
ፖለቲከኞች፣ ምሁራን እና የመገናኛ ብዙኃን ታሪክን የስሜት መቀስቀሻ ከማድረግ ተቆጥበው ለጋራ አብሮነት ታሪክ ያለውን ፋይዳ ሊያስቀድሙ እንደሚገባ የአርበኛ ልጆች እና አባቶች ተናገሩ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 27/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአንድ ሀገረ መንግሥት የትናንትና የዛሬ ታሪክ ሲመዘዝ ከሀገር ምስረታው አሁን እስካለንበት ያለውን መረጃ የያዘ ኾኖ በመጥፎና በመልካም የተሠሩ ኹነቶችን የተቀበለና የደመረ ሊሆን ይገባል፡፡ ታሪክ የግድ ሁሉንም በእኩል ደረጃ እንዲያግባባ አይጠበቅም፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን በምሁራንም ኾነ በፖለቲከኞች መካከል የሚታየው ከእውነታ ያፈነገጠ የታሪክ አረዳድ በጋራ ቆመን ያስመዘገብነውን ታሪክ በተሳሳተ መንገድ መወሰዱ ሀገርንም ሕዝብንም ዋጋ እያስከፈሉ ቀጥለዋል፡፡
በ80ኛ ዓመት የአርበኞች የድል በዓል በአዲስ አበባ ሲከበር አሚኮ የአርበኛ ልጆች እና አባቶችን አነጋግሯቸዋል፡፡
አባት አርበኛ አበራ ሞልቶት “የታሪክ አተያይ እና አረዳዳችን መፈተሸና ታሪካችን የፖለቲካ ብቻ ሳይሆን ከዛ የተሻገረ እና በእሴት ውስጥ ሆኖ የተጋመደ መሆኑን የዚህ ትውልድ ተገንዝቦ የጋራ ታሪካችን ማስቀደም ይገባል” ብለዋል፡፡
ሌላው የበዓሉ ታዳሚ አቶ ያዝን የሽጥላ ፖለቲከኞች፣ ምሁራን እና የመገናኛ ብዙኃን ታሪክን የስሜት መቀስቀሻ ከማድረግ ተቆጥበው ለጋራ አብሮነታችን ታሪክ ያለውን ፋይዳ ሊያስቀድሙ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ትውልዱ የታሪክ እውነታን ገልጦ እንዲመረምር እና ፖለቲከኞችም ኾኑ ምሁራን የጋራ እና የኛ የሆነውን ታሪክና ማንነት በማስገንዘብ በኩል ኃላፊነታቸውን ከተወጡ የማይካደውን የታሪክ እውነታ ለቀጣይ ትውልድ ማሻገር እንደሚቻልም ገልጸዋል፡፡ ፖለቲከኞች እና ምሁራን በጋራ ለሀገርና ለሕዝብ ሲሉ ተናበው መሥራት አለባቸውም ብለዋል፡፡
ከጥንታዊ የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ልጅ ኤርሚያስ ተሰማ እርገጤ “ትውልዱ ታሪክን የግጭት መቆስቆሻ ከማድረግ ተቆጥቦ ከትናንት የኛ ታሪክ መማርን ማስቀደም እንጅ በተሳሳተ የታሪክ ንግርት ለመኖር መሞከር ዋጋ ያስከፍላልና መታረም ይገባል” ነው ያሉት፡፡
በጽንፍ ፖለቲካ ውስጥ ቆመው ታሪክን ማዛባት ላይ የሚሠሩ ሰዎች መብዛት አሁንም ዋጋ እያስከፈለ ቀጥሏል ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ ለግል የፖለቲካ ፍጆታ ሲባል የሕዝብን አብሮነት ለመናድ የሚሠሩ አካላትን መታገል አለብን ብለዋል፡፡
የተሳሳተ የታሪክ ንግርት ለችግር እየዳረገ በመኾኑ የትናንት ታሪክን በማንበብ፣ በመጠየቅና እውነታውን በመረዳት “ዛሬና ነገን” የተሻለ ለማድረግ በጋራ መሥራት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ጋሻው ፈንታሁን – ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m