
“አርበኛ ሸዋረገድ ገድሌ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው በጎ ማድረግን በዓለማዊ ሕይወታቸው ደግሞ ሀገር መውደድን፣ ለዓላማ ጸንቶ
ማሸነፍን አስተምረዋል” የታሪክ ምሁር
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 27/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ሴት አርበኞች ታሪክ ውስጥ ቀድመው ይጠራሉ፡፡ ትውልዳቸው ሰሜን
ሸዋ ተጉለት አካባቢ ነው፡፡ አባታቸው አቶ ገድሌ በአጼ ምኒልክ ቤተመንግሥት የአገልጋይነት ሚና ነበራቸው፡፡ በቤተሰቦቻቸው
እንክብካቤ አድገው በዘመኑ የነበረውን የቤተክህነት ትምሕርት ተምረዋል፡፡ በአካባቢው ወግና ባሕል መሰረትም ከፊውታራሪ
ደቦጭ ጋር ጋብቻ ፈጽመዋል- አርበኛ ሸዋረገድ ገድሌ፡፡ ጋብቻው ግን መዝለቅ የቻለ አልነበረም፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ
ሸዋረገድ በሴቶች ላይ የሚደርስን ግፍና ጭቆና አልቀበልም በማለታቸው ነው፡፡
ጋብቻቸውን ካፈረሱ በኋላ ለምናኔ በነበራቸው ፍላጎት ለሦስት ዓመታት በደብረ ሊባኖስ ገዳም ነዳያንን እና መናንያንን በመመገብ፣
ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም አቅንተው ለሦስት ዓመታት አገልግለዋል፤ በኋላም በአባታቸው ጉትጎታና ልመና ወደ እናታቸው የትውልድ
ስፍራ ተመልሰው በዚያ ኖረዋል፡፡
የጉለሌ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያንን አስተክለዋል፤ በአምስት ዓመቱ የፋሽስት ኢጣሊያ ጦር ወረራ ኢትዮጵያ ለተቀዳጀችዉ
ድል አይተኬ ሚና ነበራቸው፡፡ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አሥተዳደር መምሕር አቶ የሽዋስ እስከዚያ አርበኛ
ሸዋረገድ ገድሌ ከ1928 ዓ.ም እስከ 1933 ዓ.ም በነበረው የኢጣሊያ ጦርነት ስማቸውን በደማቅ ቀለም የጻፉ ሴት አርበኛ
ናቸው ብለዋል፡፡
እንደ ምሁሩ ገለጻ ሸዋረገድ ወደ አርበኝነት ከመግባታቸው በፊት በንግድ ሥራ ተሠማርተው በርካታ ሠዎችን አግዘዋል፡፡ ዘይት
በማምረትና በመሸጥ ውጤታማ ሥራ ሠርተዋል፡፡ ባንክ በመጠቀምና አክሲዮን በማቋቋም ዘመናዊነትን አስፋፍተዋል፡፡
በተሠማሩበት የበጎ አድራጎት ሥራ አርዓያነታቸውን አስመስክረዋል፡፡
በ1927 ዓ.ም ለተመሠረተው የቀይ መስቀል ማኅበር ንብረታቸውን ሸጠው አበርክተዋል፤ የማኅበሩ ሰብሳቢ በመሆንም
አገልግለዋል፡፡
በ1928 ዓ.ም ጣሊያን ኢትዮጵያን በግፍ ስትወር የአርበኝነትን መንገድ ካቀጣጠሉ ሴቶች አንዷ ናቸው፡፡ በጦርነቱ ወቅት መረጃ
በማቀበል፣ መድኃኒት በመላክ እና መሣሪያ በመግዛት የማይተካ ሚና ተወጥተዋል፡፡ በዚህ የተነሳ 12 ጊዜ ታስረው የተፈቱ፣ እስከ
ሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ነገር ግን ወደ እድሜ ይፍታሽ የተቀየረላቸው አርበኛ ናቸው፡፡
ሸዋረገድ ገድሌ ከሀገር ወጥተው አዚናራ ወደ ምትባል ከሰርዲኒያ ሰሜናዊ ምዕራብ በነበረች ደሴት በታሠሩ ወቅት የአርበኝነት
ሥራቸውን የበለጠ ይሠሩ ነበር፡፡ ሚስጥራዊ መልዕክት አንድ የጅቡቲ ወዳጃቸው በሰጣቸው ‘‘ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ’’
የሚል ጽሑፍ ባለበት ወረቀት ከንጉሡ የተላከ መልዕክት በማስመሰል ለአርበኞቹ መረጃ ያደርሱ ነበር፡፡ ትግሉ በተፋፋመ ሠዓት
ጦር መርተው ራሳቸው እስከ መዋጋት ደርሰዋል፡፡
ሽምቅን በማደራጀት፣ ጸረ ቅኝ አገዛዝ ትግሉን በማፋፋም፣ የጠላትን ደካማ ጎን በመለየት እና ግልጽ መረጃ በማድረስ የጠላት
ምሽግ እንዲደረመስ አድርገዋል፡፡
የታሪክ ምሁሩ እንዳሉት ሸዋረገድ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው በጎ ማድረግን፣ ለሌሎች መስጠትን፣ በዓለማዊ ሕይወታቸው ሀገር
መውደድን፣ ለዓላማ ጸንቶ ማሸነፍን አስተምረዋል፡፡ ግላዊ ነጻነትን ላለማስነጠቅ ጭቆናን እምቢ ብሎ መውጣት፣ ከነ ገረሱ ዱኪ
እና ጃገማ ኬሎ ጋር ያደረጉት ትብብር ለአንድነት ከከፈሉት ዋጋ ውስጥ ይቆጠራል ብለዋል፡፡
አርበኛ ሸዋረገድ ገድሌ የኢጣሊያ ጦር በጀግኖች አርበኞች ድል ተመቶ ኢትዮጵያ ነጻ ስትወጣ ለእድሜ ይፍታሽ ከታሰሩበት
ከአዚናራ ደሴት በነጻነት ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡
አርበኛ ሸዋረገድ ጥቅምት 22/1942 ዓ.ም ነበር ህይወታቸው ያለፈው፡፡ የአሁኑ ትውልድ ከአርበኛ ሸዋረገድ ገድሌ የዓላማ
ጽናትን፣ የሀገር ፍቅርን፣ አልበገር ባይነትን፣ በጎ ማድረግን ሊማር ይገባል ብለዋል ምሁሩ፡፡ እኒህን ለጠላት ያልተበገሩ አርበኛ
ስማቸው ከመቃብር በላይ ሆኖ ትውልድ እንዲማርበት ማስተዋወቅ ተገቢ እንደሆነም መክረዋል፡፡
በትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m