
ኮሚሽነር አበረ አዳሙ የአማራ ፖሊስ ዘመናዊ አሠራር እንዲከተልና ብቁ ተቋም እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ እንደነበሩ የሥራ
ባልደረቦቻቸው ተናገሩ፡፡
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 27/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የቀድሞው የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩት ኮሚሽነር አበረ
አዳሙ ትናንት ሕይወታቸው ማለፉ ይታወሳል፡፡
ኮሚሽነር አበረ አዳሙ በሥራ ዘመናቸው የነበራቸውን አበርክቶ በተመለከተ አሚኮ ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የኮምዩኒኬሽንና ሚዲያ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር መሠረት ደባልቄ ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ሕዝብ
የሚወዱ እድሜያቸውን ሙሉ ለሀገርና ለወገን ሲሉ የታገሉ እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡ ለሀገርና ለሕዝብ ሲሉ ከተመቻቸ ኑሯቸው ርቀው
በቁርጠኝነት ያገለገሉ መሪ መሆናቸውንም ነው የተናገሩት፡፡
ኮሚሽነሩ በአማራ ፖሊስ ተቋም ውስጥ ለውጥ እንዲመጣና ተቋሙ ዘመኑን የሚመጥን እንዲሆን ራዕይ ይዘው ሲሠሩ የነበሩ
መሆናቸውንም አብራርተዋል፡፡ የፖሊስ ሠራዊቱ ግልጽ በሆነ አሠራር እንዲመራ ያደረጉ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡ በተቋሙ
አቅምንና ደረጃን መሠረት ያደረገ አሠራር እንዲኖር ያደረጉ ናቸውም ብለዋቸዋል፡፡ ተቋሙ ዘመናዊ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት
ሲያደርጉ መቆየታቸውንም አንስተዋል፡፡
ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ሴቶች የትምህርት ዕድል እንዲያገኙና ወደ ኃላፊነት እንዲመጡ ያደረጉ ናቸውም ብለዋል፡፡
ኮሚሽነሩ ፖሊስ በሙያው ተጠቃሚ እንዲሆን የሚሹና ለማድረግ የሚጥሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
ለሥራቸው ቀናዒ የሆኑና በማንኛውም ሰዓት ሰውን ለመርዳት ዝግጁ የሆኑ እንደነበሩም ነግረውናል፡፡
የሥራ ኃላፊዎች በነጻነትና በራስ መተማመን እንዲሠሩ የሚያበረታቱ እንደነበሩ አስገንዝዋል፡፡ ከቤትና ከቤተሰቦቻቸው ርቀው
ለአማራ ሕዝብ ተጋድሎ ያደረጉ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
በአማራ ፖሊስ ኮሚሽን የማኅበረሰብ አቀፍ፣ ትራፊክና ኢንቨስትመንት መመሪያዎች ዘርፍ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ሙሉ ሁነኛው
ኮሚሽነር አበረ የፖሊስ አባል ከመሆን እስከ መሪነት የደረሱ እንደነበሩ ነው ያስታወሱት፡፡
ኮሚሽነሩ የአማራ ፖሊስ ኮሚሽንን በመሩበት ዘመን ዘመናዊ አሠራርን በመፍጠር ለውጥ ያመጡ ናቸው ብለዋል፡፡
ኮሚሽነሩ ወደ ተቋሙ እንደተቀላቀሉ ተቋሙ የነበረበትን ደረጃ በማጥናት በተቋሙ ውስጥ የነበሩ ችግሮችን፣ ውጫዊና ውስጣዊ
ተፅዕኖዎችንና በመለዬት ተቋሙ ለውጥ እንደሚያስፈልገው መወሰናቸውንም አስታውሰዋል፡፡ በተቋሙ ውስጥ ሥራና ሠራተኛን
ለማገናኘት፣ ተቋሙን ወደፊት ለማራመድ የሄዱባቸው አሠራሮች ለሌሎች ተሞክሮ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ተቋም በሕግና
በሥርዓት መመራት አለበት ብለው የሚያምኑ እንደነበሩም አንስተዋል፡፡
የፖሊስ ሠራዊት በአዋጅ ሲቋቋም የተቀመጠው ሕግ መተግበር አለበት የሚል አቋም የነበራቸው መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የፖሊስ ተቋሙን የሚመሩ ሰዎችም በአቅምና በሕግ አግባብ እንዲመጡ ያደረጉ መሆናቸውን ነው የተናገሩት፡፡
በፖሊስ ኮሚሽኑ ተጨባጭ ለውጥ ያመጡ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል የጸጥታ ኃይል አስደናቂ ጉልበት የፈጠረው በእሳቸው አሠራርና አደረጃጄት መሠረት መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ኮሚሽነሩ የፈጠሩት አደረጃጄት ጠንካራ መሠረት መጣሉንና የተከፈተበትን ጥቃት መቋቋም ማስቻሉንም አንስተዋል፡፡
ኮሚሽነሩ ጥሩ የመሪነት ጥበብ የነበራቸው ልምዳቸውን የሚያካፍሉና በለውጥ የሚያምኑ ሰው እንደነበሩም ነግረውናል፡፡
ኮሚሽነሩ ለአማራ ፖሊስ፣ ሕዝብና መንግሥት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያደረጉ እንደነበሩም ገልጸዋል፡፡ የአማራ ክልል እንዲረጋጋና
ራሱን እንዲጠብቅ ቁርጠኛ የሆነ አቋም የነበራቸው መሆኑን ያነሱት ምክትል ኮሚሽነሩ የአማራ ሕዝብ ኢትዮጵያን የገነባ፣ ያቆዬና
ወደፊት ይዞ የሚጓዝ ነው ብለው የሚያምኑ እንደነበሩም ተናግረዋል፡፡
የአማራ ሕዝብ በምክንያታዊነት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በውስጡ ይዞ ኢትዮጵያን ከፍ እንዲያደርግ ጽኑ ፍላጎት የነበራቸው
እንደነበሩም ነው የነገሩን፡፡
ሥራ ወዳድ እንደነበሩም አመላክተዋል፡፡ ሥራ በመውደዳቸው ልጆቻቸውን ለማዬት እንደጓጉ በድንገት ማለፋቸውንም
አስታውሰዋል፡፡
አንድ ሀገር ወደ ፊት ለመጓዝ በሕግና ሥርዓት መመራት ይገባል የሚል ጽኑ አቋም የነበራቸው ሰው እንደነበሩም ገልጸዋል፡፡ ሕግና
ሥርዓት ያልያዘ አካሄድ ተሸናፊ ነው፤ ሀገርንም ይበድላል የሚሉ እንደነበሩም ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽነሩ ማንበብ የሚወዱ የፖሊስ አባላትም በእውቀት የተመሠረተ ሥራ እንዲኖራቸው ጥረት የሚያደርጉ እንደነበሩም ነው
የነገሩን፡፡ ኢትዮጵያዊ አንድነትና አይሸነፌነትን እናምጣ፣ ፖሊስም በዚህ መርህ ይገንባ ብለው የሚያምኑ እንደነበሩም ነው
የተናገሩት፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m