
ባሕር ዳር፡ መስከረም 6/2012 ዓ.ም (አብመድ) በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ናይጄሪያውያን ለደረሰባቸው ጥቃት ደቡብ አፍሪካ ይቅርታ ጠየቀች፡፡
ከሳምንት በፊት በደቡብ አፍሪካ የተቀሰቀሰውን መጤ ጠል ጥቃት ተከትሎ በሀገሪቱ የሚኖሩ ሌሎች አፍሪካውያን ጥቃት ደርሶባቸዋል፡፡ ይህንን ተከትሎም ናይጄሪያ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ 187 ዜጎቿን ማስወጣቷ ይታወቃል፡፡ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲርል ራማፎሳ ደግሞ የሃገራቸው ዜጎች ባደረሱት መጤ ጠል ግጭት ጉዳት የደረሰባቸው የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ዜጎችን ከፍተኛ መልእክተኛ በመላክ ይቅርታን ጠይቀዋል፡፡
ከናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪ ጋር ቆይታ ያደረጉት የደቡብ አፍሪካ ልዩ መልእክተኛ ጄፍ ራዴቤ ድርጊቱ የደቡብ አፍሪካ እሴቶችን የሚፃረር እና ሕዝቡን የማይወክል ነው ብለዋል፡፡ ደቡብ አፍሪካ ለቀጣናው ሰላም፣ መረጋጋት እና አብሮነት በቁርጠኝነት እንደምትሰራም ነው ያረጋገጡት፡፡
ፕሬዝዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪ በበኩላቸው ናይጄሪያ ለደቡብ አፍሪካ ነፃነት ትልቅ መስዋዕትነት መክፈሏን ተናግረው፤ ፕሬዝዳንት ሲርል ራማፎሳ ይቅርታ ለመጠየቅ መልዕከተኛ በመላካቸው አመስግነዋል፡፡
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲርል ራማፎሳ በቀድሞው የዝምባብዌ ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ አስከሬን ሽኝት በሃራሬ ብሄራዊ ስቴዲየም ተገኝተው ባደረጉት ንግግር በሃገራቸው በሚኖሩ የውጭ ዜጎች ላይ ለደረሰው ጥቃት በይፋ ይቅርታ መጠየቀቻው ይታወሳል፡፡
ምንጭ፡- ሲጂቲኤን
በታዘብ አራጋው