በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ ለማረጋገጥ እየሠራ መሆኑን የአማራ ክልል አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን አስታወቀ፡፡

106
በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ ለማረጋገጥ እየሠራ መሆኑን የአማራ ክልል አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 29/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ወይዘሮ ግንቤ አየነው በጎንደር ከተማ አሥተዳደር አዘዞ አካባቢ ነዋሪ ናቸው፡፡ ኑሯቸውን የማሽን ጥልፍ በመሥራት ይመራሉ፡፡ ወይዘሮ ግንቤ አካል ጉዳተኛ ቢሆኑም በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ለመሳተፍ ከአንድ ወር በፊት የምርጫ ካርድ አውጥተዋል፡፡ ወይዘሮ ግንቤ እንደገለጹት አካል ጉዳተኞች እንደማንኛውም ዜጋ የመምረጥ፣ የመመረጥ እና የመታዘብ መብት አላቸው፡፡ ይኼን መብታቸውን የሚያስጠብቁት ደግሞ የምርጫ ካርድ በመያዝ ነው፡፡ “ሥለዚህ መብቴን ለመጠቀም ደግሞ ካርድ አውጥቻለሁ” ብለዋል፡፡
ሌሎች አካል ጉዳተኞችም ባለው አጭር ጊዜ የመራጭነት ካርድ መያዝ እና መብታቸውን ተጠቅመው መምረጥ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ “ሌሎች በመረጡት መመራት ሳይሆን እኛም የሚበጀንን በመምረጥ መብታችንን መጠቀም አለብን” ነው ያሉት ወይዘሮ ግንቤ፡፡
ባለፉት ሀገራዊ ምርጫዎች አካል ጉዳተኞች ተሳትፎ ላይ ቅሬታ እንዳላቸው የገለጹት ወይዘሮዋ አሁን የተሰጠው ትኩረት አስደስቷቸዋል፡፡ አካል ጉዳተኞች ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም ማኀረበረሰብ ዲሞክራሲያዊ መብቱን ለማስጠበቅ የምርጫ ካርድ መያዝ እንዳለበትም መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ሌለዋ ወይዘሮ ኢትዮጵያ አለምአንተ በጎንደር ከተማ አሥተዳደር የቀበሌ 20 ነዋሪ ናቸው፡፡ ወይዘሮ ኢትዮጵያ የአዕምሮ ውስንነት ያለባት እና እድሜዋ ከ18 ዓመት በላይ የሆናት ወጣት ልጅ አለቻቸው፡፡ ልጃቸው በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ለመሳተፍ የምርጫ ካርድ በማውጣቷ ደስተኛ ናቸው፡፡
ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሁሉንም ያሳተፈ እንዲሆን እየተሠራ ያለው ሥራ ውጤታማ እንዲሆን እሳቸውም የበኩላቸውን ለማበርከት እየሠሩ መሆኑን ነግረውናል፡፡ ማንኛውም ሠው ዴሞክራሲያዊ መብቱን ለመጠቀም የምርጫ ካርድ ማውጣት አለበት ብለዋል፡፡
እንደ ወይዘሮ ግንቤ ሁሉ ወይዘሮ ኢትዮጵያም ያለፉት ሀገራዊ ምርጫዎች የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ በተመለከተ ደስተኛ አልነበሩም፡፡ በስድተኛው ሀገራዊ ምርጫ የአዕምሮ ውስንነት ያለባቸው አካል ጉዳተኞች እንዲመርጡ መደረጉ የምርጫው ሂደት ጥሩ ነው ባይ ናቸው፡፡
ለስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በቅድመ ምርጫ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው፡፡ ከነዚህ መካከል አንዱ የመራጮች ምዝገባ ነው፡፡ ምዝገባው በሀገር አቀፍ ደረጃ መጋቢት 1/2013 ዓ.ም ተጀምሮ መጋቢት 30/2013 ዓ.ም ተናቆ ነበር፡፡ ነገር ግን የምርጫ ካርድ ማውጫ ጊዜው እስከ ሚያዝያ 29/2013 ዓ.ም ድረስ መራዘሙን ተከትሎ በርካታ አካል ጉዳተኞች ካርድ ማውጣታቸውን የነገሩን ደግሞ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሴት አካል ጉዳተኞች ማኅበር ሰብሳቢ ወይዘሮ በላይነሽ ሲሳይ ናቸው፡፡
ወይዘሮ በላይነሽ አካል ጉዳተኞችን በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ለማሳተፍ የተለያዩ ተግባራት እየተሠሩ መሆኑን ነግረውናል፡፡ ወይዘሮ በላይነሽ እንዳሉት በስድስቱም ክፍለ ከተሞች የሚገኙ ሴት አካል ጉዳተኞች በምርጫው እንዲሳተፉ ለማድረግ በየደረጃው ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ ሥልጠናውን የወሰዱ አካል ጉዳተኞችም ለሌሎች መልዕክት በማስተላለፍ እስካሁን 420 ሴት አካል ጉዳተኞች የምርጫ ካርድ ወስደዋል፡፡
መስማት የተሳናቸው አካል ጉዳተኞች ካርድ የሚወስዱበትን መንገድ ለማመቻቸት የማስተርጎም ሥራ ተሰርቷል ብለዋል፡፡ ወይዘሮ በላይነሽ እንደተናገሩት በሕግ መብታቸው ያልተገደቡ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው አካል ጉዳተኞች የምርጫ ካርድ እንዲወስዱ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል፡፡ ሁሉም አካል ጉዳተኞች “የኔ ጉዳይ ያሳስበዋል” የሚሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ካርድ ማውጣት አለባቸው ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ሰብሳቢ አቶ ፍሬሰላም ዘገየ በሁሉም ዞኖች የሚገኙ አካል ጉዳተኞች በምርጫው እንዲሳተፉ የምርጫ ካርድ እንዲያወጡ የማድረግ ሥራ መሠራቱን ነግረውናል፡፡ እንደ አቶ ፍሬሰላም ገለጻ አካል ጉዳተኞችን በተመራጭነት፣ በመራጭነት እና በታዛቢነት ለማሳተፍ የነበረው ፍላጎት ዝቅተኛ ቢሆንም በተደረገው ውይይት ችግሩ ተፈትቷል፡፡
በክልሉ ባሉ ሁሉም ዞኖች የሚገኙ አካል ጉዳተኞች በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ እንዲሳተፉ ዛሬ የመጨረሻው ቀን መሆኑን በመረዳት የምርጫ ካርድ መውሰድ አለባቸው ብለዋል፡፡
ይህንን በውጤታማነት ለመፈጸም በተደጋጋሚ ስልጠና መሰጠቱንም አስታውቀዋል፡፡ ምርጫን በሚመለከት የወጡ ሕጎች አካል ጉዳተኞችን ያማከሉ መሆናቸውን ለመለየትም ውይይት ተካሂዷል ብለዋል፡፡ 14 አካል ጉዳተኞች በተመረጡ ሠባት ዞኖች ላይ ቅድመ ምርጫ ሁኔታው ምን ይመስላል የሚለውን ለመቃኘት መንቀሳቀሳቸውን አቶ ፍሬሰላም ነግረውናል፡፡
ምርጫ ጣቢያዎች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ መሆናቸውን እና በሂደቱ የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ የሚያበረታታ መሆኑን መታዘባቸውን ገልጸዋል፡፡ ምርጫው ሠላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባልም ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleኮሚሽነር አበረ አዳሙ በኢትዮጵያ ጉዳይ የማይደራደሩ እንደነበሩ ቤተሰቦቻቸው ተናገሩ፡፡
Next article“በቀጣይ አምስት ዓመታት የሚያስተዳድረኝን ፓርቲ ለመምረጥ ካርድ አውጥቻለሁ፤ሁሉም ዜጋ በቀሪው ሰዓት ካርድ በማውጣት መሪውን በካርድ ሊወስን ይገባል” 80 ዓመት አዛውንት