ደጅአዝማች ቢተወደድ መንገሻ ጀምበሬ ማን ናቸው?

1420

ደጅአዝማች ቢተወደድ መንገሻ ጀምበሬ ማን ናቸው?
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 27/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ዛሬ ለ80ኛ ጊዜ የሚከበረውን የአርበኞች ቀን በዓል ምክንያት በማድረግ
የኢትዮጵያ ምድር ካፈራቻቸው ልበ ሙሉ ጀግኖች መካከል የደጃአዝማች ቢተወድድ መንገሻ ጀምበሬን ማንነት ልንነግራችሁ
ወደድን። ሚያዝያ 27/1933 ዓ.ም የድል ቀን ሲነሳ አርበኛ ደጃአዝማች ቢተወደድ መንገሻ ጀምበሬ የፈጸሙትን አኩሪ ታሪክ
ማስተዋስ ግድ ይላል። ደጅአዝማች ቢተወድድ መንገሻ ጀምበሬ ግንቦት 13/1984 ዓ.ም በሜጫ አውራጃ መወለዳቸውን ከግለ
ታሪካቸው የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
አቶ አሳየ አንተነህ በዳንግላ ወረዳ በሚገኘው ቢተወደድ መንገሻ ጀምበሬ ትምህርት ቤት ሲያስተምሩ ቆይተው በጡረታ
ተገልለዋል። በልጅነታቸው፣ በጎልማሳነታቸውና አሁንም ጡረታ ላይ ሆነው ስለ ደጅአዝማች ቢተወድድ መንገሻ ጀምበሬ የተለያዩ
መረጃዎችን በማሰባሰብ ይታወቃሉ፡፡ እንደ አቶ አሳየ ገለጻ የደጃዝማች ቢተወድድ መንገሻ ጀምበሬ አባት ጀምበሬ እምሩ የሜጫ፣
የዴንሳ፣ የጉታ፣ የአገው ምድር ባላባት በመሆን ለብዙ ዘመናት አካባቢውን አሥተዳድረዋል፡፡ የደጃዝማች ቢተወድድ መንገሻ
ጀምበሬ ቤተሰቦች ከአባታቸው እስከ ቅድመ አያቶቻቸው ድረስ ሁሉም የደጃዝማች ማዕረግ ያላቸው ናቸውም ብለዋል፡፡
ደጃዝማች ቢተወድድ መንገሻ ጀምበሬም ብልህ፣ አስተዋይ፣ በልጅነት ዘመናቸው በአልሞ ተኳሽነታቸው ተወዳዳሪ
የማይገኝላቸው፣ በበገና ድርደራ እና በፈረስ ግልቢያ የሚታወቁ ነበሩ፡፡ ለአደንና ውኃ ዋናም ልዩ ፍቅር ያላቸው ትልቅ አርበኛ
ነበሩ፡፡ ደጃዝማች ቢተወድድ መንገሻ ጀምበሬ በተወለዱ በዘጠኝ ዓመታቸው አባታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ከአያታቸው
ደጃዝማች እምሩ ቤት ኾነው የቤተ ክህነት ትምሕርት እየተከታተሉ አደጉ፡፡ ከዚያ በኋላም አያታቸው ደጃች እምሩ ሲሞቱ
ከአጎታቸው ደጃአዝማች ሽፈራው እምሩ ጋር በመሆን የተለያዩ ወታደራዊ ስልጠናዎችን እየወሰዱ አደጉ፡፡ በእድገት ዘመናቸው
የደጃአዝማች ቢተወድድ መንገሻ ጀምበሬን ጀግንነት የተመለከቱት ደጃዝማች ሽፈራው እምሩ ከሚያሥተዳድሩት ግዛት በመቀነስ
ቆላ አቦሌ የሚባለውን ግዛት ሰጧቸው፡፡
ከዚያ በኋላም በተወለዱ በ32 ዓመታቸው የደጃዝማችነት ማዕረግ በማግኘታቸው የቡሬ ዳሞት አውራጃንና ሰከላ አካባቢዎችን
ማሥተዳደር ጀመሩ፡፡ በመልካም ፀባያቸው፣ በአስተዋይነታቸው እና ለሀገራቸው ባላቸው ልዩ ክብር ምሥጉን ሆኑ፡፡
በሚያሥተዳድሩት አካባቢ የፀጥታው ችግር የሌለበት፣ በትንሹም በትልቁም የሚወደድ ባሕርይ እንዳላቸው በመታወቁ ሜጫን
እንዲያሥተዳድሩ ትልቅ ኃላፊነት ተሰጧቸዋል፡፡ በወቅቱ እሳቸው በሚያሥተዳድሩት ግዛት ፍርድ የሚያጓድል፣ ድሃን የሚበድል፣
