
የኮሚሽነር አበረ አዳሙ የሕይወት ታሪክ
ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ከአባታቸው ከአቶ አዳሙ መኮንን እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ጦቢያ ንጋቱ የካቲት 13/1961 ዓ.ም በቀድሞው የጎጃም ክፍለ ሀገር ቆላ ደጋ ዳሞት አውራጃ ደጋዳሞት ወረዳ መለስ ብሳና ሜዳ ቀበሌ ተወለዱ፡፡ እድሜያቸው ለትምሕርት እስኪደርስ በቤተሰቦቻቸው እንክብካቤ አድገው በ1973 ዓ.ም ወይን ውኃ አንደኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት ገብተው እስከ 8ኛ ክፍል ተማሩ፡፡ ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ባላቸው ትምሕርትን የመቀበል ተፈጥሯዊ ተሰጥዖ በአራት ዓመታት ውስጥ የመጀመሪያ ደረጃ ትምሕርታቸውን በማጠናቀቅ ሀገር አቀፉን የስምንተኛ ክፍል ሚኒስትሪ ፈተና ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ወደ 9ኛ ክፍል ተዛውረዋል፡፡
ኮሚሽነር አበረ ተወልደው ባደጉበት አካባቢ ቅርብ የሆነ የሁለተኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት ባለመኖሩ ከትውልድ አካባቢያቸው ርቀው መሄድ ስለነበረባቸው አጎታቸው ይኖሩበት ወደ ነበረበት አምቦ ከተማ በመሄድ የሁለተኛ ደረጃ ትምሕርታቸውን በላቀ ውጤት በመጨረስ አጠናቀዋል፡፡ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወስደው ኮሌጅ የሚያስገባ ነጥብ ያመጡ በመሆናቸው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩንቨርሲቲ ኮሌጅ ባወጣው የመኮንንነት ፈተና ተሳትፈው በማለፋቸው በፖሊስ ዩንቨርሲቲ ኮሌጅ የሚሰጠውን የመኮንንነት ትምሕርት አጠናቀው በምክትል መቶ አለቃነት ማዕረግ በዲፕሎማ በ1986 ዓ.ም ተመርቀዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ፖሊስ ዩንቨርሲቲ ኮሌጅ ከተመረቁ በኋላ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዞን 2 ወረዳ 21 ቂርቆስ ፖሊስ ጣቢያ ተመድበው በወንጀል መከላከል፣ ወንጀል ምርመራና በተለያዩ ኃላፊነት ቦታዎች ለአምስት ዓመታት ያህል ሰርተዋል፡፡ በኃላፊነት በነበሩበትም ወቅት ወንጀልን በመከላከል፣ ሕዝብን በማገልገል ተደጋጋሚ ሽልማቶችን ተቀብለዋል፡፡
በወቅቱ በነበረው ሥርዓት መሪዎች መመሪያን አይቀበልም በሚል ሰበብ ከሦስት ጊዜ በላይ ለእስር ተዳርገው ነበር፡፡ ኮሚሽነር አበረ ጥቃትን የሚቀበል ስብዕና የሌላቸው በመሆኑ ይህንን በደል በመጠየፍ በቀድሞው የደኅንነት ኃላፊዎች ከታሰሩበት ቦታ የተደገሰላቸውን ሞት በማምለጥ ከሀገራቸው ለመሰደድ ተገደዋል፡፡ ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ከአያቶቻቸው በወረሱት ኢትዮጵያዊ ጀግንነት ህወሓት መራሹን መንግሥት በኃይል ለመጣል ወደ ኤርትራ በረሀ በመውረድ “የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር’ የሚባል ድርጅት ከትግል ጓደኞቻቸው ጋር በመመስረት የወታደራዊ ክንፍ አዛዥ በመሆን ሲታገሉ ቆይተዋል፡፡
ከዚያም ትግሉን ለማስፋትና ህወሓት መራሹን መንግሥት ከሥልጣን በፍጥነት ለማውረድ ከኤርትራ በተጨማሪ በደቡብ ሱዳን፣ በኬኒያና በዩጋንዳ ትግሉን ሲመሩ ቆይተዋል፡፡
በኋላም ራሳችውን ከቀጥታ የትግል ተሳትፎ ለተወሰነ ጊዜ በማግለል በኬንያ ሊሙሩ ከተማ በሚገኘው የአሜሪካን ዩኒቨርስቲ የነፃ ትምህርት ዕድል በማግኘታቸው በሊደርሽፕ ማኔጅመንት ዲግሪያቸውን ያገኙ ሲሆን የአራት ዓመቱን ትምህርት በ2 ዓመት ብቻ በላቀ ውጤት አጠናቀዋል።
