የመራጮች ምዝገባ ዛሬ ይጠናቀቅባቸው በነበሩ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የምዝገባ ቀን ለተጨማሪ ሰባት ቀናት እንዲከናወን ምርጫ ቦርድ ወሰነ፡፡

175

የመራጮች ምዝገባ ዛሬ ይጠናቀቅባቸው በነበሩ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የምዝገባ ቀን ለተጨማሪ ሰባት ቀናት
እንዲከናወን ምርጫ ቦርድ ወሰነ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመራጮች ምዝገባን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
መግለጫው እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ ዋና ተግባር የሆነው የመራጮች ምዝገባን እያከናወነ እንደሆነ
ይታወቃል። በዚህም ሂደት በመጀመሪያ ሰሞን የነበረው የመራጮች ምዝገባ መቀዛቀዝ በከፍተኛ ሁኔታ ተሻሽሎ በአሁኑ ወቅት
በጊዜያዊነት በተሰበሰበው መረጃ (ያለፉት ሦስት ቀናትን ሳይጨምር) 28 ሚሊየን 731 ሽህ 935 ያህል መራጮች የተመዘገቡ
ሲሆን የመራጮች ምዝገባ በ41 ሽህ 798 ያህል ምርጫ ጣቢያዎች እየተከናወነ ይገኛል።
የመራጮች ምዝገባ ከተያዘለት የጊዜ ገደብ በተጨማሪ ለ15 ቀን ተጨምሮ ከአፋር እና ከሶማሌ ክልሎች ውጪ የማጠናቀቂያ
ጊዜው በዛሬ ሚያዝያ 29/2013 ዓ.ም እንደሚሆን ማሳወቁ ይታወሳል።
በዚህ ወቅትም
1. የመራጮች ምዝገባ በተራዘመበት ወቅት ተደራራቢ የበዓላት ቀናት መኖራቸው እና በዚያም የተነሳ በሕጉ መሰረት ብሔራዊ
በዓላት ዝግ በመሆናቸው የመራጮች ምዝገባ ሊከናወን አለመቻሉን
2. የመራጮች ምዝገባ በተራዘመበት ወቅት 1 ሽህ 500 መራጮች የመዘገቡ ጣቢያዎቸን ለይቶ ንዑስ ጣቢያዎችን የማደራጀት
ሂደት ጊዜ መውሰዱን በዚህም ምክንያት ከፍተኛ የመራጮች መጨናነቅ ምርጫ ጣቢያ ላይ መፈጠሩን ተረድቷል።
ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት የመራጮች ካርድ በመውሰድ መምረጥ የሚችሉ ቀላል የማይባሉ ዜጎች በዚህ የተነሳ
የመራጮች ካርድ አለመውሰዳቸውን ቦርዱ በመገንዘብ ባደረገው ስብሰባ የመራጮች ምዝገባ ዛሬ ይጠናቀቅባቸው በነበሩ
በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር፣ በድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር፣ በአማራ ክልል፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ በደቡብ ብሔር
ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል፣ በጋምቤላ ክልል፣ በሃረሪ ክልል፣ በኦሮሚያ ክልል እና በሲዳማ ክልል የመራጮች ምዝገባ እስከ
አርብ ግንቦት 06/2013 ዓ.ም ድረስ ለተጨማሪ 7 ቀናት እንዲከናወን ወስኗል።
በዚህም መሰረት በእነዚህ የከተማ መስተዳድሮች እና ክልሎች የሚገኙ መራጮች የመራጭነት ካርዳቸው በነዚህ ቀናት
በአቅራቢያቸው በሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት እንዲወስዱ እያሳወቅን፣ የቦርዱ አስፈጻሚዎች እና አስተባባሪዎች በሕጉ
መሰረት ቅዳሜ እና እሁድን ጨምሮ ከዛሬ ጀምሮ ባሉት ቀናት እስከ ግንቦት 06/2013 ዓ.ም ድረስ የመራጮች ምዝገባን
እንዲያከናውኑ እናስታውቃለን።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
ሚያዝያ 29 ቀን 2013 ዓ.ም

Previous articleለመምረጥ የሚችል ዜጋ ቀሪ ሰዓቱን ተጠቅሞ የምርጫ ካርዱን በእጁ እንዲያስገባ መራጮች ጥሪ አቀረቡ፡፡
Next articleየዲጂታል ኢትዮጵያ 2025ን ለመተግብር የሚያስችል የ200 ሚሊየን ዶላር የብድር ስምምነት ተፈረመ።