የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “ሕወሓት” እና “ሸኔ” በሽብርተኝነት ለመፈረጅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ አጸደቀ፡፡

200
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “ሕወሓት” እና “ሸኔ” በሽብርተኝነት ለመፈረጅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ አጸደቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 28/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ምክር ቤቱ ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ባካሄደው 6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 13ኛ መደበኛ ስብሰባ ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እና ሸኔ በሽብርተኝነት እንዲሰየሙ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ አጽድቋል፡፡
ሁለቱም በሽብርተኝነት የተሰየሙት ድርጅቶች ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲና የመብት መከበር ጥያቄዎች እና ትግል አማካኝነት የመጣውን ለውጥ ለመቀልበስ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን ሲፈጽሙ እና ሲያስፈጽሙ መቆየታቸው ተነስቷል፡፡ የሚያደርሷቸው ሁሉን አቀፍ ጥፋቶችም የዜጎችን የእርስ በርስ ግንኙነት በመሸርሸር እና ሕገ መንግሥቱን ህልውና አደጋ ላይ ለመጣል መሥራታቸውን መንግሥት በማስረጃ ደርሶበታል ሲሉ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡
ከጀርባቸው የፖለቲካ አስተሳሰብን ያነገቡት እነዚህ የሽብር ቡድኖች እንቅስቃሴያቸው የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ ሦስት ስር ስለሽብር ወንጀል ድርጊት የተሰጠውን ሙሉ ትርጓሜውን ሙሉ በሙሉ የሚያሟላ ድርጊት እንደፈጸሙም ዋና ዐቃቤ ሕጉ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶክተር) ለምክር ቤት አባላት አብራርተዋል፡፡
ሁለቱን ድርጅቶች በአሸባሪነት ለመሰየም በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ተቀባይነት ያገኘውን የውሳኔ ሀሳብም የሕዝብ እንደራሴዎቹ አጽድቀዋል፡፡ የሕዝብ እንደራሴዎችም ውሳኔው የዘገየ ቢሆንም ተገቢና ትክክለኛ ሲሉ ድጋፋቸውን አሰምተዋል፡፡ አሁንም የወንጀል ድርጊቱን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሚገባ ማሳወቅ፣ ውሳኔዎችን በአሠራር መደገፍ፣ ሕጋዊ ሥርዓቱን ተከትሎ አፈጻጸሙ ተግባራዊ ይደረግ ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ንጹሐን ዜጎች ሰለባ እንዳይሆኑ፣ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ እና የጸጥታና የደኅንነት ተቋሙን ማጠናከር እንደሚገባም አንስተዋል፡፡ ይህን ተከትሎ የሚመጣውን የውስጥም ሆነ የውጭ ጫናን ለመመከት ከወዲሁ ሊሠራ ይገባልም ብለዋል፡፡ ውሳኔውም “ውሳኔ ቁጥር 10/2013 ዓ.ም” ሆኖ ጸድቋል፡፡
ዘጋቢ፡- ጋሻው ፈንታሁን – ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleሰበር ዜና
Next articleየኮሚሽነር አበረ አዳሙ የሕይወት ታሪክ