
ኮሚሽነር አበረ አዳሙ በኢትዮጵያ ጉዳይ የማይደራደሩ እንደነበሩ ቤተሰቦቻቸው ተናገሩ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 28/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የቀድሞው ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ሥርዓተ ቀርብ
ተፈጽሟል፡፡ አሚኮ በቀብር ሥነ ሥርዓታቸው ከተገኙ ቤተሰቦቻቸው ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
የኮሚሽነሩ ታናሽ ወንድም ተመስገን አዳሙ ወንድማቸው እንኳን ለተወለዳቸው ይቅርና ለኹሉም አዛኝና ታማኝ ነበሩ ነው ያሉት፡፡
ከመልካምነት በስተቀር ሌላ የማያውቁ በተቻላቸው አቅም ሁሉ ሰውን መርዳት የሚሹና ከችግር መውጫ መንገድ የሚያመላክቱ
ሰው እንደነበሩም ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽነር አበረ አዳሙ የቤተሰቡ አርዓያና መሪ እንደነበሩም ተናግረዋል፡፡ እህትና ወንድሞቻቸው የእሳቸውን ፈለግ ይዘው
ማደጋቸውንም ነው የተናገሩት፡፡ በተቻላቸው መጠን ቤተሰቦቻቸውን ታላቅ እገዛ ያደርጉ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡
ከእምነታቸው የማይጎድሉ ለሥራና ለሀገር ታላቅ ፍቅር የነበራቸው ሰው እንደነበሩም ተናግረዋል፡፡ ለሀገርና ለሕዝብ ቅድሚያ
የሚሰጡ ናቸው ያሉት አቶ ተመስገን ቤተሰቦቻቸውን ጥለው ለሀገርና ለሕዝብ ሲሉ የመጡ ስለመሆናቸውም ገልጸዋል፡፡ ሀገር
ከሌለች ኹሉም የለም፤ መቅደም ያለበት ሀገርና ሕዝብ ነው ብለው የሚያምኑ ሰው እንደነበሩም ነግረውናል፡፡
በኢትዮጵያ ጉዳይ የማይደራደሩ እውነትን መሠረት አድርገው ሥራቸውን የሚከውኑ ሰው እንደነበሩም ተናግረዋል፡፡ በሐሳብ
ልዕልና የሚያምኑ ለሕዝብ ክብር አብዝተው የሚጨነቁ ነበሩም ብለዋል፡፡ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽንን እየመሩ በቆዩበት ጊዜ
ሙሉ ጊዜያቸውን ለሥራ የሠጡ እንደነበሩም ጠቅሰዋል፡፡
የኮሚሽነሩ ቅርብ ዘመድና አብሮ አደግ ዳኛቸው ዓለሙ ኮሚሽነሩ ለቤተሰባቸው አሳቢ ተምረው ከፍተኛ ቦታ ላይ እንዲደርሱ
የሚፈልጉ፣ ሳያዳሉ የሚኖሩ፣ ትጉህ ሰው ነበሩ ብለዋል፡፡ ኮሚሽነሩ ከልጅነታቸው ጀምረው ለሀገራቸው የታገሉ እንደነበሩም
ተናግረዋል፡፡ ኹሉም በፍቅር እንዲኖር የሚሹ ሰው እንደነበሩም ነው ያመላከቱት፡፡ ለሀገርና ለሕዝብ ያልተቆጠበ ትግልና
መስዋዕትነት የሚከፍሉ ሰው እንደነበሩም ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽነሩ ተግባቢ፣ ሥራ አክባሪና የሰውን መብት የማይጋፉ ሰው እንደነበሩም ነው የተናገሩት፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