ከዚያም በመቀጠል በዓለም አቀፍ ስደተኞችና ሰብዓዊነት ረጅ ተቋማት አማካኝነት ወደ ስዊድን ሀገር በማቅናት በስደተኝነት ይኖሩ ነበር፡፡ ከዚያም “ግንቦት ሰባት የነፃነትና የእኩልነት ንቅናቄን ከመስራች አባልነት አንስቶ እስከ ከፍተኛ አመራርነት በመምራት ታግለው አታግለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በስዊድን ሀገር የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ፕሬዝዳንት በመሆን ሕዝባቸውን አገልግለዋል፡፡
በስዊድን ቆይታችውም ከታዋቂው የሉንድ ዩኒቨርስቲ (Lunds University) ሕግና የማኅበረሰብ ሳይንስ ጥናት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን (MSc in Sociology of Law) በከፍተኛ ውጤት ያገኙ ሲሆን የመመረቂያ የምርምር ጽሑፋቸው በዩንቨርስቲው ተመርጦ በመታተም ለገበያ ቀርቦላቸዋል፡፡
መጽሐፋቸውም የበይነ-መረብ መገበያያ በሆነው በአማዞን በሽያጭ ላይ ይገኛል፡፡ ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ከሌላኛው በስዊድን ሀገር አንጋፋና ታዋቂ ከሆነው ማልሞ ዩኒቨርስቲ (Malmo University) ሌላኛውን ሁለተኛ የማስተርስ ዲግሪያቸውን በዓለም አቀፍ ስደተኞችና የማኅበረሰብ ግንኙነት (MA in Intomational Migration and Ethnic Relations) በከፍተኛ ማዕረግ አግኝተዋል፡፡
ኮሚሽነር አበረ በስዊድን ሀገር እያሉ ተጨማሪ የመጀመሪያ ዲግሪ በሕግና በፖሊስ ሳይንስ (BA in Legal and Police Science) ከሌላኛው የስዊድን ታዋቂ ከሆነው ሊኔኖስ ዩንቨርሲቲ (Linnaeus University) አግኝተዋል፡፡
ከእነዚህ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ትምህታቸውን ጨርሰው ፤ ጥሩ ገቢ የሚያስገኝ ሥራ አግኝተው፤ ልጆች ወልደው ፤ ከትግሉ ጎን ለጎን የግል ኑሯቸውን ማጣጣም በጀመሩበት ወቅት በኢትዮጵያ ለውጥ መምጣቱን ተከትሎ በተደረገላቸው ጥሪ ሕዝባቸውን ለማገልገል ወደ ሀገራቸው ሊገቡ ችለዋል፡፡
በሀገር ደረጃ የመጣውን ለውጥ በመቀላቀል በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፖሊስ ኮሚሽን ታሪክ የመጀመሪያው በፖሊስ ሳይንስ የተመረቀ ፖሊስ ኮሚሽነር በመሆን ከየካቲት 2011 ዓ.ም እሰከ ሚያዝያ 2013 ዓ.ም ድረስ በቅንነትና በታማኝነት አገልግለዋል፡፡ ኮሚሽነር አበረ ሀገራቸውን አንስተው የማይጠግቡ፤ ለሕዝባቸው ልዩ ፍቅር ያላቸው፤ ሁሉም ነገር ከሀገር እና ከሕዝብ በታች ነው ብለው የሚያምኑ፤ በሕይወት እስከተለዩበት ጊዜ ድረስ ሀገራቸውን እና ሕዝባቸው እንዳስቀደሙ የኖሩ እውነተኛና ሀቀኛ አርበኛ ናቸው፡፡
ኮሚሽነር አበረ አዳሙ በጣም ቆፍጣነ ወታደር፣ ምሁር፣ ደራሲ፣ ገጣሚ እና የሕግ ባለሙያ ሲሆኑ ከሦስት በላይ ቋንቋዎችን አቀላጥፈው መናገርና መፃፍ የሚችሉ በሁሉም ዘርፍ በሚባል ደረጃ ሙሉ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ነበሩ።
ኮሚሽነር አበረ በአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ለተደረገው ሪፎርም ጥናት በማድረግና በመምራት የአንበሳውን ድርሻ በመውሰድ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ከማድጋቸውም በላይ ሪፎርሙን በቁርጠኝነት በመምራት አመርቂ ውጤቶች እንዲመዘገቡ አድርገዋል፡፡
በኮሚሽነር አበረ መሪነት ከተመዘገቡ የሪፎርሙ ውጤቶች መካከል ጥቂቶችን ለመጥቀስ ያህል፡-
• ከለውጡ በፊት የነበሩ የአሠራር ችግሮችን በማስቀረት በኮሚሽኑ ውስጥ የሥራ ምደባ በበቂ ችሎታና ክህሎት ላይ የተመሰረተ ብቻ እንዲሆን በመደረጉ በሠራዊቱ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ በራስ መተማመን እንዲፈጠር አድርገዋል፤ በዚህም በርካታ ተተኪ ወጣት ወንድና ሴት መኮንኖች ወደ ኃላፊነት እንዲመጡ አድረገዋል፡፡
