ሊቀ ህሩያን ሃዋዝ ብዙነህ በመግለጫው ያመላከቱት፡፡ በሰልፉ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ይዘት ያለው መፈክር ማስተጋባት፣ አብሮነትን እና መቻቻልን የሚሸረሽሩ መልዕክቶችን ማስተላለፍ እንደማይፈቀድ አሳስበዋል፡፡ የሰልፉ አስተባባሪዎች ከሚያዘጋጇቸው መልዕክቶች ውጭ ማሳተምም ሆነ ማስተላለፍ እንደማይቻልም የሰልፉ አስተባባሪ ኮሚቴ ቀሲስ ቴዎድሮስ አያሌው አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ክፍሉ ሞገስ

ፎቶ፡- በባለ ዓለምዬ

Previous articleደቡብ አፍሪካ ይቅርታ ጠየቀች፡፡
Next articleየክልሉ ቴክኒክ ሙያ እና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ በዲፕሎማ መርሀ ግብር ለማስተማር ከተሰጣቸው ዕውቅና ውጪ ሲያስተምሩ የተገኙ ዘጠኝ ካምፓስ እና ኮሌጆችን መዝጋቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