መንገደኛን የሚዘርፍና በአጠቃላይ ሕገ ወጥ ተግባር የሚፈጽም ሰው ሲኖር በፍጥነት ፍርድ በመስጠት የሚታወቁ ናቸው፡፡
በ1928 ዓ.ም የጣሊያን ወራሪ በመጣ ጊዜ በግዛታቸው ማለትም በሜጫ አውራጃ አካባቢ የሚገኘውን ጦር አስከትለው ከራስ
እምሩ ጋር በትግራይ በኩል በመዝመት ለእናት ሀገር የሚከፈለውን መስዋትእነት ከፍለዋል፡፡ በጦርነቱ ወቅት የጣሊያን ኃይል
እየበረታ ሲመጣ ወደ ኋላ በማፈግፈግና እንደገና በየአካባቢው የሚገኘውን የጎበዝ አለቃ እያስተባበሩ ጠንካራ ውጊያ በማድርግ
የጠላትን ጦር ድል የተቀዳጁ አርበኛ ነበሩ፡፡ ከትግራዩ ጦርነት በተጨማሪ የጎጃም አርበኞች የጣሊያን ወራሪዎችን በአራት
አቅጣጫ ተከፋፈለው ሲፋለሙ ደጃዝማች ቢተወድድ መንገሻ ጀምበሬ አገው ምድርን፣ ሠከላን፣ ሜጫን፣ ጉታን፣ አቸፈርን፣ አለፋ
ጣቁሳ መርተው እንደነበር አቶ አሳየ ተናግረዋል፡፡
በላይ ዘለቀ ቢቸናን፣ ራስ ኃይሉ ደብረ ማርቆስንና ሞጣን እንዲሁም ራስ በዛብህ ዳሞት አካባቢን በማካለል የጠላት ጦርን እረፍት
ነሱት፡፡ ቢተወድድ መንገሻ ጀምበሬ ከደጃዝማች በላይ ዘለቀና ከሌሎች የውስጥ አርበኞች ጋር በመሆን የጋራ ጠላትን የተዋጉና
በሀገር ጉዳይ እጅግ ከፍተኛ መናበብ የነበራቸው መሆኑንም አቶ አሳየ ተናግረዋል፡፡ ወራሪ ጠላትን የማሸነፋቸው ምስጢርም
በጋራ መሥራት መቻላቸው ነው ብለዋል፡፡ በውጊያ ወቅትም በየመካከላቸው መረጃ ይለዋወጡ እንደነበረም ስለ እሳቸው የተጻፈ
መረጃ ያመላክታል፡፡ ከሌሎች አርበኞች ጋር በመሆን ለፈጸሙት ጀብድ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የእንደራሴነት ማዕረግ
መስጠታቸውን የግል ታሪካቸው ያስረዳል፡፡
በጀግንነታቸው ጠላት እጅግ የሚፈራቸው ደጃዝማች ቢተወድድ መንገሻ ጀምበሬ በአንድ ወቅት በባሕር ዳር አካባቢ በወራሪው
ኃይል ተማርከው የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ከጠላት መንጋጋ መውጣት መቻላቸውን አቶ አሳየ አስረድተዋል፡፡ ከምርኮ
በማምለጥም የሜጫንና የጉታን ማኅበረሠብ በማስተባበር የጠላትን ምሽግ እየሰባበሩ ጠላትን ድል ነስተዋል፡፡ ቢተወድድ
መንገሻ ጀምበሬ በአርበኝነት ዘመናቸው በሠከላ፣ በፋግታ፣ በባሕር ዳር፣ በትግራይ አካባቢዎች ከወራሪ ጦር ጋር በመዋጋት ድል
የተቀዳጁ ጀግና የሀገር ባለውለታ መሆናቸውን ታሪክ ይመሰክራል፡፡
ከድል በኋላ በ1935 ዓ.ም በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዳንግላ ከተማ ትምህርት ቤት ተሰይሞላቸዋል፡፡ ትውልዱ ሀገር
ወዳድነትን እና መስዋእትነትን እንዲማር ታሪካቸውን የማስተዋወቅ ሥራ ሊሠራ እንደሚገባም አቶ አሳየ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous article“አርበኛ ሸዋረገድ ገድሌ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው በጎ ማድረግን በዓለማዊ ሕይወታቸው ደግሞ ሀገር መውደድን፣ ለዓላማ ጸንቶ ማሸነፍን አስተምረዋል” የታሪክ ምሁር
Next articleʺአልጎድል ስላለ ብለውት ብለውት የመከራውን ጎርፍ በደም ተሻገሩት”