
“በቀጣይ አምስት ዓመታት የሚያስተዳድረኝን ፓርቲ ለመምረጥ ካርድ አውጥቻለሁ፤ሁሉም ዜጋ በቀሪው ሰዓት ካርድ በማውጣት መሪውን በካርድ ሊወስን ይገባል” 80 ዓመት አዛውንት
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 29/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ካርድ ያላወጡ ዜጎች ካርድ እንዲያውጡ የሰጠው ተጨማሪ የሁለት ሳምንታት ጊዜ ዛሬ ይጠናቀቃል፡፡ ዜጎች በቀሪው ሰዓት ካርድ ማውጣት እንዳለባቸውም ይጠበቃል፡፡
የ80 ዓመት አዛውንቱ አቶ የኔው አዳል በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ቲሊሊ ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ እሳቸው በመጪው ሀገራዊ ምርጫ ለመሳተፍ ካርድ በማውጣት እየተጠባበቁ ይገኛሉ። ሊያስተዳድራቸው የሚፈልጉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ በጉጉት በመጠባበቅ ላይ የሚገኙት አቶ የኔው “እኔ ዕድሜየ ገፍቷል፣ ነገ ልሙት ዛሬ አልውቅም፣ በቀጣይ አምስት ዓመታት የሚያስተዳድረኝን ፓርቲ ለመምረጥ ካርድ አውጥቻለሁ፤ሁሉም ዜጋ በቀሪው ሰዓት ካርድ በማውጣት መሪውን በካርድ ሊወስን ይገባል” ብለዋል፡፡
በባለፉት አምስት ተከታታይ ምርጫዎች ካርድ በማውጣት መሳተፋቸውን የገለጹት አቶ የኔው ወጣቱ ትውልድም ካርድ በማውጣት ሊያስተዳድረው የሚገባውን ፓርቲ መምረጥ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
ሌላው የ70 ዓመት የቲሊሊ ከተማ ነዋሪ አቶ አያና ዋሴ እንዳሉት በካርድና በዜጎች ይሁንታ የሚመጣው መንግሥት ሀገሪቱን ተረጋግቶ ለመምራት ዕድል ስለሚያገኝ ሁሉም ዜጎች በካርዳቸው ሊመራቸው የሚችለውን የፖለቲካ ፓርቲ ሊመርጡ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ እሳቸውም ለአካባቢ ነዋሪዎች ተሞክሮ ለመሆን ቀድመው ካርድ መውሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡
‹‹ምርጫ ከተጠናቀቀ በኃላ ሰላም ይመጣል ብለን እናስባለን›› ያሉት አዛውንቱ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እያካሄዱት ያለውን የምርጫ ቅስቀሳም እየተከታተሉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ወጣቱም ከመቸኮልና ስሜታዊ ከመሆን በመውጣት በተረጋጋ መንፈስ ሊያስተዳድር የሚችለውን ፓርቲ በካርዱ መምረጥ እንዳለበት መክረዋል፡፡
አቶ ሞላ አያሌውም የቲሊሊ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ለመሳተፍ ካርድ ማውጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ ከምርጫ በኋላ በውስጥም በውጭም ሰላም የሚነሱ አካላትን ድል ማድረግ ያስፈልጋል የሚሉት አቶ ሞላ ምርጫው በሰላም ተጠናቆ ከሚመረጠው መንግሥት ጋር በመሆን የዜጎችን ሰላም ለማስጠበቅ መነሳት፣ የተጀመሩ ትልልቅ ፕሮጀክቶች የሚጠናቀቁበትን ሁኔታ ማስብ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ሌላው የቲሊሊ ነዋሪ አየነ አለማዬሁ የ75 ዓመት አዛውንት ናቸው፡፡ ካርድ ማውጣታቸውንም ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በፊት በታዛቢነት እንደተሳተፉና ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊ እና ተዓማኒ እንዲሆን በምርጫ ቦርድ እና በመንግሥት እየተከናወነ የሚገኘው ተግባር እንዳስደሰታቸውም ተናግረዋል፡፡
በመኾኑም ዜጎች ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ለቀጣይ አምስት ዓመታት የሚመራቸውን ፓርቲ መምረጥ አለባቸው ብለዋል፡፡ በንግድ ሥራቸው እንደሚተዳደሩ የገለጹት አቶ አየነ ከትግራይ፣ ከኦሮሚያ፣ ከሱማሌና ከተለያዩ አካባቢዎች የንግድ ዕቃዎችን ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ በማዘዋወር መገበያየት የሚቻለውም በምርጫ የተመረጠ ሕጋዊ መንግሥት ሲኖር ነው፤ ሁሉም ዜጋ በካርዱ መሪውን ሊመርጥ ይገባል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