• የፖሊስ ሪፎርም በተለያዩ ችግሮች እንዲቆም ተደርጎ የነበረውን ችግሩን በመፍታት ሪፎርመን ወደ ኋላ ከመመለስ አደጋ በመታደግ ሪፎርሙ ተግባራዊ በመደረጉ ለሌሎች ክልሎችና ለፌደራል ፖሊስ በተሞክሮነት እየተወሰደ ያለ ነው፡፡
• የክልሉ ፖሊስ አባላትን ልዩ ልዩ የጥቅማጥቅም መመሪያ እንዲዘጋጅ እና ስራ ላይ እንዲውል አድርገዋል፡፡
• በኮሚሽኑ በተለያዩ መዋቅር የተደራጁ የሥራ ክፍሎችን በአንድ ዘርፍ ሥር በማደራጀት የወንጀል መከላከል አቅማቸው እንዲያድግና በተለይም የክልሉ ልዩ ኀይል ፖሊስ ከክልል አልፎ ሀገራዊ የሕግ ማስከበር ሥራ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የኃላፊነት ሚናቸውን ተጫውተዋል፡፡
• የክልሉ ፖሊስ ልዩ ልዩ መመሪያዎች ለበርካታ ዓመታት ሳይፀድቁ የቆዩቱን እንዲፀድቁ በመደረጉ በአባላት ውስጥ ይታይ የነበረውን የመልካም አስተዳደር ችግር እንዲፈታ ሠርተዋል፡፡
• ሪፎርሙ የሴቶችን ተሳትፎ በእጅጉ ያሳደገ መሆኑ እና ሌሎችም በርካታ ውጤቶች ተገኝተዋል፡፡
ኮሚሽነር አበረ ከመደበኛ ሥራቸው ጎን ለጎን ከብዙ ንባብ እና ልምድ ያገኙትን ዕውቀት በመቀመር “የሕግ የበላይነት ለሀገራዊ ልማት” በሚል ርዕስ መጽሐፍ በመጻፍ የሕግ የበላይት ለሀገር ዘላቂ ልማትና ሰላም ያላቸውን አስተዋፅኦ በማሳየት ለትውልድ አበርክተዋል፡፡
በአጠቃላይ ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ባላቸው ጥልቅ የሀገርና የሕዝብ ፍቅር የተነሳ የራሳቸውን ቤተሰብ መስዋዕት በማድረግ ከተመቻቸ የውጭ ሀገር ኑሮ ሕዝቤን አገለግላለሁ በሚል ከለውጡ ዋዜማ ጀምረው በወኔና በፍፁም የሀገር ፍቅር ስሜት ወደ ሀገር ቤት መጥተው በአልተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ ሆነው የአማራ ብሔራዊ ክልልን ከፀጥታ ቀውስ የታደጉ፤ በሠራዊቱ አመራሮችና አባላት ዘንድ ተቀባይነት የነበራቸው፤ አስተዋይ፣ ቅንና ተግባቢ እንዲሁም ሙያዊ ብቃትና ክህሎት የነበራቸው፤ ሙያው የሚጠይቀውን ሥነ-ምግባር የተላበሱ ባለምጡቅ አዕምሮ ነበሩ፡፡
ኮሚሽነር አበረ አዳሙ የልዩ ኃይሉን፣ የመደበኛ ሠራዊቱንና በተቋሙ ሥር ያሉትን ሠራተኞች የሚመዝኗቸው በትምህርት ዝግጅታቸው፣ በዕውቀታቸው፣ በሥነ- ምግባራቸውና በሥራ ብቃታቸው እንጂ ሌሎች መመዘኛዎችን አምርረው የሚጠሉ ብቻ ሳይሆን አድሏዊ አሠራርንና ኢ-ፍትሐዊነትን በመቃወም ነፍጥ አንስተው በረሃ የወረዱና በሚችሉት ሁሉ የታገሉ ጀግና መሪ ነበሩ፡፡
ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ህወሓት በእብሪት የአማራ ክልልን በወረረችበትና ኢትዮጵያን በእናት ጡት ነካሽነት በወጋችበት ጊዜ ቁርጠኛ አመራር የሰጡና የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ በሕግ ማስከበሩ ሂደት በሀገር አቀፍ ደረጃ ያስመዘገበውን ዘመን ተሻጋሪ ገድል ዕውቀታቸውንና ክህሎታቸውን ተጠቅመው በመምራት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያደረጉ ነበሩ፡፡ ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ባለትዳርና የሁለት ወንድ ልጆች አባት እንዲሁም የበርካቶች ወንድም የነበሩ ሲሆን ሚያዚያ 26/2013 ዓ.ም ድንገት ባጋጠማቸው ህመም ሆስፒታል ገብተው በህክምና እየተረዱ እያሉ በተወለዱ በ52 ዓመታቸው ህይወታቸው አልፏል፡፡
የቀብር ሥነ-ሥርዓታቸው የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የክልሉ ከፍተኛ የፖሊስ መኮንኖችና አባላት፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸውና ቤተሰቦቻቸው በተገኙበት በባሕር ዳር ፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ዛሬ ተፈጽሟል፡፡